አባታችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ያላቸውን የአገልግሎትና የሕይወት ተሞክሮ እንዲያካፍሉን እንግዳ አድርገናቸዋል ተከታተሏቸው፦
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ፈቃደኛ በመሆንዎ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። ስለ ልጅነት ሕይወትዎ ይንገሩን? የት ተወለዱ? የት አደጉ? የእናትና የአባትዎ ስም ማን ይባላል? የቤተሰብዎን ሁኔታ አያይዘው ቢነግሩን።
ሊቀ ትጉሃን ደሴ መኮንን፦ እኔም ይህን ቃለ መጠይቅ ከእናንተ ጋር እንዳደርግ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። የተወለድኩት በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ስማዳ ወረዳ ልዩ ቦታው እመሠዋ ደብር በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ነው። አባቴ ካህን ናቸው መምሬ መኮንን ጣሹ ይባላሉ ፤እናቴ እማሆይ አስናቀች በለው ይባላሉ። የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት በዚያው በተወለድኩበት አካባቢ ሲሆን እንደማንኛውም የገጠር ልጅ የቤተሰቦቼን ከብት በእረኝነት በመጠበቅ ነው። በኋላም ወደ አብነት ትምህርት ቤት ገብቼ በዲቁና ማዕረግ ማገልገል እንደጀመርኩ ከአሁኗ የትዳር አጋሬ ወ/ሮ አስጥይው አበጀ ጋር የካቲት ፲፱ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ.ም በሥርዓተ ተክሊል ጋብቻችንን ፈጽመናል። ሰባት ልጆች እና ሰባት የልጅ ልጆች ያደረስኩ ሲሆን ከነዚህ ከሰባቱ ሁለቱ ልጆቼ በሕይወት የሉም።
ስምዐ ጽድቅ፦ ስለ አብነት ትምህርት ቤት ሕይወትዎ ይንገሩን የት የት ተማሩ?
ሊቀ ትጉሃን፦ ትምህርት የጀመርኩት እዚያው የተወለድኩበት እመሠዋ በዓታ ደብር ነው። በዚያ ከባሕታዊ አባ ገብረ መስቀልና ከአለቃ ወልደ ገብርኤል ከፊደል ጀምሮ ዳዊትን፣ በስማዳ አርባዕቱ እንስሳ ደብር ከመሪጌታ አካል ተፈራ ውዳሴ ማርያም ዜማን ተማርኩ፤ በጋይንት አትከና ጊዮርጊስ ከመሪጌታ ክፍሌ ጾመ ድጓና ምዕራፍ እንዲሁም መዝገብ ቅዳሴን ተምሬ አጠናቀቅሁ። እነዚህን ትምህርቶች ከተማርኩ በኋላ በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም እዚያው ጎንደር ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል የዲቁና ማዕረግ ተቀበልኩ።
ስምዐ ጽድቅ፦ ማዕረገ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ የት የት አገለገሉ? ምን ያህል ጊዜ አገለገሉ
ሊቀ ትጉሃን፦ የዲቁና ማዕረግን ከተቀበልኩ በኋላ አገልግሎት የጀመርኩት በዚያው በተወለድኩበትና ባደኩበት እመሠዋ በዓታ ደብር ነው። በግንቦት ወር በ፲፱፻፶፯ ዓ.ም እዚያው ጎንደር ከብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅስናን ማዕረግ ተቀበልኩ። በዚሁ ደብር እና በአካባቢው ባሉ የተለያዩ ደብራት በቅስና መንፈሳዊ አገልግሎትንም ስሰጥ ቆየሁ።
በእመሠዋ በዓታ ደብር በቋሚነት እንዲሁም በአካባቢው ላይ ባሉ ሌሎች ደብራት አልፎ አልፎ በቅስና ማዕረግ ሳገለግል የቆየሁት እስከ ፲፱፻፷፭ ዓ.ም ድረስ ነው። በዚሁ ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ከትውልድ ሀገሬ ለቅቄ ወደ ሸዋ ክፍለ ሀገር በመምጣት ዝቋላ አካባቢ እምቦሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በቅስና ማዕረግ ተቀጥሬ ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር አገለገልኩ። በዚያ ደብር እና አጎራባች በሆኑ ደብራት ላይ በመዘዋወር አስተምር ነበርና ቁጥራቸው ከሦስት መቶ በላይ የሆኑ ኢ-አማንያንን በማስተማር እና በማጥመቅ የሥላሴ ልጅነት እንዲያገኙ አድርጌአለሁ። እዚያ ግን ብዙ መቆየት አልቻልኩም።
ስምዐ ጽድቅ፦ ለምን? ምንድን ነበረ ምክንያቱ?
ሊቀ ትጉሃን፦ በእምቦሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እና በአካባቢው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የጀመርኩትን ሐዋርያዊ አገልግሎት በስፋት እንዳልሰጥ እንቅፋት ገጠመኝ። እንደሚታወቀው ወቅቱ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም አብዮት የፈነዳበት ፤የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የወደቀበት እንዲሁም ሥልጣኑን ከተረከበው የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም አንጻር የእኔ አስተምህሮ እንደ ኃጢአት በመቆጠሩ በጊዜው እና ዘመን ባመጣቸው ባለሥልጣናት ወከባው በዛብኝ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ከዚያች ከተማ ቢያሳድዱአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ›› ማቴ ፲፥፳፫ ባለው አምላካዊ ቃል በዚያ አካባቢ ተዘዋውሬ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሌ እና በገጠመኝ ከፍተኛ ተቃውሞ ከሥራዬ በመፈናቀሌ በአቴን ለቅቄ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ደጅ ጠኝ ሆንኩ። ከሁለት ዓመት ደጅ ጥናት በኋላም በ፲፱፻፷፰ ዓ.ም በወቅቱ በነበሩት የካቴድራሉ አለቃ መምህር ገብረ ሚካኤል በኋላ ብፁዕ አቡነ ሣሙኤል መልካም ፈቃድ በቅስና የሥራ መደብ ተቀጥሬ አገልግሎት ጀመርኩ።
ስምዐ ጽድቅ፦ እስካሁን ድረስ በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል እያገለገሉ መሆኑ ይታወቃል ከዚያም በተጨማሪ የተለያዩ ታላላቅ መንፈሳዊ ሥራዎች እንደሠሩ ይነገራልና እስኪ ስለዚያ ይንገሩን?
ሊቀ ትጉሃን፦ እውነት ነው እስከ አሁን እዚያ ነው እያገለገልኩ ያለሁት። አገልግሎቴ በቋሚነት እዚያ ይሁን እንጂ ከካቴድራሉ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ብዙ የልማት ሥራዎችን ስሠራ ቆይቻለሁ። በካቴድራሉ የሰበካ ጉባኤ አባል ሆኜ ካቴድራሉን ከማሳደስ ጀምሮ በግቢው ውስጥ የተለያዩ ሕንጻዎች ሲሠሩ፣ የግቢው አስፋልት ሲታደስ እንዲሁም በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ስም ሊሰየም የነበረው የጎፋ ገብርኤል አደባባይ ሲሠራ ምእመናንን በማስተባበር ገቢ ሳሰባስብ ቆይቻለሁ፤ በካቴድራሉ ውስጥ እጅግ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤት አስገንብቻለሁ። ቋሚ የአገልግሎት ቦታዬ ጎፋ ገብርኤል ቢሆንም በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ኢ-አማንያንን በማስተማር የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ አድርጌአለሁ። አብያተ ክርስቲያናት በሌሉባቸው ቦታዎች በመሄድ ምእመናንን በማስተባበር ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አስተክያለሁ፡ አሁንም አቅሜ በፈቀደ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገልኩ እገኛለሁ። ወደፊትም ከዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ አገልግሎት እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ አልለይም።
ስምዐ ጽድቅ፦ ከነዚህ የልማት ሥራዎች ባሻገር ስለ አሳነጹአቸው አብያተ ክርስቲያናት በዝርዝር ይንገሩን
ሊቀ ትጉሃን ፦ ከመደበኛ አገልግሎቴ ውጪ ምእመናንን በማስተባበር በተለያዩ ቦታዎች ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አስተክዬ ለምእመኑ አገልግሎት እንዲሰጡ አስደርጌአለሁ። ለምሳሌ፦
- ሐምሌ ፳፭ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የኤረር ጎሮ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የፉሪ ምስካበ ቅዱሳን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፤ጥር ፳፯ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የመቱ አልዩ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ መጋቢት ፳፰ ቀን ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የደብረ በረከት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፤ጥር ፰ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የፈለገ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን፤ ሰኔ ፳፭ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው የዓለም ባንክ አካባቢ የደብረ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከአሠራሁአቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ጎንደር በተወለድኩበት አካባቢ ስማዳ ወረዳ የምትገኘው ታላቋ የበዓታ ደብር ከፍተኛ እድሳት ሲደረግላት በአዲስ አበባ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆችና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ለእድሳቱ ከሚፈለገው ሦስት እጅ የሚሆነውን በደረሰኝ በመሰብሰብ እና በማስረከብ ደብሩ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ እንዲታደስ የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌአለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመን ውስጥ የገጠመዎት ጥሩም ሆነ መጥፎ ገጠመኝ ካለዎት ይንገሩን
ሊቀ ትጉሃን፦ በሰው ሕይወት ውስጥ ብዙ ገጠመኞች ይኖራሉ። በዚያው ልክ ጥሩ እና መጥፎ ገጠመኞች ይፈራረቃሉ፤ እኔም በነዚህ ሁለት ተቃራኒ ሕይወቶች ውስጥ አልፌአለሁ ስለሁሉም ነገር ግን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በሕይወቴ ውስጥ እጅግ የምደሰትበት እና በጎ የሕይወት ገጠመኝ ብዬ የምለው እግዚአብሔር አምላክ ፈቅዶልኝ በተለያዩ ቦታዎች ምእመናን የሚሰበሰቡበት፣ ክርስትና የሚነሱበት፣ ንሰሓ የሚገቡበት፣ ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉበት እንዲሁም ሲሞቱ በሥጋ የሚያርፉበት አብያተ ክርስቲያናትን ማሳነጽ መቻሌ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እርካታዬና ደስታዬ ነው።
ሌላው እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች መንፈሳዊ ሥራዎችን ስሠራ የገጠሙኝ መጥፎ ገጠመኞች መቼም የምረሳቸው አይደሉም። ጊዜም እንዳልወስድ ከነዚያ ውስጥ ጥቂቱን እናገራለሁ። ቅድም ለመግለጽ እንደሞከርኩት በዝቋላ አካባቢ እምቦሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እያገለገልኩ በተጓዳኝ ያላመኑ ምእመናን እንዲያምኑ፤ ያመኑ ክርስቲያኖች እንዲጸኑ ወንጌልን በምሰብክበት ጊዜ በደርግ ወታደሮች ‹‹ዐቢዮቱን የሚቃወም እና ደርግን የሚፃረር›› በሚል ብዙ እንግልት ደርሶብኝ ከሥራ እስከመፈናቀል ደርሻለሁ። በዚያ በደረሰብኝ እንግልትም አካባቢውን ለቅቄ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። አዲስ አበባ መካነ ሕያዋን ጎፋ ገብርኤል ካቴድራል ያለሥራ ለሁለት ዓመት በደጅ ጠኚነት ከተቀመጥሁ በኋላ በቅስና ማዕረግ ተቀጥሬ አገልግሎት ጀመርኩ።
አዲስ አበባ ጎፋ ገብርኤል ካቴድራል በቅስና ባገለግልም ክርስትናን የማስፋፋት፣ ምእመናንን የማብዛት እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትን የማስተከል ሐሳብ ከመጀመሪያው ውስጤ ስለነበረ ወደተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስተከል እንቅስቃሴ ጀመርኩ። በመጀመሪያም የላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ለማሠራት የተወሰኑ ኮሚቴዎችን ይዤ በየእድሩ እየሄድን ቤተ ክርስቲያኑ ይሰራ ዘንድ ፊርማ እናሰባስብ ነበር። ይህን ያዩት ፀረ ሃይማኖት የደርግ ባለ ሥልጣናት ‹‹ዐብዮቱን ለመቀልበስ የሚንቀሳቀሱ የኢዲዩ ቅጥረኞች በተለይም የጄኔራል ነጋ ተገኝ ዘርና ተልእኮ ፈጻሚዎች ናቸው›› በሚል ሽፋን ተይዘን ወደ እስር ቤት ተወረወርን።
እኔ በታሰርኩበት በዚያ የችግር ወቅት ሥራዬ በመታጎሉና የሚሸፍንልኝም ሰው ባለማግኘቴ ከጎፋ ገብርኤል ካቴድራል ይከፈለኝ የነበረው ደሞዜ ተቋረጠ። በዚህ መሀል ለምግብ የደረሱ ለሥራ ግን ያልደረሱ ልጆቼ እና የቤት እመቤት የሆነችው ባለቤቴ ለችግር ተጋለጡ፤ የሚለብሱት እና የሚበሉት እስኪያጡ የችግር ዶፍ ወረደባቸው። ባለቤቴ ደብዳቤ በመጻፍ ከደብሩ ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ ተንከራተተች፤ እርስዋን ከሕፃናት ልጆቼ ጋር የሚታደግ ግን አልተገኘም። ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድም ደሞዜን እንዲሰጧት እና ሕፃናቱን ከረኃብ እንድትታደግ ብትለምንም ‹‹የሚሠራው እዚህ ደብር ሲሆን ወደ ሌላ ቦታ የሄደው በጥጋብ ነውና ላልሠራበት አንከፍልሽም›› በማለት ሲመልሱአት አይዞሽ የሚል ረዳት አልነበራትም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት በጽናት ያንን የመከራ ዘመን አልፈነዋልና እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ምክንያቱም ከዚያ እስር ቤት ስወጣ ተመልሼ አብያተ ክርስቲያናትን ወደ ማሳነጽ ነው የሄድኩት። ሐዋርያው ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ረኀብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? መራቆት ነውን ?ሾተል ነውን? ሮሜ ፰፥፥፴፭ እንዳለው የሚደርስብኝን መከራና ችግር ሳልሰቀቅ ዛሬም ድረስ እግዚአብሔርን እያገለገልኩት እገኛለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን በመጨረሻ የሚያስተላልፉት ወይም ቀረ የሚሉት ነገር ካለ
ሊቀ ትጉሃን፦ የሰው ልጅ ወደዚህ ምድር የመጣው እግዚአብሔርን ሊያመሰግን፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊኖር፣ እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ሥራ ሊሠራ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ለእኛ ካደረገልን አንጻር እኛ ለእርሱ ምንም አላደረግንለትም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ፣በዚህ ምድር ተመላልሶ ያስተማረው መጨረሻም ሊያድናቸው፣ ሊታደጋቸው መከራ ሞት መቀበሉ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ነው፤ እኛ ግን እንደ ሐሳቡ አልተመላለስንም ፡ ባስቀመጠን ቦታ አልተገኘንም፣ጊዜ ሞታችንን እያሰብን እንኳ ተዘጋጅተን እየጠበቅነው አይደለም። የክርስቲያን ሥራው ግን ከዚህ ሊያልፍ ይገባዋል እላለሁ። ይልቁንም እኛ ካህናት ድርብ አገልግሎት አለብን ብዙዎቻችን ዛሬ በዐሥራ አምስት ቀን አንዴ የሚሰጠንን የቤተ መቅደስ አገልግሎት ብቻ ይዘን ነው ቁጭ ያልነው። ነገር ግን ወጥተን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልንሰብክ፣ ያዘኑትን ልናረጋጋ፣ የታሰሩትን፣ የታመሙትን ልንጠይቅ፣ ልንደግፍ ይገባል። በአጠቃላይ ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ እኛ ካህናት ትጉህ እረኛ ልንሆን ይገባል።
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።
ሊቀ ትጉሃን፦ እግዚአብሔር ይስጥልኝ እኔም አመሰግናለሁ።