Thursday, 08 April 2021 00:00

“ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመበረዝ በተነሡ ቡድኖች ላይ እስካሁን የተወሰደ ተጨባጭ ርምጃ የለም” - ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ (የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመበረዝ ከካቶሊክ እስከ ፕሮቴስታንት ከተሐድሶ እስከ ቅባትና ጸጋ እንዲሁም ሌሎች ለዘመናት ጥረት ሲደርጉ ቆይተዋል። እነዚህ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ካሉ ሀገራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚደረግላቸው ድጋፍ በከፍተኛ የሰው ኃይልና ገንዘብ ታግዘው ለዘመናት የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ሲሸረሽሩ ምእመናንን ሲያወዛግቡና ሲከፋፍሉ ቆይተዋል። ቤተ ክርስቲያንም ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጋ ከቅጥሯ ውጭ ያሉትን ቀሳጥያን ከቅጥሯ ስታርቃቸው በውስጧ የነበሩ የእናት ጡት ነካሾችን ደግሞ በመምከር፣በማስተማር፣ንስሐ በመስጠት በዚህ ሁሉ አልፈው የማይመለሱትን ደግሞ በማውገዝ ከዐውደ ምሕረቷ እንዳይቆሙ ከቅጥሯ እንዳይደርሱ በማድረግ አስተምህሮዋን ከብረዛ ምእመኖቿን ደግሞ ከነጠቃ ስትታደግ ቆይታለች። እነዚህ የበግ ለምድ የለበሱ ነጣቂ ተኩላዎች ለጊዜው የተሳካላቸው ቢመስላቸውም  የቤተ ክርስቲያንን አሸናፊነትና መለኮታዊ ኃይል መቋቋም ሳይችሉ ቆይተዋል። የነጣቂ ተኵላዎች ጥረትም ከንቱ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በቻለችው መጠን ከሐዋርያዊ ጉዞዋ ሳትገታ ለዓለም ብርሃን መሆኗን ቀጥላለች። 

 

ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ ቦግ እልም የሚሉ ቀሳጥያን ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ ለመበረዝ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ እንደሆነ እንገነዘባለን። ቀሳጥያኑ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ በመጤ አስተምህሮ ለመተካት ደፋ ቀና ከሚሉባቸው አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት አንዱ ነው። “የቅባትና ጸጋ እምነት አራማጆች ነን” በማለት በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ምእመናንን ሲከፋፍሉ፣

የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ሲሸረሽሩ፣ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባቶችን ሲያዋክቡ፣ ከሥራ ገበታቸው ሲያባርሩ፣ ሲያስገድሉ፣ ዶግማዊ የቤተ ክርስቲያን መጠሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያንን “ተዋሕዶ” የሚለውን በማውጣት ወደ “ጥንታዊቷ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን” ኑ እያሉ ሲያታልሉ እንዲሁም ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ ሲፈጽሙ ቆይተዋል። በአሁኑ ሰዓትም የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን የብጥብትና የሁከት ቀጠና ለማድረግ በትኩረት እየሠሩ ይገኛሉ። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የሀገረ ስብከቱ ማኅበረ ምእመናን፣ አገልጋይ አባቶች፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አገኘው ተሻገር እንዲሁም የአጎራባች ሀገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ቅዱስ ሲኖዶስም የሃይማኖት ጉዳይ ነውና ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ለምሥራቅ  ጎጃም ሀገረ ስብከት አጎራባች ከሆኑ አህጉረ ስብከት መካከል የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት አንዱ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ጉዳዩን አስመልክቶ ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል። ያደረጉትን ቆይታም ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በሚመች መልኩ ወደ ጹሑፍ ቀይረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ። 

ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ። 

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- ጉዳዩ አሳስቧችሁ አሳቤን እንዳካፍላችሁ ለቃለ መጠይቅ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፤ ተባረኩ።  

ስምዐ ጽድቅ፡- የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በሀገረ ስብከት ደረጃ የተዋቀረው መቼ ነው? በውስጡስ ምን ያህል አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ? በአሁኑ ሰዓት የሕዝበ ክርስቲያኑ ሁኔታ ምን ይመስላል? አገልግሎቱስ?

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ በሀገረ ስብከት ደረጃ የተዋቀረው በ፳፻፬ ዓ.ም ነው። ሀገረ ስብከቱ በርካታ ምእመናን፣ ካህናት አገልጋዮች እንዲሁም አጥቢያዎች ያሉበት ነው። በዚህ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከ፲፻፰፻ (አንድ ሽህ ስምንት መቶ) በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ሲሆን በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናትም ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የበቁና የነቁ ካህናት፣መምህራነ ወንጌልና ሊቃውንት ይገኛሉ። አብዛኛው የአካባቢው ኅብረተሰብ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ከወጣቶች ጀምሮ እስከ አገልጋዮች ድረስ የሚሰጠው አገልግሎት ነፍስን የሚያስደስት የመንፈስ ርካታን የሚጨምር ነው። በሁሉም አጥቢዎች ወንጌል በበቂ ሁኔታ ይሰበካል፣ ጸሎተ ምህላ ይደረጋል እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑን በዕውቀትና በምግባር የሚያንፁ የተለያዩ መርሐ ግብራት ይዘጋጃሉ። 

በሀገረ ስብከታችን ይህ ዘመን ያመጣው ጊዜ የወለደው የተሐድሶ እንቅስቃሴ የለም። ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ኅብረተሰብ ኦርቶዶክሳዊ በመሆኑ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ የሆነ ባዕድ አስተምህሮን አይቀበልም፤ ለዚያም ተገዥ አይሆንም። ምእመኑ ሃይማኖቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ በወሬ ሳይሆን የሃይማኖቱን አስተምህሮ በተግባር እየገለጠ  የሚኖር በመሆኑ ክፉና በጎውን የሚበጀውንና የማይበጀውን አስተምህሮ ጠንቅቆ ለይቶ የሚያውቅ ነው። ምእመኑ የቀደመችና እውነተኛ የሆነችውን እምነቱን አጥብቆ እንዲይዝ ሌሎች ሊቃውንት ከሚሰጡት ትምህርተ ወንጌል በተጨማሪ እኔም በየወረዳውና በየአጥቢያዎች እየተዘዋወርኩ አስተምራለሁ፤ እመክራለሁ፤ እባርካለሁ። ይህ መሆኑም ሀገረ ስብከቱ በደንብ የተሰናዳ እንዲሆን፣ ብዙ ሊቃውንትንም ማፍራት እንዲቻል ቤተ ክርስቲያንም በልማት እንድታድግ አድርጓል። 

ቤተ ክርስቲያን በምታከናውነው የልማት ሥራ ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከዕለት ወደ ዕለት ክርስቲያናዊ ግዴታውን በበቂ ሁኔታ እየተወጣ ይገኛል። ምእመናን በየጊዜው የሚያደርጉት የገንዘብና የዓይነት ርዳታ ለተቋማት ግንባታ ገቢ ማስገኛ፣ ለጉባኤ ቤቶች ግንባታ፣ ለአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ግንባታና ለነባር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና እየዋለ ይገኛል። ሀገረ ስብከቱ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ አገልጋዮችን ሳይቀር ተቀብሎ እያስተናገደ ነው። በትምህርት ረገድም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ባሉት ጉባኤ ቤቶች በጥሩ ሁኔታ እያስተማረ ይገኛል። በአጠቃላይ በሀገረ ስብከቱ ሙሉ አገልግሎት አለ፤ በአገልግሎቱም  ምእመናንም ሆኑ አገልጋዮች ደስተኞች ነን።   

ስምዐ ጽድቅ፡- የሀገረ ስብከትዎ አጎራባች በሆነው ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ላይ እየተፈጸመ ያለው የዶግማና ቀኖና ጥሰት በተለይ ከቅባት እምነት ጋር ተያይዞ እንዲሁም አስተዳደራዊ በደሎችን በተመለከተ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል፤ ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ምን አነሣሣዎት? 

ብፁፅ አቡነ ዘካርያስ፡- የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ለእኔ አጎራባች ሀገረ ስብከት ብቻ ሳይሆን ለአሥራ ስድስት ዓመታት ያስተማርኩበት ነው። እዚያ በነበረኝ ቆይታ ብዙ ካህናትን ክህነት ዲያቆናትም ዲቁና የሰጠሁበት ሀገረ ስብከት ነው። በሀገረ ስብከቱ ብዙ ቁም ነገር የሠራሁበት፤ የብርቱ ሊቃውንት መፍለቂያና የጠንካራ ምእመናን መገኛ እንዲሆን ያደረኩት ነው። ነገር ግን ሁኔታውን መለስ ብየ ሳየው እኔ ከዚያ ሀገረ ስብከት ከወጣሁ  በኋላ የነበረው እንዳልነበር የተሠራው እንዳልተሠራ ሆኖ መመልከት ጀምሬአለሁ። ነገሮች ሁሉ መሥመራቸውን ስተው የዶግማ፣ የቀኖናና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች የሚስተዋሉበት ሀገረ ስብከት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለሀገረ ስብከቱ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች አህጉረ ስብከት ጭምር ችግር እየፈጠረ መሆኑን በመረዳቴና ችግሩ ከመባባሱ በፊት መፍትሔ እንዲበጅለት በማሰብ የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል ለሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ ጽፌአለሁ። 

ምንም እንኳን አንዱ ሀገረ ስብከት በሌላው ላይ ጣልቃ አይገባም የሚል መመሪያ ቢኖርም አንገብጋቢ የሃይማኖት ጉዳይ በሚኖርበት ወቅት ግን ጣልቃ መግባትን መመሪያው ስለማይከለክል እኔም ጉዳዩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለቅዱስ ሲኖዶሱ በጻፍኩት ደበዳቤ ላይ ያለውን ሁኔታ በግልጽ አስረድቻለሁ። ደብዳቤውን ለቅዱስ ሲኖዶስ የጻፍኩት በነበረኝ ሥጋት ብቻ ተነሣሣቼ ሳይሆን ‹‹በቅባት እምነት›› ስም የተደራጁ ኃይሎች የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ለመሸርሸርና አንድነቷን ለማናጋት ጥረት እያደረጉ ያሉ በመሆናቸውና በሀገረ ስብከታችን ጭምር ገብተው የጥፋት ተልዕኮቸውን ለመፈጸም ሥምሪት ሲያደርጉ በመታዘቤ ነው። ‹‹በቅባት እምነት›› ስም ከተደራጁት ኃይሎች አንደኛው የተሐድሶ ክንፍ ሲሆን ዓላማቸውም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት መጣስ፣ ልዩነት መፍጠርና እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ  በባዕድ አስተምህሮ መበርዝ ነው። 

እንደሚታወቀው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጥንታዊና ታሪካዊ አድባራትና ገዳማት ያሉበት፣ ታልልቅ አባቶችና ሊቃውንት የሚገኙበት፣ በርካታ ምእመናን ያሉበትና ቀደምት የሆነ ሀገረ ስብከት ነው። በዚህ ሀገረ ስብከት እኔ በነበርኩበት ወቅት በጣት የሚቆጠሩ አፈንጋጭ ኃይሎች ከመኖራቸው ውጭ ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጅነት አክብሮ የሚኖርበት ነበር። የነበሩት አፈንጋጮችም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዳይጥሱና ምእመናንን በባዕድ ትምህርት እንዳይከፋፍሉ በጥንቃቄ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገባቸው በቤተ ክርስቲያን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ የምእመናን አንድነት ተጠብቆ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተከብሮ ነበር የቆየው። በዚህ ወቅት ግን ሀገረ ስብከቱ ድሮ ከነበረው በተቃራኒ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል። 

 

Read 412 times