Wednesday, 28 April 2021 00:00

አለቃ ኅሩይ ተ/ሃይማኖት ከ፲፰፻፺፯ - ፲፱፻፸፮ ዓ.ም

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አዕማድ ሆነው ሲያገለግሏት የኖሩ እና የሚኖሩ የብዙ ሊቃውንት መምህራን ባለቤት ናት። እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በልጅነት ሕይወታቸው ከቤተሰቦቻቸው እና ከቀዬአቸው ርቀው በመሄድ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመማር ብዙ ዋጋ ከፍለው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወታቸው ከራሳቸው አልፈው ወንበር በመዘርጋት ብዙዎችን የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማፍራት አገልግሎቱ እንዲቀጥል ወርቃማ አሻራቸውን ያሳረፉ ብዙዎች ናቸው። በነበራቸው የአገልግሎት ዘመናት ሁሉ ደሞዝ ሳይቆረጥላቸው፣ ቀለብ ሳይሰፈርላቸው  ቤተ ክርስቲያንን በትሩፋት ሲያገለግሉ ኖረዋል።  በተሰጣቸው የዕድሜ ዘመን ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት አስጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር ሊቃውንቶቻችን ዘመን የማይሽረው ሥራ ሲሰሩ ኖረዋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት፣ በሥነ ምግባር፣ በትውፊቱ ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል፤ ዘመን አመጣሹን ማዕበል ሁሉ ተቋቁማ እንድታልፍ ገና ከጥዋቱ ጠንካራ የሃይማኖት መሠረት ጥለዋል። ቤተ ክርስቲያን በመምህራን ለምልማ እንድትታይ የተጉ፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚረከብ ጠንካራ ትውልድ ሲቀርጹ የኖሩ ሊቃውንቶቻችን የአብነት ትምህርት ቤቱ ምሰሶ ሆነው አልፈዋል። ከእነዚህ የቤተ ክርስቲያን ብርቅዬ ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆኑትን አለቃ ኅሩይ ተ/ሃይማኖትን የሕይወት ታሪክ ለ‹‹ቤተ አብርሃም›› በሚሆን መንገድ አዘጋጅተነዋል ተከታተሉን።

 

አለቃ ኅሩይ ተ/ሃይማኖት ከእናታቸው ከወ/ሮ ሸዋረገድ ቢተውና  ከአባታቸው ከቄስ ተ/ሃይማኖት ሲሳይ በ፲፰፻፺፯ ዓ.ም በሸዋ  ክ/ሀገር  በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ አንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ተወለዱ። የልጅነት ሕይወታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ከብት በመጠበቅ ያሳለፉት አለቃ ኅሩይ በአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት በጊዜው የንባብ መምህር ከነበሩት ከመምህር አባ ወንድሙ ዘንድ በመሄድ የንባብ፣ የዳዊትና የግብረ ዲቁና ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ፲፱፻፰ ዓ.ም በ፲፩ ዓመታቸው ከአቡነ ማቴዎስ የዲቁና ማዕረግ ተቀብለዋል። 

ለመንፈሳዊ ትምህርት ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ በዚያ ሳይወሰኑ የተወለዱበትን መንደር ትተው በሸዋ ክ/ሀገር በሚገኘው የዜና ማርቆስ ገዳም በመሄድ ግብረ ትሕትና ከነበራቸው ከመምህር አባ ሀብተ ጊዮርጊስ ዘንድ የዜማ ትምህርት ጾመ ድጓን አጠናቀዋል። ከዚያም የቃለ እግዚአብሔር ትምህርት በሰፊው ወደ ሚናኝበት ጎንደር ክ/ሀገር በመሻገር በቤተልሔም ልዩ ስሙ ሾላ ጊዮርጊስ ከሚባል ደብር ከነበሩት ከመምህር ገብረ ሕይወት ዘንድ ጾመ ድጓ፣ ድጓና ምዕራፍ ተምረው አጠናቀው በቤተልሔም አስመስክረዋል። ከዚያም በጎንደር ክ/ሀገር ስማዳ ልዩ ስሙ አጅ ኪዳነ ምሕረት ከምትባል ቦታ ለአራት ዓመታት በመምህርነት ቆይተዋል።

አለቃ ኅሩይ ሐሳባቸው በአብነት ትምህርት ቤት የሚቀራቸውን መንፈሳዊ ትምህርት ጨርሶ መዝለቅ ነበርና መምህርነቱን በመተው እዚያው ስማዳ ልዩ ስሙ አርባዕቱ እንስሳ ከሚባል ቦታ ከታወቁት የቅኔ መምህር ምሥራቅ ዘንድ የቅኔ ትምህርታቸውን ተምረው ቅኔ እያስነገሩና እየዘረፉ ቆይተዋል። ከዚያም ወደ በለሳ በመሄድ ልዩ ስሟ አጣሌ ማርያም ከምትባል ቦታ ከታወቁት የአቋቋም መምህር መምህር ማስረሻ ዘንድ የአቋቋም ትምህርታቸውን በመማር አስመስክረዋል። ወደ ሰቆጣ መድኃኔ ዓለም ደብርም በመሄድ ከታወቁት የቅኔ መምህር ከመምህር ኤልሳዕ ዘንድ ተቀምጠው የተማሩትን በማጠናከር ለጥቂት ጊዜ ቆይተዋል።

ከሰቆጣ መድኃኔ ዓለም ወደ ሰሜን ቤተ አልቦ ሚካኤል በመሄድ ከመምህር አባ ኀይለ ጊዮርጊስ ዘንድ መዝገብ የቅዳሴና የዝማሬ የመዋሥዕት ተምረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከመምህር ቀለመወርቅ ዘንድ ዝማሬ መዋሥዕቱን አጠናቀው አስመስክረዋል። ከዚህ ቀጥለው ጎንደር መካነ ኢየሱስ በመሄድ መጻሕፍተ ብሉያትን በመማር አጠናቀዋል። በጠቅላላው በጎንደር ክፍለ ሀገር ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ ዝማሬ መዋሥዕት፣ መዝገብ ቅዳሴ፣ ቅኔና  መጻሕፍተ ብሉያትን በመማርና በማስተማር ለሃያ አምስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ሀገሪቱን ወርሮ የነበረው የጣሊያን ሠራዊት ሀገሪቱን ለቆ ሲወጣ በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ተማሪዎቻቸውን በማስከተል ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ክፍለ ሀገር ተመልሰው በማስተማሩ ወንበር ዘርግተው ሲያስተምሩ ቆይተዋል። 

በሕይወታቸው ሙሉ በቤተ ክርስቲያን ወንበር ዘርግተው ሲያስተምሩ የቆዩትና ከቤተ ክርስቲያን አንዲትም ቀን ያልተለዩት መምህር በዚያው ዘመን የሕግ ባለቤታቸውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አግብተው ስድስት ሴቶች እና አምስት ወንዶች ልጆችን አፍርተዋል። ጎንደር ክ/ሀገር በነበሩበት ጊዜና ወደ ሸዋ ክፍለ ሀገር ከተመለሱ በኋላ የጀመሩትን የጸዋትወ ዜማና የጸሎት መጻሕፍትን በብራና ላይ የመጻፍ ሥራን ጨርሰው ለተለያዩ አድባራት እና ገዳማት ለአገልግሎት ይውሉ ዘንድ አበርክተዋል። መጻሕፍቶቻቸው ከሚገኙባቸው ገዳማት ውስጥ አንዱ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አንዱ ነው። 

ወንበር ዘርግተው በርካታ ተማሪዎችን በማስተማር ሲተጉ የነበሩት ታላቁ መምህር አለቃ ኅሩይ ማዕረገ ቅስናን ከተቀበሉ በኋላ  በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ‹‹እንተ ይእቲ ጽርሐ አርያም አንጎለላ ኪዳነ ምሕረት መካነ ልደቱ ወጥምቀቱ ለዳግማዊ ሚኒልክ›› በሚል ስያሜ ለምትጠራው  ለአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ደብር አለቃ ሆነው ተሹመዋል። በዚያም በነበራቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ወንበር ዘርግተው ከሚያስተምሩት ተማሪ ጎን ለጎን የአጥቢያውን ካህናትና ምእመናን ልጅ አዋቂ ሳይሉ ግብረ ትሕትና በተሞላበት መንፈስ ሲመሩ ቆይተዋል።

አለቃ ኅሩይ ለአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ደብር ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ በመቃኞ ያለችውን የእመቤታችንን ታቦት ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንደትገባ ከነበራቸው መንፈሳዊ ቅንዓት የተነሣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ብዙ ደክመዋል፣ ወጥተው ወርደዋል። በአካባቢው ያሉትን ተወላጆች በማስተባበር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንዋን በማሠራት ጽላቷ ከመቃኞ ወጥታ ወደተሠራላት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንደትገባ አድርገዋል። አለቃ ኅሩይ እንደቀደሙት ደጋግ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የራሳቸውን ክብርና ዝና መናገር የማይፈልጉ መምህረ ትሕትና ናቸው። ለዚህ ማረጋገጫው በሕይወት በነበሩበት ወቅት የሕይወት ታሪካቸውን እንዲነግሩአቸው ሰዎች በጠየቁአቸው ጊዜ ‹‹ምን ታሪክ አለኝና ትጠይቁኛላችሁ በዚህ ዓለም ላይ ታሪክ ሠሪው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ይልቁንስ ሃይማኖታችሁን አጠንክራችሁ ጠብቁ›› በማለት እንደመለሱላቸው የሚያውቁአቸው ያነሳሉ።

አለቃ ኅሩይ በአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ደብር በአለቅነት ከዚያም በተጨማሪ ፊት የጀመሩትን ወንበር ዘርግተው የአብነት ትምህርቱን በማስተማር ብዙ ተማሪዎችን ያፈሩ ሲሆን በቦታው ለ፴፬ ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ ‹‹አዳም ሆይ መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ ›› ተብሎ እንደተነገረው በአደረባቸው ሕመም ምክንያት ታኅሣሥ ፴ ቀን ፲፱፸፮ ዓ.ም በተወለዱ በ፸፱ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። 

የአባታችንን ነፍስ ከደጋጎቹ ጎን ያኑርል!

 

Read 947 times