Wednesday, 10 March 2021 00:00

‹‹የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ነው ያኖረኝ›› መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ ብሩ ክፍል ሁለት

Written by  መጽሐፈ ሲራክ
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። ናዝሬት ቅድስት ማርያም በመጽሐፍ መምህርነት ተመድቤ ብሔድም የስብከተ ወንጌል ኃላፊነቱንም ደርበው ስለሰጡኝ ሁለቱም የሥራ መደብ ላይ አገለግል ነበር። ሠርክ ጉባኤ ከእሑድ እስከ እሑድ አስተምር ነበር፤ ከጉባኤው በኋላ ማታ ማታ ልጆች ሰብስቤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ሥርዓተ ቅዳሴ አስተምራለሁ፤ በእርግጥ ብዙ ዲያቆናትም ወጥተዋል። እዚያ ካስማርሁዋቸው ውስጥ ውጪም ሄደው የሚያገለግሉ አሉ። ያኔ ብዙውን ሥራ ካለ አንድ ረዳት የምሠራው እኔ ነበርኩ። መምህር ዘላለም ወንድሙ ከወር አንድ ቀን ቅዳሜ ወይም እሑድ እየመጣ በስብከተ ወንጌል ትምህርት ያግዘኝ ነበር እንጂ ሌላ የሚያግዘኝ ሰው አልነበረም። በዚያ የሥራ ብዛት ዕረፍት ስላልነበረኝ ሰውነቴ እጅግ ተጎድቶ ነበር። ለአራት አመታት በዚያ ካገለገልኩ በኋላ በ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ዝውውር ጠይቄ በመጽሐፍ መምህርነት ወደ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል መጣሁ። እንግዲህ ከ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እዚህ ነው ያለሁት።    ስምዐ ጽድቅ፦ አሁን እዚህ ከመጡ በኋላ በመጽሐፍ መምህርነት ቀጠሉ ማለት ነው? የምን ያህል ተማሪዎች አሉዎት? አባ አእምሮ ፦ ወደ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ተዛውሬ ስመጣ በመጽሐፍ መምህርነት ቢሆንም  ብዙ ተማሪ ግን አልነበረም። እንደመጣሁ አካባቢ  መጽሐፍ መምህርነት ጀምሬ ነበረ ፤አንድ አራት ልጆች መጥተው መማር እንደጀመሩ የሚበላ የለም፣ የማስተማሪያ  ቤት የለም ማንም ዞር ብሎ የሚያያቸውና የሚረዳቸው በማጣታቸው ተማሪዎቹ ጥለውት ሄዱ። እነዚህን ልጆች  ቤተ ክርስቲያን መጠለያ እንኳ ብትሰጣቸው ለምግባቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ ደግ ነው ለምነው ይማሩ ነበር፤ ሆኖም የሚያስተባብር በመጥፋቱ ትምህርቱን አቋርጠው ጥለውት ሄደዋል። ከዚያ ወዲህ ምንም ተማሪ የለም። የመጽሐፍ መምህርነቱ በዚህ ምክንያት ከመቆሙ ውጪ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለይ በስብከተ ወንጌል ሳገለግል ነው የቆየሁት አሁንም እያገለገልኩ ነው። ሌላው ወደ ደብረ መዊዕ እንደመጣሁ በቦታው ላይ ፊደል የሚያስቆጥር መምህር አልነበረም፤ እኔም ዝም ብዬ ከምቀመጥ ለምን ልጆችን ፊደል አላስቆጥርም? ብዬ በራሴ ፍላጎት እና መነሣሣት ማስማስተማር ስጀምር ብዙ የአካባቢው ልጆች መጡ። ግእዙን፣ ውዳሴ ማርያሙን፣ ንባቡን፣ ዳዊቱን ሁሉ አስተምራለሁ። ማታ ማታ መጠለያው እና አዳራሹን ሞልተው ነው ሕፃናቱ የሚማሩት። አሁን ዓለማዊው ትምህርት በፈረቃ ስለሚሰጥ ትምህርት በሌላቸው ቀን እየመጡ ጥዋት እስከ ስድስት ሰዓት እና ማታ  ከአስራ ሁለት ሰዓት  እስከ አንድ ሰዓት ይማራሉ፤ ሆኖም ብቻዬን ነው የማስተምራቸው አጋዥም የለኝም።   ከማስተምራቸው ውስጥ ከፊደል ጀምረው፣ ዳዊት ዘልቀው ውዳሴ ማርያም፣ መልካ መልኩን ሁሉ የጨረሱ አሉ። መጀመሪያ መልእክተ ዮሐንስን ግእዝና ወርድ ንባቡን አስነብባቸዋለሁ እሱን ካነበቡ በኋላ ወንጌለ ዮሐንስን ቀጥሎ ዳዊትን አስነብባቸዋለሁ። ከዚህ በፊት ግን በስመ አብ ብለው ጀምረው ውዳሴ ማርያም አንቀጸ ብርሃን፣ መልካ መልኮቹን እነዚህን ጨርሰው ነው ወደ ምንባብ የማመጣቸው። ሂደቱ እንደዚህ ነው በዚህ መካከል ይህን ሁሉ ጨርሰው ዳዊት የሚማሩ ጎበዝ ሴቶች ልጆች አሉ፤ ዳዊቱን ጨርሰውም አጠናቀው የሄዱ አሉ። አሁንም በጣም ጎበዝ የሆኑ ሴቶች ልጆች አሉ። የወንጌሉን ንባብ ጨርሰው ወደ ዳዊት የሚገቡ ማለት ነው። ወንጌል ከጨረሱ በኋላ ዜማ የሚፈልግ ካለ ወደ ዜማ ቤት፣ ቅዳሴ የሚፈልግ ወደ ቅዳሴ ቤት ይሄዳሉ። ቅዳሴ ቤት የገቡ ብዙዎች ናቸው ቅዳሴውን ጨርሰው አሁን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ብዙ ልጆች ናቸው። እስከዛሬ እየተማሩ የሄዱ በቁጥር ይህን ያህል ናቸው ብዬ መናገር ባልችልም ብዙ ዲያቆናት እየተማሩ ዲቁና እየተቀበሉ ሄደዋል። እዚህም በተራ እየገቡ የሚቀድሱ ዲያቆናት ብዙ ናቸው። ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም ንባብ የሚማሩ አሁንም ሞልተዋል።  ስምዐ ጽድቅ ፦ እርስዎ ያፈሩዋቸው ተማሪዎች ምን ያህል አሉ ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያናችን የተለያዩ መዋቅሮች ላይ ካሉ ቢነግሩን? አባ አእምሮ፦ በእርግጥ ካስተማርኩዋቸው ተማሪዎች እልቅና ላይ የደረሰ ሰው የለም፤ ናዝሬት እያለሁ ካስተማርኩዋቸው ውስጥ አሁን በቤተ ክርስቲያን በአገልግሎት ላይ የሚገኙ አሉ። ቅድም እንደነገርኩሽ እዚህ ከመጣሁም መጽሐፍ የሚማር ተማሪ ባለመኖሩ ንባቡን ዳዊቱን ይህንን መልካ መልኩን እሱን እሱን ነው የማስተምር እነዚህ ብዙ ናቸው። በደሞዝም የተቀጠሩ በአብዛኛው በዲቁናና በቅስና አገልግሎት ላይ ነው ያሉት። ስምዐ ጽድቅ፦ በዚሁ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በስብከተ ወንጌል፣ የኮሌጅ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ የተለያዩ ማኅበራትን እና ምእመናን ያስተምሩ እንደነበር ይነገራል እስኪ ስለዚያ ይንገሩኝ? አባ አእምሮ፦ እውነት ነው በስብከተ ወንጌል፣ በአካባቢው ላይ ያሉ የኮሌጅ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችንና የተለያዩ ማኅበራትን ሰብስቤ ስብአስተምራለሁ። ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብስቧቸው በዚህ ግቢ የሚማሩ የቅዱስ ጳውሎስ የጤና ተማሪዎች ነበሩ። ከነዚህ ተማሪዎች ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ በጣም ነው የሚስደስተኝ። ጉባኤውን በጸሎት ማስጀመርና ሲያልቅ በጸሎት በመዝጋት እንዲሁም መምህር በሚቀርበት ጊዜ ሸፍኜ በማስተማር ማኅበሩን አግዝ ነበር። ታላላቆቹ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ለማስተማር ይመጡ ነበር።  በየዓመቱ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ እናስመርቃቸው ነበር ፊት የመጣው ይመረቃል ከኋላ የመጣው ደግሞ ይቀጥላል። በኋላ ላይም የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ተከፍቶ ስለነበር እነሱንም በዚሁ ግቢ ውስጥ ሰብስቤ ስብከተ ወንጌል አስተምር ነበር።  ብዙ ተማሪዎች ከዚህ ቦታ መንፈሳዊ ትምህርት ቀስመው ሄደዋል። ያን ጊዜ አዳራሹ ስለሚጠበን ውጭ ላይ ድምጽ ማጉያ በመጠቀም ነበር የምናስተምራቸው። ይህ ጉባኤ እስካሁን ድረስ አለ እሱን ጉባኤ እኔው ነኝ የምከታተለው።  ከነዚህ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በተጨማሪ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ ማኅበረ አዳም ወሔዋን የሚባሉ አራት ማኅበራትን በዚሁ ግቢ ውስጥ ሰብስቤ ስብከተ ወንጌል የማስተምራቸው እኔ ነበርኩ። እነዚህ ማኅበራት ከጉራጌ ማኅበረሰብ የመጡ ነበሩ፤ ከሚማሩት መንፈሳዊ ትምህርት ባሻገር የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳድሳሉ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳንጻሉ። ገጠሩ ላይ ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው ምእመናን አስከሬን የሚቀብሩበት አጥተው ቤተ ክርስቲያን እና መቃብር ፍለጋ የስድስት ሰዓት መንገድ የሚጓዙበት ጊዜም ነበረ፤ እነዚህ ማኅበራት እንዲህ ዓይነት ችግር ባሉባቸው ቦታዎች በመሄድ አብያተ ክርስቲያናትን በቅርባቸው አሳንጸውላቸዋል። ይህን ሁሉ ያደረጉት እዚህ መጥተው ወንጌል በመማራቸው ነው። የእነርሱ ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን ወደዚህ ካቴድራል በመምጣት እና ፈቃድ በመውሰድ በአካባቢው ላሉ የመንግስት ሰራተኞች መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጥ ነበር። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ የፓስተር ኢንስቲዩት፣ የጤና ጣቢያ፣ የመድኃኒት ፋብሪካ፣ የመናኸሪያ ሰራተኞችን ዓርብ ዓርብ አስተምር ነበር። ለነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ደብዳቤ ሰጥቶኝ ነው እያገለገልኩ ያለሁት። ብዙ ሰራተኞች እየመጡ ይማሩ ነበር፤ አዳራሹ እየሞላ ውጭ ቆመው የሚማሩ ነበሩ።  ስምዐ ጽድቅ፦ አሁን ጉባኤው እንዴት እየሄደ ነው? አባ አእምሮ፦  አሁን እንኳ በኮረና ምክንያት አገልግሎቱ ቆሞ ነበር በዚህ ሰሞን ጀምረናል አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው። እዚህ ጤና ጣቢያው ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ልጆች አሉ እነሱ ሌሎች ሰራተኞችን  እየቀሰቀሱ ጉባኤው እንደበፊቱ ተጀምሯል።  ስምዐ ጽድቅ፦ እንደ እርስዎ ያሉ መምህራን እንዲበዙ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት ይላሉ? አባ አእምሮ፦  ቤተ ክርስቲያን ተተኪ መምህር እንዲበዛ ተግታ መሥራት አለባት እላለሁ፤ አሁን ግን ያ እየሆነ አይደለም። ይልቁንም ማኅበረ ቅዱሳን ገጠሩ ድረስ ዘልቆ እየሠራ ነው። ቤተ ክህነት፤ ባለ ሀብት የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ መንግሥት  ለዚህ ስራ በኅብረት ቢሰለፉ ጥሩ ነው እላለሁ። በተለይ ቤተ ክህነት አጥብቆ ሊያስብበት ይገባል። የአብነት መምህራኑ የታሉ ተብለው ተፈልገው ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል። ያኔ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተተኪ ትውልድን ያፈራሉ። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ይተባበር ነው የምለው። ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ።  እኔም እኮ አሁን ቁጭ ብዬ የማስተምረው ዳቦ ስላገኘሁ ነው። እኛ ስንማር  ደረቅ ባቄላ፣ ለምለም እንጀራ በልተን ነው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እዚህ የደረስነው። የአብነት መምህራኑን እንደዚህ የሚያስቀጥል ሁኔታ አይደለም ዛሬ ያለው። ለዚህ ነው የአብነት መምህራኑ በደንብ ሊያዙ ይገባል የምለው።  አሁን ማኅበሩ ብቻ ነው እየሠራ ያለው ለምሳሌ ጎንደር መንበረ መንግሥት አራቱ ጉባኤ ቤት ማለት ነው ተማሪው በጀት ወጥቶለት ሰርከ ኅብስት ተሰጥቶት ያው ያቺን እየበላ እየተማረ ነው። እንደ አገባባቸው የጊዜ ገደብም ተሰጥቶአቸው የተማረው ቦታ እየለቀቀ ያልተማረው እየገባ ነው ያለው፤ እንዲህ ቢሆን ብዙ ነገር ይሠራል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ዕድል አንድና ሁለት ቦታ ነው ያለው ሌላ ቦታ የለም። እንዲህም ሆኖ በገጠሩ ዓለም የእግዚአብሔር ሥራ ይገርማል። በደመወዝ ሳይሆን በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቀው የሚያስተምሩ አባቶች ሞልተዋል። ስምዐ ጽድቅ፦ ትምህርት ቤት እያሉ የመገልበጥ ሥራ ከሠሩባቸው  መጻሕፍት ውጪ የጻፏቸው መጻሕፍት አሉ? አባ አእምሮ፦ በዓይኔ ምክንያት መጽሐፍ ማዘጋጀት አልቻልኩም። እንኳን መጽሐፍ ልጽፍ የማነበውን እንኳ እየተቸገርኩ ነው ያለሁት። በጣም የሚገርመው እስከ እድሜ ልኬ ትምህርት አቆማለሁ የሚል እምነት አልነበረኝም። መሀከል ላይ ዓይኔ ታመመ አሁን አምስት ደቂቃ ሳነብ እንባዬ ነው የሚፈሰው። ተመርምሬው ነበር ዶክተሩ ዓይህ ስለተጎዳ ጥበቃ አድርግለት በማለት አሳስቦኛል። እንግዲህ በዓይኔ ምክንያት ምንም ነገር መሥራት አልቻልኩም ማለት ነው። በልጅነቴ ዓይኔ በመጎዳቱ አሁን ላይ ምንም መስራት አልቻልኩም። እንደውም ትምህርት ለመማር በጣም ተነሳስቼ ነበር ነገር ግን ዓይኔን እንዴት ላድርገው አልቻልኩም ትምህርቱን አቆምኩኝ።  ስምዐ ጽድቅ፦ በአገልግሎት ዘመንዎ ደስ የሚልዎት ወይም ያዘኑበት አጋጣሚ ካለ ገጠመኝዎትን ይግለጹልን? አባ አእምሮ፦ በሕይወት ዘመን ጥሩም መጥፎም ነገር ይገጥማል። እኔ በሕይወቴ የተደሰትኩበት አጋጣሚ እስቴ መካነ ኢየሱስ እያለሁ አራቱን ወንጌላውያን ትርጓሜ በእጄ መገልበጤ ነው። ቀለም በጥብጬ ብዕር ቀርጬ ደብተር አስምሬ በመጻፌ ትዝ የሚለኝና የሚያስደስተኝ ትልቁ ሥራ እሱ ነው። ሌላው እዚህ ደብረ መዊዕ ከመጣሁ በኋላ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማስተማር ያሣለፍኩት ጊዜ ነው የሚያስደስተኝ፤ በእርግጥ አሁንም በዚሁ አገልግሎት ውስጥ ነው ያለሁት። ሌላው በሕይወት ዘመኔ ክፉ አጋጣሚ ነው ብዬ የማነሳው የአብነት ት/ቤት የገጠመኝን ነው። በአብነት ት/ቤት ብዙ ፈተናዎችን አልፌአለሁ ማጣት፣መራብ፣መታረዝ ስንቱ ይዘረዘራል? በተለይ እስቴ መካነ የሱስ ብዙ  አሳልፌያለሁ በእርግጥ ትልቅ እውቀት ይዤ ወጥቻለሁ እሱ ነው ትልቁ ትርፌ የምለው። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ያ ይመስለኛል ዛሬ ከሰው ፊት ያደረሰኝ። እንደዚያ የምንለብሰው፣ የምንበላው ሳይኖረን ቤተ ክርስቲያን እናገለግል ነበር።  ሰዓታት፣ ማኅሌት እንቆም ነበር በፈቃዳችን ነው እንጂ ምንም አይከፈለንም። ከዚያ ህይወት የሚያስደስተው ያን ጊዜ የተሰጠን ጥንካሬና ብርታት ብቻ ነው። እንዴት ነው ሰው ምግብ ሳይበላ ውሃ ሳይጠጣ ቃለ እግዚአብሔርን እያገለገለ መኖር የሚችለው? ይህ የመላእክት ሥራ ነው እያልኩ አሁን ሳስበው ይገርመኛል።  ትምህርት ቤት ሳለን አንዲት ቁምጣና አንሶላ ነበረ ልብሳችን ሌላ የለም፤ ያችኑ ቀን ለብሰን እንውላለን ሌሊት ለብሰናት እናድራለን። ይህችው ቁምጣ ከመቀመጫዬ ላይ አለቀችብኝ ምን ላድርግ? ገንዘብ የለኝ አልገዛ፤ በቅርብ ዘመድ የለኝ አልብሱኝ አልል። አስታውሳለሁ አንድ ቀን ወደ ማታ ላይ ቁራሽ ልመና ወደ መንደር ስሄድ ከአንዱ ቤት ጓሮ ወይም ኮሲ ላይ ትልቅ ቡትቶ ተጥሏል ከዚያ ላይ ትልቅ ካኪ ተጥፎበት አየሁኝ። ያንን ቡትቶ ሰው እንዳያየኝ ይዤው ጫካ ገባሁና ካኪውን ከውስጡ አውጥቼ ከወንዝ ወስጄ በማጠብ ያንን ጥፌ የተወሰነ ጊዜ ተጠቀምኩበት። አሁን ሳስበው ይገርመኛል፤ እንባዬ ሁሉ ይመጣል። ‹‹ድህነት ከሰማይ ይርቃል የሚባለው ለካ እውነት ነው›› እላለሁ። ወይ እግዚአብሔር! ደሀውን ሀብታም፤ሀብታሙን ደሀ የምታደርገው ብዬ የነቢዩ ዳዊትን መዝሙር እያስታወስኩ አመሰግነዋለሁ። እንግዲህ ከዚያ ተነስቼ ነው ወደ ጎንደር ፤ከጎንደር ወደ ናዝሬት፤ ከናዝሬት እዚህ የደረስኩት። እዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ እንደሚታወቀው ነው ባልታሰበው ነገር ይመጣል ልብሱ፣ ጋቢው፣ ካባው ወደ ፲፩ ካባ ነው ለሰው የሰጠሁት። ይሄ ራሱ ታሪክ ነው። ለወደፊት የሚመጣውን አላውቅም እግዚአብሔር እስከዚህ ድረስ አድርሶኛል። ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለን? አባ አእምሮ፦ እኔም ፈልጋችሁ መጥታችሁ ካለኝ ጥቂት እንዳካፍል እንግዳ ስላደረጋችሁኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
Read 673 times