የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ሞት ሽፋን በማድርግ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጽንፈኛ ሙስሊሞች በፈጸሙት ጥቃት ሳቢያ ንብረታቸው በቃጠሎ ለወደመባቸውና ለተፈናቀሉ ምእመናን ማቋቋሚያ የሚውል የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ቤተክርስቲያን እንደምታደርግ ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ/ም በሰጠችው መግለጫ አስታወቀች፡፡
ቤተክርስቲያን የምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ለእያንዳንዱ ተጎጂ ምእመን ከቅዱስ ዮሐንስ በዓል በፊት የሚከፋፈል ሲሆን የተፈጸመውን ጥቃት እንዲያጣራ ኃላፊነት የተሰጠው ዐቢይ ኮሚቴም በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናንንና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ይኖሩበት በነበረበት አካባቢ በቋሚነት በማቋቋም የጽንፈኞቹን ኦርቶዶክሳውያንን የማፈናቀልና የማጥፋ ሴራ ለማክሸፍ እንደሚሰራ አስገንዝቧል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በምእመናንና በንብረታቸው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ እንዲሁም ምእመናንን መልሶ በማቋቋሙና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ዙሪያ ዐቢይ ኮሚቴው ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር እንደተወያዩ ታውቋል፡፡