Wednesday, 24 March 2021 00:00

ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ከ፲፱፻፳፩ - ፲፱፻፹፩ ዓ.ም

Written by  መጽሐፈ ሲራክ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የብዙ ሊቃውንት አባቶች መፍለቂያ ምንጭ ናት። ሰማዕታትን፣ ደናግላኑን ሐዋርያትን፣ ጳጳሳትን፣ መነኮሳትን፣ ያፈራች የቅዱሳን እናት ናት። ብዙዎቹ በተሰጣቸው ዘመን ወደዚህ ዓለም መጥተው በቅድስና በንጽሕና ኖረው፣ አስተምረው፣ጸልየው፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለቤተ ክርስቲያን ክብር ቆመው እና አገልግለው በስተመጨረሻም ዘመን ገቷቸው አንቀላፍተዋል።  በዘመናቸው ተነስተው እንደ ተወርዋሪ ኮከብ አብርተው፣ መልካም ገድልን በመጋደል እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሩጫቸውን ጨርሰው በገነት ወደ ቅዱሳን ማኅበር ከተቀላቀሉት መሀከል  ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ አንዱ ናቸው። እኛም የብፁዕነታቸውን የሕይወት ታሪክ፣ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን ባጠቃላይ እስካረፉበት መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ያለውን ዜና ሕይወታቸውን በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል መልካም ንባብ፦  ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በቀድሞ ስማቸው አባ ጸጋዬ ቢሆነኝ በዚያን ጊዜ አጠራር በደቡብ ጎንደር አስተዳደር በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆማ ፋሲለደስ  ተብሎ በሚታወቀው ታላቅ ገዳም ከአባታቸው ከቀኝ ጌታ ቢሆነኝ ዋሴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ውዴ መሸሻ በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ተወለዱ።  ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በመካነ ልደታቸው በቆማ ፋሲለደስ ፊደል፤ ዳዊትና ጸዋትወ ዜማ ከታወቁት ከታላቁ የቆሜ ድጓ ምሥክር ከነበሩት ከመምህር ሐዲስ ተምረዋል። በጥር ፲፱፻፴፭ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም ከግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ ማዕረገ ዲቁናን ተቀበሉ።   ብፁዕነታቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ፈለግ በመከተል መንፈሳዊ ዕውቀታቸውን ለማስፋፋት በነበራቸው ጽኑዕ ፍላጎት ከትውልድ ቦታቸው ወጥተው በልዩ ልዩ ክፍላተ ሀገራት በመዘዋወር ከአያሌ ኢትዮጵያውያን መምህራን የቤተ ክርስቲያችንን ከፍተኛ ትምህርት በመቅሰም መንፈሳዊ ዕውቀትን ገብይተዋል። በዚሁ መሠረት ከደቡብ ጎንደር ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሄደው በሞጣ አውራጃ ድቦ ኪዳነ ምሕረት ቅኔ እስከነአገባቡ ተምረዋል። ወደ ደቡብ ጎንደር በመመለስም በጋይንት አውራጃ በስማዳ ወረዳ ደብረ ዕንቍ ከመምህር ጌጡ ተሰማ ተጨማሪ የቅኔ ትምህርታቸውን  አስፋፍተዋል። ቀጥሎም ወደ ደቡብ ወሎ በመሄድ በአማራ ሳይንት ወረዳ፤ በሮ ሚካኤል ከነበሩት ከአለቃ ከበደ የቅኔ ትምህርትን ከነአገባቡ በመማር አጠናቀው በመምህርነት ተመርቀዋል። በመጻሕፍት ትርጓሜ ረገድም በዚያው በቦረና ሣይንት አውራጃ በመካነ ሰላም ከአለቃ ታመነ አግደው ትርጓሜ ነገሥትን፣ በደሴ አውራጃ በደሴ መድኃኔ ዓለም ከአባ ገብረ ማርያም ገብረ ሐና ዳዊትን፣ የውዳሴና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜን ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ የትምህርተ ኅቡአት ፣ የኪዳንና የፍትሐ ነገሥት ትርጓሜን ተምረዋል። ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በደቡብ ወሎ በትምህርት ላይ ነበሩበት ጊዜም በ፲፱፻፵ ዓ.ም በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ሕገ ምንኩስናን ተቀብለዋል። መስከረም ፳፩ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ.ም በግሼን ማርያም ማዕረገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል የጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በታዕካ ነገሥት በዓታ መታሰቢያ ቤት የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርታቸውን ቀጥለው ሐዲሳትን ከመምህር ገብረ ሕይወትና ከመምህር ሥምረተ አብ ቀጸላ፣ ብሉያትን ከመምህር ጌራ፣ አቡሻህርን ደግሞ ከመምህር ገብረ ሕይወትና ከመምህር ኪዳነ ማርያም ተምረው ተመርቀዋል። ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ከፍ ብሎ በዝርዝር እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ባህል እውነተኛ ምንጮች ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መምህራን ነገረ መለኮትን አጥንተው ካስመሰከሩ በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል።    ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በተለያዩ ሊቃውንት የቤተ ክርስተያንን ዕውቀት ከቀሰሙ በኋላ በ፲፱፻፶፮ ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ በሐዲሳት ትርጓሜ መምህርነት ተመድበው እስከ ፲፱፻፸፩ ዓ.ም ድረስ ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ በማስተማር ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የካቴድራሉ ቄሰ ገበዝ በመሆን መንፈሳዊ ፍቅርን በተሞላ ሰብእና ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል።  በተጨማሪም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ተመድበው ብዙ ወጣቶችን አፍርተዋል። ቀደም ሲል ማኅበረ እስጢፋኖስ ሲባል የነበረው የካህናት ማኅበር እንዲሁም ማኅበረ ሥላሴ እየተባለ ይጠራ በነበረው የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር ዘወትር ቅዳሜና እሑድ በመገኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ነገረ መለኮትን በማስተማር ከፍ ያለ አገልግሎት ሰጥተዋል። በተለይም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በሚያደርጉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሁሉ በመሳተፍ በማኅበሩ ውስጥ እየተመረጡና እያስተማሩ ለማኅበሩ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አበርክተዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በነበራት ሰፊ እንቅስቃሴ  ቤተ ክርስቲያንዋ ለምትጠብቀው አገልግሎት አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲመረጡ በተወሰነው መሠረት ጥር ፭ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ.ም ከተመረጡት ፲፫ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ አንዱ ሆነው በመመረጥ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ማዕረገ ጵጵስናን ተቀብለዋል። ማዕረገ ጵጵስናን እንደተቀበሉ በቀድሞው  የኤሊባቦር ክፍለ ሀገር ኤጲስ ቆጶስ ሆነው በመሾም በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ መንፈሳዊ ተግባራትን አከናውነዋል። ከነዚህ መንፈሳዊ ተግባራት መካከልም ፦ በዚሁ በተመደቡበት ኤሊባቦር ልዩ ስሙ ዳበና በተባለው ሥፍራ ፻፳ ኪሎ ሜትር መንገድ በእግራቸው በመጓዝ እና በማስተማር ለካህናት ማሰልጠኛ መጠናከር አስተዋጽኦ አድርገዋል።  ብፁዕነታቸው በዚሁ ሀገረ ስብከት በነበራቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ሰበካ ጉባኤ አደራጅተዋል፣ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን አቋቁመዋል፣ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት በማቋቋም እናት እና አባት ለሌላቸው ልጆች ምግብ፣ መጠለያ እና ትምህርት እንዲያገኙ አድርገዋል። የመቱ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ለሀገረ ስብከቱ በሚመጥን መልኩ በካቴድራል ደረጃ ከፍ አድርገው አሠርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሰንበት ትምህርት ቤትን በማቋቋምና በማደራጀት ብዙ ወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆነው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ አድርገዋል።  ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በጥር ወር ፲፱፻፸፮ ዓ.ም የኤርትራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ተዛውረው ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። በተለይም ለቤተ ክርስቲያን እድገትና የካህናትን ኑሮ ለማሻሻል በወጣው ቃለ አዋዲ መሠረት  ለምእመናን ጥቅሙን በማስረዳትና የነበረውን ችግር በማስወገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበካ ጉባኤ አስጀምረዋል።  ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከቱ የካህናት በጀት እንዲከፈት በማድረግ በየወረዳው ሊቃነ ካህናትን መድበዋል። በተጨማሪም ለካህናትና ለመምህራን ለቢሮ ሠራተኞች ደሞዝ እንዲሻሻል በከፍተኛ ጥረት አዲስ በጀት አስከፍተዋል። የአስመራ አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበርም በሰበካ ጉባኤ ገቢ ላይ ገንዘብ እንዲዋጣና ከሀገረ ስብከቱም ወጭ በማድረግ ለሠልጣኝ ካህናት ለትራንስፖርትና ለመምህራን አበል በመክፈል ራስ አገዝ የካህናት ማሠልጠኛ ከፍተው ካህናቱ በየሦስት ወሩ እንዲሠለጥኑ አድርገዋል። በሀገረ ስብከቱ ብዙ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፣ብዙ ዘመን የቆዩትም በአዲስ መልኩ እንዲሠሩ አድርገዋል። ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት እስከተዛወሩበት የጥቅምት ወር ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን በኤርትራ ክፍለ ሀገር በድርቅና በሰላም መታጣት ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች የምታከናውነውን የርዳታ ሥራ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ቆይተዋል። በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት  የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  ሆነው እንዲሠሩ ተመድበው በሀገረ ስብከቱ ሥራ በጀመሩ በአራት ወራት ውስጥ ብዙ የትሩፋት ሥራዎችን አከናውነዋል። በጎንደር ከተማ አዘዞ ሚካኤል የሚገኘውን የካህናት ማሠልጠኛ በቦታው ድረስ እየተገኙ በማስተማር ከማበረታታቸውም በላይ ማሠልጠኛውን በገንዘብ ይደግፉ ነበር። የጉባኤ ቤቶች ተጠናክረው እንዲስፋፉ በነበራቸው ጽኑዕ ዓላማ መሠረት በጎንደር ከተማ ውስጥ ለተለያዩ ጉባኤ ቤቶች ከግል ገንዘባቸው ልግስና አድርገዋል። ለድሆች፣ ለጦም አዳሪዎች ከግል ገንዘባቸው ችሮታ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በየአውራጃው እየተዘዋወሩ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠገኑ ሐሳብና መመሪያ ሰጥተዋል። በተለይም የቆማ ፋሲለደስ ገዳም  እንዲታደስና ቆርቆሮ እንዲለብስ አስፈላጊውን ገንዘብና ቁሳቁስ እንዲያገኝ ከፍተኛ የማስተባበር ተግባር ፈጽመዋል።  በጎንደር ደብረ ታቦርና በወረታ ያሉትን የሕፃናት ማሳደጊያዎች ተዘዋውረው በመጎብኘት ለሕፃናት ትምህርትና ምክር በመስጠት የሕፃናት ማሳደጊያዎቹም የበለጠ እንዲስፋፉ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በደብረ ታቦር የሚገኙትን የችግኝ ጣቢያዎች ተዘዋውረው በመጎብኘት ብዙ የድጋፍ ሥራን ሠርተዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝናብ እጥረት ችግር የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት በሌቦ አውራጃ በአዲስ ዘመን እና በእብናት ያቋቋመቻቸውን ሦስት የርዳታ ጣቢያዎች በመጎብኘት እና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴውን በመከታተል ለተጎጂ ወገኖች ርዳታ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል። ብፁዕነታቸው በሕይወተ ሥጋ በነበሩባቸው ዓመታት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነት ሲያገለግሉ የቆዩ ፤ለብዙዎች አርአያ የሆኑ መንፈሳዊ አባት ነበሩ። ሀብተ ክህነት፣ሀብተ ትሕትና፣ ሀብተ ጾም፣ ሀብተ ጸሎት፣ ሀብተ ፍቅር እንዳላቸው በብዙዎች ዘንድ የሚነገርላቸው ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ባደረባቸው ሕመመም ምክንያት በተወለዱ በ፷፩ ዓመታቸው መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሥጋ አርፈዋል። ብፁዕነታቸው ከዚህ ዓለም በሥጋ ቢለዩም በመንፈስ ሕያው ሆነው ይኖራሉ።                                   በረከታቸው ይደርብን 
Read 735 times