Monday, 05 October 2020 00:00

“የተደራጀ አክራሪ ኃይል ቤተክርስቲያንን እያጠቃት እንደሆነ በተደጋጋሚ ለመንግሥት አሳውቀናል” ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ሰብሳቢ ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በባህልም ሆነ በሃይማኖት እንዲሁም በሕግ ራሳቸውን የመከላከል መብት አላቸው፡፡ የትኛውም ምእመን ራሱንም ሆነ በእምነት የሚመስሉትን የመጠበቅ ኃላፊትነት አለበት፡፡ ሌላውን ማጥቃት ሳይሆን ሌላው ሊያጠቃ ሲል ቀድሞ መከላከል ችላ የማይባል ተግባር መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሰዓት ኦርቶዶክሳውያን ራሳቸውን ለመላከል ሳይችሉ ቀርተው ወይም አቅሙ ስለሌላቸው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ስለማይፈቅድ ነው፡፡ ክፉን በበጎ እንጂ ክፉን በክፉ መልስ የሚል አስተምህሮ ቤተክርስቲያን የላትምና፡፡ ስምዐ ጽድቅ፡- በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች በተደጋጋሚ በኦርቶዶክሳውያንና በንብረታቸው ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቃት መድርሱ ምንን ያሳያል ይላሉ?  ቀሲስ ሙሉቀን፡- ከዚህ ቀደም እስላማዊው አክራሪ ቡድን የፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች በዋናነት አብያተ ክርስቲያናትንና ምእመናንን ዒላማ ያደረገ ነበር፡፡ በዚህኛው ጥቃት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ ላይ መንግሥት ትኩረት አድርጎ መከላከያ ሠራዊትን በማሰማራት አብያተ ክርስቲያናትን መጠበቅ ሲጀምር እስላማዊው አክራሪ ቡድን ደግሞ ታክቲክ ቀይሮ ምእመናንን፤ ቤታቸውንና ሀብት ንብረታቸውን ማጥቃት ጀመረ፡፡ የድርጊቱ ዋና ዓላማ ምእመናን መኖሪያ ቤት ሲያጡና የዕለት ጉርስ ሲርቃቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ወይም ተቸግረው እንዲሰልሙ ማድረግ ነው፡፡ ምእመናን ከሌሉ ደግሞ በየአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከሕንፃነት የዘለለ ሚና አይኖራቸውም፡፡ ከሰሞኑ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተከሰሠተው ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋም ምእመናን እንደተለመደው ቤተ ክርስቲያናቸውን በመጠበቅ ላይ እያሉ እስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን የምእመናኑን ቤትና ንብረት ይዘርፍና ያቃጥል ነበር፡፡ 

 

በዚህ ሁኔታ ታድያ ኦርቶዶክሳውያኑ በአንድ ጀምበር ከመጽዋችነት ወደ ተመጽዋችነት ተሸጋግረዋል፡፡ ችግሩ እንደ አጠቃላይ የሚያመላክተው አክራሪ ኃይሉ ከኦርቶዶክሳውያን የፀዳች ኦሮሚያን የመመሥረት ሕልም እንዳለው ነው፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በተደጋጋሚ ከሞራላዊ ልዕልና ያፈነገጠና ጭካኔ የተሞላበት ወንጀልን በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች እስላማዊው አክራሪ ቡድን በምእመናን ላይ በሚፈፅማቸው የወንጀል ድርጊቶች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጸጥታ ኃይሎች ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደሆኑ ይነገራልና ይህን እንዴት ይገልፁታል? በዚህ ሁኔታስ ሀገሪቱ ወዴት እያመራች ነው ይላሉ? 

ቀሲስ ሙሉቀን፡- እውነት ነው አንዳንድ የመንግሥት አካላትና የፀጥታ ኃይሎች ከእስላማዊው አክራሪ ቡድን ጋር አብረው በጋራ እየሠሩ መሆናቸው ለእኛ አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ሁልጊዜ ለከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች አዲስ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ግን መንግሥት ማመን የማይፈልገውን ጉዳይ ተገዶም ቢሆን ማመን ችሏል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋና አካባቢው የተፈፀመው ጥቃት በክልሉ ርእሰ መስተዳድርና በክልሉ ካቢኔ ተወስኖ የተፈጸመ ነበር፡፡ በዚያ ወቅትም የክልሉ ልዩ ኃይልና ”ሂጎ‘  በሚል ስያሜ የተደራጀው የጥፋት ኃይል ነበር በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ አሰቃቂ ጥቃት የፈጸመው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሲዳማ ክልል የተፈጸመውንም ጥቃት ይመሩ የነበሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋም በባለሥልጣናቱና በፀጥታ ኃይሉ የሚመራ ነው፡፡ 

በአንድ ወቅት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በጥቃት የሞቱ ኦረቶዶክሳውያን አስክሬን እንዳይቀበር እስከመከልከል ደረጃ እንደደረሰ እናስታውሳለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ ግለሰብ በኦሮሚያ ክልል ኦርቶዶክሳውያን የጠሩትን ”የመብታችን ይከበር‘ ሰላማዊ ሰልፍ ከልክሎ ሙስሊሙ ግን ሰልፍ እንዲወጣ የፈቀደ ግለሰብ ነው፡፡ ስለዚህ በኦሮሚያ ክልል ኦርቶዶክሳውያንን ሰልፍ መከልከል ምንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በአንድ ሀገር እየተኖረ ግለሰቡ ለሙስሊሙ የተለየ መብት ሰጭ ሆኗል፡፡ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በምእመናን ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ይመሩና ያስተባብሩ የነበሩት ፖሊስ ኮሚሽነሮችና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ የተደራጀው እስላማዊ አክራሪ ቡድን ከየወረዳውና ቀበሌው ተሰባስቦ ምእመናንን ለማጥቃት ወደከተማ በሚገባበት ወቅት ከላላና የሎጅስቲክ አቅርቦት ሲያደርግ የነበረው  ”የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ነኝ‘ የሚለው አካል ነው፡፡ በዚያን ወቅት በእነዚህ አካላት ላይ መንግሥት ቀደም ብሎ አስተማሪ ርምጃ ወስዶ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ትርምስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በሌላ በኩል ደግሞ ከጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን ጋር ወግነው ምእመናንን በየጊዜው በጭካኔ ያሳርዳሉ፡፡ የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ሽፋን አድርገው አክራሪዎቹ በምእመናን ላይ ጥቃት ሲፈጸሙ የምዕራብ አሩሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ለፖሊስ ኮሚሽነሩም ሆነ ለፀጥ ዘርፉ ኃላፊው ስልክ ደውለው ”ድረሱልን‘ የሚል ተማፅኖ ሲያቀርቡ ”እሺ‘ የሚል ምላሽ ከሰጡ በኋላ ስልካቸውን ዘግተው የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ እነዚህ የፀጥታ አካላት ድሮም ይሠሩት የነበረውን አሁንም ያለ ከልካይ እየሠሩ ነው፡፡ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከተፈለገ በመንግሥት ወንበር ላይ ተቀምጠው የሃይማኖትን ጉዳይ በሚያስፈፅሙ የፀጥታ አካላት ላይ አስተማሪ ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ እነዚህ አካላት ከአክራሪ እስላማዊ ቡድን የተሰጣቸውን ተልእኮ እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ሊቀጥሉ አይገባም፡፡ 

በሀገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ከተፈለገ ”የፀጥታ ኃይል ነን‘ ብለው የሃይማኖት ተልእኮን የሚያስፈፅሙት ላይ አስተማሪ ርምጃ ከተወሰደ ሌላው ነገር እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሎጀስቲክና ከለላ የሚሰጣቸውን አካል ከሕግ ፊት ማቆም ከተቻለ ሌላው ባልበሰለ ጭንቅላቱ ሊገድልና ሊዘርፍ የሚመጣውን ለመቆጣጠር ዘዴው ቀላል ይሆናል፡፡ በአብዛኛው የሕይወትና የንብረት ጉዳቶች የተፈፀሙት ከንቲባዎችና የፖሊስ አባላት በታዛቢነት ቆመው ይመለከቱ  በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ይህ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ሀገሪቱስ ወዴት እየሄደች  ነው? ያስብላል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ምእመናን በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ባሉበት ወቅት አንዳንድ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል  ምንም እንዳልተፈጠረ ጉዳዩን ሲያቃልሉት በተደጋጋሚ ይስተዋላልና ይኽ ምን ማለት ነው? 

ቀሲስ ሙሉቀን፡- የመጀመሪያው ሌላውን አካል ለማረጋጋት የታቀደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአብዛኛው በሚዲያ ቀርበው ማብራሪያ የሚሰጡት አጥቂዎቹ የፀጥታ ኃይሎች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ጥቃቱን የመሩ፣ ድጋፍ የሰጡ፣ ያበረታቱ፣ ሎጀስቲክስ ያቀረቡና ለአክራሪዎች ከለላ የሰጡ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ታዲያ የፈጸሙት በደል እንዳይታወቅባቸው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሁሉ ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ያወራሉ፤ በሰው ደምም ይቀልዳሉ፡፡ መረጃም ሲጠየቁ የሚፈልጉትን እንጂ እውነቱን እየተከናወነ ያለውን ነገር ለሕዝብ ይፋ አያደርጉም፡፡ መከላከያና የክልሉ ልዩ ኃይል ፀጥታን ለማስከበር ወደ አካባቢው  ሲሄዱ ”ተቆጣጥርነዋል ምንም ችግር የለም‘ እያሉ የሚመልሱ አካላት ናቸው፡፡ 

ስለሆነም ችግሩ መች እንደሚቆም ስላማይታወቅ ወጣቱ ተደራጅቶ ራሱንና ቤተክርስቲያኑን እንዲጠብቅ እንመክራለን፡፡ ችግሩ ከዚህ በኋላ ደግሞ የት እንደሚፈጠር አናውቅም፡፡ ሙስሊሙም፣ ፕሮቴስታንቱም፣ ፖለቲከኛውም፣ ብሔርተኛም እንዲሁም ዘረኛው ሲያኮርፉ የእልሁ መወጫ የሚያደርጓት ቤተ ክርስቲያንን ስለሆነ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሀገርን የማፍረስ ተልእኮ ያነገበ ሁሉ መጀመሪያ የሚያጠቃው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ቀድሞ ካላጠቃ  ሀገርን ማፍረስ አይችልም፡፡ ሀገርን ለማፍረስ ደግሞ የኢትዮጵያን ሚዛን ጠብቃ የያዘችውንና ለነርሱ ሀገርን የማፈረስ ተልእኮ ደንቃራ የሆነችባቸውን ቤተ ክርስቲያንን አስቀድመው ለማፍረስ ያልማሉ፡፡ 

አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች የመንግሥት አካላት ለአክራሪ ሙስሊም ከለላ እየሰጡ በምእመናን ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ ከማደርግ በዘለለ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሳሳተ መረጃ ሲሰጡ ነበር፡፡ መከላከያ ሠራዊት ችግሩን ለማረጋጋት በሚሄድበት ወቅት ”እኔ ሳልፈቅድ ለምን ገባህ‘  የሚሉ የዞን አመራሮች ባሉበት አንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንዴት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይቻላል? የእነዚህ አካላት ዓላማ ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲቀር፤ ተጨማሪ ንብረትና ሕይወት እንዲጠፋና ተልእኮ የሰጣቸውን አካል በማስደሰት ዓላማው እንዲሳካ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ጥቃቱ እንዲቀጥልና ሕዝብ ክርስቲያኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት ተማሮ ሀገሩን ጥሎ እንዲሄድ ማድርግ የመጨረሻ ግባቸው ነው፡፡ ምእመናኑ ቤታቸው ተቃጥሎ፤ ንብረታቸው ተዘርፎ የሚላስ የሚቀመስ ሲያጡ ሀገሩን ለቀው ሲወጡ ማየት ሕልማቸው ነውና እንዲወጡ ከየአካባቢው ተሰባስቦ የሚሄድላቸውን ሰብአዊ ርዳታ እንዳይጠቀሙም መንደርተኛ የዞን አመራሮች እርዳታውን ይመልሳሉ፡፡ ይህንን ጭካኔ የተሞላበት ውስበስብ የወንጀል ድርጊት ከማሳወቅ አንጻር ሚዲያዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- በቤተ ክርስቲያን ስም የተቋቋሙት የማኅበራት ኅብረት በዘላቂነት የቤተ ክርስቲያንና የምእምናን ክብርና መብት ለማስጠበቅ ምን እየሠሩ ይገኛሉ? 

ቀሲስ ሙሉቀን፡- ሁልጊዜም እንደዚህ ዓይነት መሰል ችግሮች ሲከሠቱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሁሉ ጥቃቱ ከሚፈጸምበት ቦታ ያገኘነውን መረጃ እናሳውቃቸዋለን፡፡ እየተፈጸመ ያለውን የወንጀል ድርጊት ሁሉ ሳይቆራረጥ ለመንግሥት አካላት በየጊዜው እናሳውቃለን፡፡ በዚህ መነሻነት ከመንግሥት አካላት ጋር በምንችለው መጠን እስካሁን እየሠራን እንገኛለን፡፡ አሉ የሚባሉ መረጃዎችን ሁሉ አደራጅተን ለቋሚ ሲኖዶስ አስገብተን ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን በትኩረት እንድታየው ጥረት እያደርግን ነው፡፡ ጥቃቱን ለመከላከል መፍትሔው ብዙ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ለተፈጠረው ችግር ሁሉ መፍትሔ እንድትሰጥ፣ልጆቿን እንድትጠብቅና ልጆቿም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ያለባትን ሁሉ እንድታደርግ መረጃዎችን ከመጀመሪያ አንሥቶ እስከ መጨረሻው አስገብተናል፡፡ በተጨማሪም በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ ጭፍጨፋ ባወጁ ሚዲያዎች ለአብነትም OMN (ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ) የተባለውን የግል የቴሌቭዥን ጣቢያ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ከሰን በሕግ እንዲጠየቅ ጥረት ያደረግን ቢሆንም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግን ምንም ዓይነት ሕጋዊ ርምጃ ሲወስድበት አላየንም ከዚህ ቀደም ርምጃ ባለመወሰዱ ይህ ሚዲያ በአርቲሰት አጫሉ ሁንዴሳ ሞት ማግስት ባሰራጨው ተጨማሪ የዘር ጭፍጨፋ መረጃ ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በግፍ ተገድለዋል፡፡ ሀብት ንብረታቸው ተዘረፈ፤ የተረፈው ተቃጠለ፡፡ በሕይወት የተረፉ ምእመናንም በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ ናቸው፡፡ ሌሎቹም ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ በወቅቱ መደረግ የነበረበትን ቢያደርጉ ኖሮ ይህ ሁሉ ቀውስ ባልተከሠተ ነበር፡፡ አሁን እጃችን ላይ በርካታ መረጃዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን መረጃዎች ተጠቅመን ክስ ለመመስረት ለዐቃቤ ሕግ  አደራጅተን እየሰጠን ነው፡፡ 

አንዳንዴ ኢስላም ”ሰላም ነው‘ ይላሉ፤ ግን ሰላምነቱ በተግባር የት አለ? ”ሃይማኖቴ ሰላም‘ ነው ካለ ከጅግጅጋ እስከ ኦሮሚያ ኢስላም በሚበዛባቸው አካባቢዎች ክርስቲያኖችን የሚገድልና የሚያስገድልን አክራሪ እስላማዊ ቡድን ማስቆም አለበት፡፡ የሰላም ነው የሚለው አካል ይህን አረመኔያዊ ድርጊት ሊያወግዝ ይገባል፡፡ ይህንንም በተግባር ሊያሳይ ይገባል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤውስ ምንድን ነው እየሠራ ያለው? ድርጊቱን የሚያወግዘው መቼ ነው? መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቱያንን መጠበቅ ያለባቸው ለቤተ ክርስቲያን ብለው ሳይሆን ለሀገር አንድነትና በፖለቲካ ሥልጠናቸው መቆየት እንዲችሉ ነው፡፡ መንግሥት በመንበሩ መቆየት ከፈለገና ፓርቲዎች ሥልጣን መያዝ ከፈለጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቱያንን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ የአንድነት ምሰሶ ተናግቶ የሀገር አንድነት አይታሰበም፡፡ ፖለቲካና ሥልጣን የሚኖረው ሀገርና ሕዝብ ሲኖር ብቻ ነውና፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?

ቀሲስ ሙሉቀን፡- በዚህ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ እራሳችንንና ሀገራችንን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ሀገር ያለ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቱያንም ያለ ሀገር አይኖሩም፡፡ ሁለቱ የማይነጣጠሉና አንዱ የሌላው ህልውና መሠረት ሆነው የሚኖሩ ናቸው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ነውረኛ ድርጊት የቤተክርስቲያንን ውለታ የካደ በመሆኑ ፖለቲከኞችም፣ ሃይማኖተኞችም፣ ብሔርተኞችም እንዲሁም ጽንፈኞች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡ ተከባብረን ተፈቃቅረንና በሃይማኖት እኩልነት አምነን ልንኖር ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ለሁላችን የማትሆን ሀገር ለማንኛችንም አትሆንም፡፡ ወደ መጠፋፋት ከመሄዳችን በፊት ቆመን ማሰብ ብንችል መልካም ነው፡፡ በተለይ በክርስቲያኖች ላይ ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው እስልምና በሚበዛባቸው አካባቢዎች ነውና እዚያ አካባቢ ያሉ የሙስሊም ሸኮች፣ ኡስታዞች፣ ኡለማዎችና ሌሎች የሀገር ሽማግሌዎች ልጆቻቸውን ማስተማርና መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ልጆቻቸው የማንም ፖለቲከኛና አክራሪ ኃይል መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም፡፡  ”አክራሪ እስላሞች እኛን አይወክሉም‘  በማለት ወንጀለኛውን በትክክል አሳልፈው  መስጠት አለባቸው፡፡  

 

Read 587 times