Thursday, 10 September 2020 00:00

‹‹ሁሉም ወገን ለሰላም መስፈን ዝግጁ እንዲሆን ቅዱሰ ፓትርያርኩ አሳሰቡ››

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
  ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አዲስ ዓመትን አስመልክተው መስከረም 1 ቀን !)03 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ያለፈው !)02 ዓ.ም በሀገሪቱ ብዙ ምስቅልቅል የተከሰተበት እንደነበር ተናገሩ፡፡  ባለፈው ዓመት አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ምእመናን ሲገደሉና ሲሰደዱ፤ ሃብትና ንብረታቸው ሲዘረፍ፣ ዜጎች በተለያየ ሁኔታ አካላዊ፤ ሥነ ልቡናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሲደርስባቸው እንዲሁም በሀገራቸው ባይተዋር ሆነው በጭንቀትና በሥጋት ሲኖሩ እንደነበር ቅዱስ ፓትርያርኩ በመግለጫው አስታውሰዋል፡፡  በምእመናን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በሙሉ በሌሎች ባዕዳን አካላት የተፈጸሙ ሳይሆኑ በኢትዮጵያውያን የተፈጸሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች በመሆናቸው እጅግ የሚያሳፍር ተግባር መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጠው  ‹‹ምእመናን በተፈጸመባቸው ጥቃት የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ያጋጠማቸው በመሆኑ ምእመናኑን መልሶ ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ጥረት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያላችሁ ምእመናን የተለመደ ድጋፋችሁን አድርጉ›› ብለዋል፡፡  ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተከሰቱ ምስቅልቅሎች በአዲሱ ዓመት እንዳይደገሙ በመወሰን ወደሥራ መግባት እንደሚገባ ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳስበው አዲሱ ዓመት አብያተ ክርስቲያናት የማይቃጠሉበት፣ ዜጎች በወገኖቻቸው የማይገደሉበት፣ የማይፈናቀሉበትና የማይሰጉበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡  በመጨረሻም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግጭት መፍጠር የተሸናፊነት ምልክት እንጂ የአሸናፊነት ፍኖት አለመሆኑን በመረዳት ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ትልቅ ድል እንደሚያስገኝ ቅዱስ ፓትርያርኩ አስገንዝበው በአዲሱ ዓመት ሁሉም ወገን ለሰላም መስፈን ዝግጁ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡   
Read 803 times