Wednesday, 16 September 2020 00:00

በኢትዮጵያ በኦርቶዶክሳውያን ላይ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ላይ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች በአክራሪ እስላሞች በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ዓለም አቀፉ ማሕበርሰብ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡  ባለፉት በረካታ ዓመታት በኦሮምያ ክልል በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና አናሳ ብሔረሰብ አባላት ላይ አክራሪ እስላሞች በታቀደ ሁኔታ ጥቃት ሲፈጽሙባቸው እንደነበረ ያስታወቀው ዘገባው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብቻ አክራሪ እስላሞች ከሕይወት ማጥፋት በተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናትን፣ መኖሪያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ልዩልዩ የንግድ ተቋማትን እንዲሁም ተሸከርካሪዎችን አውድመዋል ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዘውግንና የቆዳ ቀለምን ሽፋን ያደረገ በመሆኑ ድርጊቱን ውስብስበና በሌላው ዓለም ከሚፈጸሙ ጥቃቶች የተለየ ያደርገዋል ሲል ዘገባው አመልክቷል፡፡ በኦሮምያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚፈጸሙት እምነት ተኮር ጥቃቶች ከሌላ ብሔር በመጡ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ በሆኑ ክርስቲያኖችም ጭምር መሆኑ ጉዳዩን ልዩ እንደሚያደርገው ዘገባው አንስቶ በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከሚፈጸምባቸው የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት ሲልም ዘገባው አስነብቧል፡፡  የኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ሶሳይቲ ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው በአፍሪካ አንዳንድ ሀገራት ጭካኔ የተሞላበት የዘር ማጥፋት ወንጀል በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ መሆኑን አስታውቀው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባም ጠይቀዋል፡፡        
Read 921 times