Saturday, 15 May 2021 00:00

“ የአብነት መምህራን የቤተ ክርስቲያን ዓይኖች ናቸው” - ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም

Written by  መጽሐፈ ሲራክ
የዛሬው የቤተ አብርሃም ዐምድ እንግዳችን ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም ይባላሉ። ከተድባበ ማርያም ቀጥሎ በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነገሥታቱ በአብርሃ ወአፅብሃ (ኢዛና ና ሳይዛና)  ዘመነ ንግሥና  እንደተተከለ በሚነገርለት የማኅደረ ስብሐት ኦፍና ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም እና የድጓ መምህር ናቸው።  በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐ ቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ከሚገኘው የማኅደረ ስብሐት ኦፍና ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ፴፭ ዓመታት ወንበር ዘርግተው በማስተማር ብዙ መምህራን ሊቃውንትን አፍርተዋል። ከሕይወት ልምዳቸው፣ ከአብነት ትምህርት ቤት ሕይወታቸው እንደሚከተለው አካፍለውናልና እንከታተላቸው።  ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ፈቃደኛ በመሆንዎ በእግዚአብሔር ሥም እናመሰግናለን። ሙሉ ስምዎትን ከነማዕረግዎ እንዲሁም በደብሩ የአገልግሎት ድርሻዎትን ጭምር  ቢገልጹልን?  ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም፦ እኔም መጠይቅ ምላሽ እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም እባላለሁ በደብሩ  የአቋቋም እና የድጓ መምህር ነኝ።    ስምዐ ጽድቅ፦  አባታችን የት፣ መቼ ተወለዱ? የልጅነት ሕይወትዎ በተለይ የአብነት ት/ት ቤት ሕይወትዎ ምን ይመስላል?   ሊቀ ጠበብት፦ ቀኑን እና ወሩን ለይቼ ባላውቀውም የተወለድኩት በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐ ቤቴ ወረዳ ልዩ ስሙ በሬቻ ገነተ ጊዮርጊስ በሚባል ደብር ነው። ፯ ዓመት ሲሞላኝ እናትና አባቴ በዚያው ደብር ከሚገኝ  የአብነት ት/ቤት አስገቡኝ። በዚያ የመጀመሪያው ፊደል ያስቈጠሩኝ መምህሬ አባ አሰፋ ይባሉ ነበር። እሳቸው በማረፋቸው አባ ነጋሽ ከሚባሉ መምህር  ቀጠልኩ። ከሰባት እስከ አሥራ አንድ ዓመቴ ድረስ ከፊደል ጀምሮ መውዳሴ ማርያም፣ ዳዊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ማዕረገ ዲቁናን ተቀበልኩ።  ከዚያ በረመሽድ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአራት ዓመት በዲቁና አገልግያለሁ። አራት ዓመት በዲቁና እንዳገለገልኩ አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላኝ ወደ ላይ ቤት ዓለም ከተማ ማኅደረ ስብሐት ቅዱስ አማኑኤል በመሄድ የድጓ መምህር ከነበሩት መምህር በቃሉ ባይነሳኝ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ እና ድጓ ከየኔታ የማነ ብርሃን መዝገበ ቅዳሴ፣ ከአለቃ ሐረገወይን ዝማሬ መዋሥዕት፣ ከመምህር ዕፁብ አቋቋም ተምሬአለሁ።  ወደ ቤጌምድር በማቅናትም ዘመንዬ በዓለ እግዚአብሔር ከሚባል ደብር መምህር ከነበሩት እና አሁንም ድረስ በሕይወት ካሉት (አዲስ አበባ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ናቸው) ከመምህር ዘካርያስ ቅኔን ከነአገባቡ አጠናቀቅሁ። ከዚያም ጎንደር በመሄድ ከየኔታ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል (የአቋቋም መምህር) ዘንድ ለስድስት ዓመት ያህል አቋቋም ተምሬ አጠናቅቄአለሁ። እሳቸውም ብቃቴን አይተው ወገራ ወረዳ አይባ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከምትባል ደብር እንዳስተምር ፈቅደው ስለላኩኝ ለሦስት ዓመት ያህል አቋቋም አስተምሬአለሁ።  በዚያም በማስተምርበት ጊዜ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቻለሁ። በሦስቱ ዓመት ብቻ ያስተማርኩአቸው ከ፪፻ በላይ ይሆናሉ።  ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላም በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም ወደ ትውልድ ሀገሬ ዓለም ከተማ ተመልሼ በማኅደረ ስብሐት ኦፍና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ማስተማር ጀመርኩ ማለት ነው። እንግዲህ እስከ አሁን በዚሁ ሞያ ነው ያለሁት ወደ ፴፭ ዓመት ሆኖኛል፤ ወንበር ዘርግቼ ማስተማር ከጀመርኩ ማለት ነው። ስምዐ ጽድቅ፦  በዚህን ያህል የማስተማር ዘመንዎ ምን ያህል ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል? ከዚሁ ጋር  ‹ኦፍና› ማለት ምን ማለት ነው? አያይዘው ቢመልሱልን?   ሊቀ ጠበብት፦ በዚህ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ለአገልግሎት ብቁ የሆኑ ከ፮፻ በላይ የሚሆኑ አገልጋዮችን አውጥቻለሁ። ሌላው ‹ኦፍና› የቤተ ክርቲያኑ መጠሪያ ሲሆን ሁለት ትርጉም ያለው ነው አንዱ ‹ኦፍና› ማለት ወደ መልካም ቦታ መርቶ የሚያደርስ ታላቅ ጎዳና ማለት ሲሆን ፤ሁለተኛው ‹ኦፍና› ማለት እግዚአብሔር የቀረበው ቦታ ማለት ነው።   ስምዐ ጽድቅ፦ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የቤተሰብዎ አስተዋጽኦ ምን ያህል ነበረ? ሊቀ ጠበብት ፦ ቤተሰቦቼ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልነበራቸው  ምእመናን ስለነበሩ የእነርሱ ፍላጎት ለዲቁና ያህል ተምሬ በትዳር ተወስኜ እንድኖር ማለትም ከእነርሱ እንዳልርቅ ነበር። እዚህ መድረሴ የእግዚአብሔር ምርጫ ነው ብዬ አምናለሁ። ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ ነው እዚህ የደረስኩት ማለት ነው። እነርሱም ብዙ አልቆዩም ዐሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ሁለቱም በተከታታይ ስለሞቱ ብቸኛ ነበርኩ። ነገር ግን እግዚአብሔርም  በሄድኩበት አልጣለኝም። ‹‹ሰዓሊ ለነ ቅድስት›› እያልኩ ስሟን የምጠራው እመቤታችን ከጎኔ ስላለች በእርስዋ ምልጃ ነው እዚህ የደረስኩት። ስምዐ ጽድቅ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወትዎ በሁሉም ነገር አብነት ሆነውኛል የሚሏቸው ሊጥቀሱልን ይችላሉ ? በተለይ ከመምህራኑ  ሊቀ ጠበብት ፦ ብዙዎቹ መምህራን ለኔ አብነት ናቸው። በሕይወተ ሥጋ የሌሉም ያሉም አሉ። በሕይወተ ሥጋ ካሉት መምህር ዘካርያስ በማስተማር (እውቀት) አብነቴ ናቸው። የኔታ ሄኖክ ስመ ክርስትናቸው ወልደ ሊባኖስ፣ የኔታ ዕፁብ ስመ ክርስትናቸው ገብረ ኢየሱስ፣ መምህር በቃሉ የድጓ መምህሬ ‹‹ድጓን ተመራመር›› ያሉኝ እና ስማቸውን የስሜ መጠሪያ እንዲሆን የሰጡኝ ቅን መምህር ነበሩ። ሌላው በመጀመሪያ ዳዊት ያስደገሙኝ መምህር ገብረ መስቀል በሕይወቴ ውስጥ ለዛሬው ማንነቴ አብነት የሆኑኝ ናቸው።ዛሬም ዳዊት በደገምኩ ቊጥር  የክርስትና ሥማቸውን  በጸሎቴ አነሳለሁ፤ በፍፁም ከሕሊናዬ አይወጡም። ምክንያቱም ያምንም ደመወዝ በቅንነት ከእውቀታቸው ሳይሰስቱ ያስተማሩኝ ናቸውና። ያሉትን እያሰብኩ የሌሉትን ‹እግዚኦ ዐዕረፍ ነፍሳተ መምህራን› እያልኩ እጸልያለሁ።  እውነት ለመናገር በሕይወት ኖረው እንደአቅሜ ብረዳቸው ኖሮ ደስ ይለኝ ነበረ።  ከማስተማር በተጨማሪ የኔታ ዕፁብ በእውነት ትሑት መምህር ናቸው። ከትንሹም ከትልቁም ጋር መዋል የሚችሉ ቅን አባት ናቸው። በምሁርነትም ታዋቂ ናቸው ቃለ እግዚአብሔር የሚይዝላቸውን በጣም ይወዱ ነበረ። የራሳቸው ማዕድ አልነበራቸውም ከተማሪ ጋር አንድ ላይ ነበር የሚበሉት። ተማሪ ሲራብ ሲራቆት ደስ አይላቸውም ‹‹ልብስ የለህም ወይ?›› ብለው ይጠይቃሉ የሌለው ተማሪ ካዩ የራሳቸውን ነው የሚሰጡት። የድጓ መምህሩ የኔታ በቃሉ የቃለ እግዚአብሔር ሰው ናቸው። ስናጠፋ ይቈጡናል፤ ነገር ግን ለራሳችን ብለው ነው። አስተምረውን ሲጠፋብን ‹‹የት ሄደህ ነው የሚጠፋብህ›› ብለው ይቈጡናል። በትጋት እንድንከታተል ነው።  ስምዐ ጽድቅ፦ አገልግሎት ከጀመሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን የት የት አገለገሉ? ሊቀ ጠበብት ፦ በልጅነቴ ለአራት ዓመታት ያህል በረመሽድ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዲቁና አገልግያለሁ። በአፍላነቴ ወገራ ወረዳ አይባ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ለሦስት ዓመታት አቋቋም አስተምሬአለሁ። በዚያን ጊዜ ፳፬ ሰዓት ነበር የማስተምረው። ሳስተምር በሁለት መንገድ ነው በወንበር (በጉባኤ ቤቱ)  በቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ። ዋናው ነገር ለተማሪ ቤተ ክርስቲያን ናት የምታስተምረው። በወንበር የተማሩትን ቀለም መነሻ መድረሻውን በትክክል በተግባር እንዲያውቁ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሰዓት በሁለት ሰዓት እንዲደወል አደርግና ግዴታ ማኅሌት እንቆማለን። ለምሳሌ በትንሣኤ፣ በዳግም ትንሣኤ በጰራቅሊጦስ የትንሣኤን ቀለም ከመዝሙር ጀምረን ፍፃሜው እንዲዘለቅ አደርግ ነበር። በዚያ ላይ የከበሮ አመታት፣ የጽናጸል አወራወር፣ ማቆም ማሳረፍ፣ የወረቦች አመላለሶች አጠቃላይ የማኅሌቱን ሥርዓት በተግባር እንዲዲለማመዱ አደርግ ነበረ። ወደዚህም ደብር ከመጣሁ በኋላ በዚሁ መንገድ ነው የማስተምራቸው በቃል እና በተግባር ሁሉን በደንብ እንዲረዱት ነው የምፈልገው። በተፈጥሮዬ ለይስሙላ አስተምሬ ብትለው በለው ባትለው የራስህ ጉዳይ አልልም። የተማረውን ትምህርት ግዴታ በተግባር እንዲተረጉምልኝ ጥረት አደርጋለሁ። ዛሬ ግን ተማሪም ቀዝቀዝ እያለ እየሄደ ነው፤ ድካምም እየመጣ ነው ፤ እኔ እንኳ ለማስተማር አይደክመኝም ተማሪው ግን ሰንፏል እንደዱሮው አይደለም። ስምዐ ጽድቅ፦ ምክንያቱ ምንድነው ?  ሊቀ ጠበብት፦ ዛሬ ዛሬ ተማሪው እየሰነፈ ነው እውነቱን ለመናገር ከድሮው ቀንሷል። ዛሬ ሞባይል አለ ይቀርጽና ያን መስማት ይፈልጋል፤ ቢሆንም ከሰውነቱ አይዋሐድም አይቀረጽም  በቃል አይያዝም ተማሪውን አስንፎታል። ትምህርት ለተማሪው ከሰውነቱ የሚያዋሕደው ያን ቃለ እግዚአብሔር በደንብ አድርጎ ሲቀጽለው ነው። ዛሬ ከላይ ከላይ ነው መቃረም የሚፈልጉት እኔ ግን ተዉ በሚገባ ተማሩ እያልኳቸው ነው።  በእርግጥ ሁሉም በመጻሕፍት ታትመዋል ቢሆንም እንደጥንቱ በቃላቸው ነው መያዝ ያለባቸው። ተማሪዎች በቃላቸው እንዲይዙ እቈጣጠራለሁ ‹‹ሲጠፋችሁ ያን ተመልከቱ እንጂ መጽሐፍ ማየት ሞባይል ማዳመጥ ያሰንፋችኋል፤ መጀመሪያ በቃላችሁ በደንብ ያዙ›› እያልኩ እመክራቸዋለሁ። እኔ ስማር በጎንደርም በሌሎቹም ቦታዎች እንዲህ አይደለም ሞባይል የለም በቃላችን ነበር ሁሉን የምናጠናው። ተማሪው በቃሉ እንዲይዝ በቻልኩት መጠን እመክራለሁ እቈጣጠራለሁ። በዚህ ሂደት አገልግሎቴ ድሮም አሁንም አንድ ነው። ስምዐ ጽድቅ፦ በአሁኑ ሰዓት በቊጥር ምን ያህል ተማሪዎች አሉ? ሊቀ ጠበብት፦ በአሁኑ ሰዓት ወደ ፷ (ስልሳ)ተማሪዎች አሉ እነዚህ ተማሪዎች ይህን የአብነቱን ከዘመናዊው ትምህርት ጋር እያፈራረቁ እየተማሩ ነው። እኔም ተስፋ እንዳይቆርጡ ዘመናዊውንም ይህንንም ተማሩ እያልኩ እያበረታታሁ ነው።   ስምዐ ጽድቅ ፦ የተማሪው ቊጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነውና መሠረታዊ ችግሩ ምንድነው? ሊቀ ጠበብት ፦ ተማሪ የቀነሰበት የመጀመሪያው መሠረታዊ ችግር ልቦናው ተረጋግቶ እንዳይማር ወቅቱ አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ተማሪው ተረጋግቶ እንዳይማር የምግብ እና የልብስ ችግር አለበት። በኛ ጊዜ እንዲህ ችግር አልነበረም ፪፻ እና ፫፻ ተማሪ ነበር የሚማረው ያውም በየመንደሩ እየዞርን እየለመንን። መንደር ተካፍለን ነበር የምንለምነው ሕዝቡም ደግ ነበር ‹‹ በእንተ ስማ ለማርያም›› ብሎ ተማሪ ደጅ ከቆመ ነውር ነው ምግብ ሳይሰጡ አይሸኙትም በዓል ሲመጣ በክብር ተጠርቶ ነው። ዛሬ ተማሪው ወደ ገጠር ሄዶ ለመለመን ያፍራል ፣ ይሳቀቃል። ሕዝቡም እንደድሮ አይደለም ተማሪ ሲለምን ‹‹ሠርተህ አትበላም?›› የሚል መልስ ለተማሪው  ይሰጣል። ሕዝቡ በጥሩ ዓይን አያያቸውም እና ችግር ነው። እነዚህ አሁን ያሉት የተለያየ ሥራ እየሠሩ ራሳቸውን ለመደጎም ይሞክራሉ። ለምሳሌ ሙሬ (መጥረጊያ)፣ ወንፊት እያዞሩ ይሸጣሉ የአጨዳና የአረም ጊዜም ለሥራ ይሠማራሉ። በከተማውም የቀን ሥራ (ሲሚንቶ ማመላለስ፣ ድንጋይ ማጋዝ) የመሳሰሉትን ይሠራሉ። እንደዚህ ሆነው ነው የሚማሩት በዚህ የተነሳ ነው ተማሪ እየሸሸ ያለው። ከዚህም ሌላ ‹‹ራሴን የማያስችል ትምህርት ምን ያደርጋል? እኔ ራሴን የማያስችል ትምህርት ተማርኩ አልተማርኩ ምን ይጠቅመኛል?›› በማለት ተስፋ የሚቆርጡት ብዙዎች ናቸው። ‹‹እነ የኔታ ዛሬ ምን ደሞዝ አላቸው? ነው ጥያቄው እነሱ ምን አገኙና ነው እኛ የምንማረው?›› ይላሉ።  አሁን ትንሽ በማኅበረ ቅዱሳን የተያዘ ሥራ አለ በዚህ ጥሩ መንፈሳዊ ሥራ እየተሠራ ነው ያለው።  በኮረና በሽታ ብቻ እንኳ ብዙ እርዳታ ባለፈው ተደርጎላቸዋል። ከዚያን ወዲህ ነው ልባቸው የተረጋጋው። ችግራቸው ጠንክረውና ልባቸውን አስፍተው እንዳይማሩ ቃለ እግዚአብሔርን በትክክል እንዳይከታተሉ የሚበሉት፣ የሚለብሱት የላቸውም። እኛ ድሮ በርኖስ፤ ደበሎ እየለበስን ነበር የምንማረው፣ ተባዩ እከኩ ስንት ነገር ነበር? እርሱ የለም ቀርቷል። የዛሬዎቹ የሚፈልጉት ንጹህ ልብስ ነው ያን ለማግኘት ነው የሚጣጣሩት እኛ ግን በላያችን ላይ ምንም ቢወርድ ብንታመም ህልማችን ከሁሉ በላይ ቃለ እግዚአብሔር ነው።  ባጠቃላይ ተማሪዎቹ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ብለው ነው የሚያስቡት። የሚፈለገው እርዳታ ነው ባለፈው በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በመጣው እርዳታ ብዙ ተማሪዎች ረክተዋል። በጣም ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ኅብስተ ሠርክ  ማጣታቸው ነው። ከዚህ ውጪ ደግሞ የሚኖሩበት ጎጆ የላቸውም ጎጆውን ለመሥራት እንኳ እንጨት እና ሣር ችግር ነው። ተማሪው  እንጨት እና ሣር በመግዛት በተቻለው መጠን ባህሉ ትውፊቱ እንዳይጠፋ እያደረገ ነው። አሁን ግን አንገብጋቢውና ትልቁ ችግራቸው ቀለብና ልብስ ነው። ስምዐ ጽድቅ፦ የአብነት ትምህርት ቤቱ እንዳይስፋፋ በእርግጥ ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆኑ ነው የሚታየው ችግሩ እንዴት ይፈታል ይላሉ? ሊቀ ጠበብት፦ በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ቤተ ክህነቱ አብነት ትምህርት ቤቶቹ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። ይህን ስል ሙሉ ለሙሉ ትኩረት አልሰጠም እያልኩ አይደለም፤ ግን ብዙ ይቀራል። ቤተ ክህነት በየገጠሩ ያሉትን የአብነት ትምህርት ቤቶች በጀት ሊመድብላቸው ይገባል። የአብነት መምህራኑ ብዙዎችን ያፈሩ ዘንድ በወንበራቸው እንዲጸኑ በሥርዓት ሊያዙ፣ የተሻለ ክፍያ ሊያገኙ ይገባል የቤተ ክርስቲያን ዓይን ናቸውና። ቤተ ክርስቲያን ነገ የሊቃውንት ድኀ እንዳትሆን ዛሬ አብነት ት/ቤት ላይ መሥራት ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የተለያዩ ማኅበራት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የአብነት ት/ቤቱ እንዳይነጥፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል። ማኅበረ ቅዱሳን በተለያዩ ቦታዎች ባሉ የአብነት ት/ቤቶች ላይ እየሠራ ያለውን እኛም ስላየን ሊበረታታ ይገባል። ሌሎችም የእነርሱን ፈለግ ቢከተሉ ጥሩ ነው። ባጠቃላይ የአብነት ት/ቤት ምንጩ እንዳይደርቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እላለሁ። ስምዐ ጽድቅ፦ ከማስተማር በተጨማሪ የሠሩት ሥራ ይኖር ይሆን? ለምሳሌ መጽሐፍ በመጻፍ ሊቀ ጠበብት፦  ከማስተማር በተጨማሪ የጎንደርን ይትበሃል ጽፌ ታትሟል። ሌላው በዚህ በኛ ደብር ያለውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የየበዓላቱን ያሬዳዊ ወረቦች የመሳሰሉት የተካተቱበት መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ ነገር ግን ገና አልታተመም። ስምዐ ጽድቅ ፦ በሕይወት ዘመንዎ የተደሰቱበት ወይም ያዘኑበት ገጠመኝ ካለ ቢገልጹልን? ሊቀ ጠበብት፦ እንግዲህ መልካም እና ክፉ ነገሮች አንድ ላይ ነው የሚሄዱት ተወራርሰው ነው የሚኖሩት። የተደሰትኩባቸው ጊዜያት ነበሩ፤በተቃራኒው ከባድ ፈተና ደርሶብኝ ያውቃል። ከመልካሙ ልነሳና በሕይወት ዘመኔ የተደሰትኩበት ቀን ወገራ ከምትገኘው አይባ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከምትባል ደብር መምህሬ እንዳስተምር ፈቅደውልኝ ለማስተማር የሔድኩበት ጊዜ ነው። ሌላው በየቀኑ ከተማሪዎች ጋር ስለምውልና ስለማስተምር ደስተኛ ነኝ። በሕይወቴ ክፉ ገጠመኝ ወይም ያዘንኩበት የምለው ተማሪ ቤት ሆኜ የታመምኩበትን ጊዜ ነው። ቅኔ ቤት እያለሁ ቅኔ ልቀኝ ሥላሴ እንደደረስኩ በጣም ታመምኩ፤ ብዙ በሽታ ነበረብኝ፣ ራሴን ያዞረኝ ነበር። በዚያ ምክንያት በዐቢይ ጾም ጉባኤ አቋርጬ ጠበል ሄድኩ በረሃ ላይ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ጠበል ነበረ ዐቢይ ጾም እስከሚያልቅና እስከ ሆሣዕና ድረስ እዚያው ነበርኩ የእግዚአብሔር ምሕረት ቅርብ ነውና ተጠምቄ ዳንኩ። የሚገርመው ወደ ጸበል ስሄድ እግዚአብሔርን በጸሎት‹‹ ይህን ጠላት ያመጣብኝን ፈተና ከላዬ አንሣልኝ፣ አምላክነትህና አዳኝነትህን ልመስክር ልመሰክር›› ብዬ ተስዬ ነበር። ጸበሉ ዋሻ ነው እዚያ ሰው የለኝም ብቻዬን ነበርኩ እዚያ ሆኜ ዳዊት እደግም እጸልይ ነበር። ቅድም እንዳልኩት ቅኔ ቤት ሥላሴ (የቅኔ ክፍል) ላይ አቋርጬ ነበር የሄድኩትና መምህሬ ሙቶ ነው ብለው  እንዲፈልጉኝ ተማሪዎችን በየቦታው ልከው ነበረ። ስመለስ ‹‹የት ቆይተህ ነው?›› አሉኝ ‹‹ፀበል ነበርኩ›› አልኳቸው በዚያው ትምህርቴን ቀጠልኩ በሕማማት መጥቼ ጀምሬ አንድ ሁለት ወር እንደተማርኩ ሰኔ አካባቢ ቅኔ አስቀኙኝ ይሄ እንግዲህ የእግዚአብሔርን አምላክነቱን፣ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ያየሁበት ከባዱን ፈተና ያለፍኩበት ነውና አምላኬን እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ። ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለን? ሊቀ ጠበብት፦  እኔም በእግዚአብሔር ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
Read 864 times