Tuesday, 08 September 2020 00:00

ሃይማኖት ተኮር ግድያንና የዘር የማጥፋት ወንጀልን ለመከላከል ጥሪ ቀረበ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ካልፎርኒያ ነቫዳ አሪዞና ሀገረ ስበከት ጽ/ቤት የዘር-ጥፋት መከላከያ ተቋም (ኢተክዘተ) ሃይማኖት ተኮር ግድያና የዘር ማጠፋት ወንጀልን በጋራ እንከላከል ሲል ነሐሴ 21 ቀን 2012 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቀረበ፡፡ በሃይማኖት፣በዘርና በማንነት ላይ ያተኮረ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከል ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ድርጅቶች ጋር ማለትም (SAGE) በጋራ ለመሥራት እንደተስማማ  በመግለጫው ያስገነዘበው ተቋሙ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘር-ጥፋት መከላከያ ተቋምም (ኢተክዘተ) የሃይማኖት አባቶችን፣ ምሁራንን፣ ወጣቶችንና ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችን ያካተተ ሆኖ እንደተመሠርት ከመግለጫው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች፣ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትጵያውያን እንዲሁም ለዓለም ሰላምና እና መረጋጋት የሚጨነቁ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ሀገራቸውን ወክለው በተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች የሚሠሩ በሙሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ለቤተክርስቲያኗ ድጋፍና ርዳታ እንዲያደርጉ ተቋሙ በመግለጫው ጠይቋል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌና በጅማ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም የተደራጁ አክራሪ ኃይሎች በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በምእመናንና በአገልጋዮች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፍና ግድያ እንደፈጸሙ ተቋሙ በመግለጫው አስታውሷል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን በሚከተሉት ሃይማኖት ምክንያት ብቻ ለተፈጸመባቸው ግድያና ጭፍጨፍ ሕግና ሰላምን ለማስከበር በየአካባቢው የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ፓሊሶችና የፌደራል ፓሊስ ኃይሎች በወቅቱ ግድያውንና ጭፍጨፍውን ያልተከላከሉ እንደሆነ መግለጫው አመልክቶ  የተወሰኑ የፀጥታ ኃይሎችም ለአክራሪ ጽንፈኛ ብድኑ ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ እንድነበር አስታውቋል፡፡      በተፈጸመባቸው ጥቃት ምክንያት መኖሪያ ቤታቸውና ንብረታቸው የተቃጥለባቸው ምእመናን የዕለት ምግብና መጠጊያ በማጣታቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕዝበ ክርስቲያኖች በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተጠልለው በመገኘታቸው ለከፍተኛ ርኅብና ሥነ ልቡናዊ ችግር በመጋለጣቸው አስቸኳይ የሥነ ልቡና፣የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደርገላቸው ተቋሙ በመግለጫው አሳስቧል፡፡  
Read 704 times