Friday, 06 August 2021 00:00

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ ጥንታዊ ገዳሞቻችን አስቸኳይ ጥበቃና ክብካቤ ይፈልጋሉ! ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ባለፈው እትማችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ እትማችን ደግሞ ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ ቀርበናል። በጥሞና ትከታተሉ ዘንድ ግብዣችን ነው።  ግብጻውያኑ ጳጳሳትም ሆኑ መነኮሳት በእኛ ገዳማትና መነኮሳት ላይ የሚፈጸሙትን አረመኔያዊ ተግባር ለተመለከተ ክርስቲያን መሆናቸውን ይጠራጠራል። በጣም ጨካኞች፤ የራሳቸውን እንጂ የሰውን ሐሳብ፣ ስሜትና ፍላጎት የማያከብሩ ዕብሪተኞች ናቸው። በገዳማችን ውስጥ በብዛትና በኃይል እየገቡ “አንወጣም” በማለት ለመውረር ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት በአካባቢው  የፀጥታ ኃይልና በልጆቻችን በሳልነት ወረራውን ማካሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል።ምንም እንኳን ኃይልና ብዛት ቢኖራቸውም ከሰው ኃይል የእግዚአብሔር ኃይል ይበልጣልና ምስኪኖቹና በቁጥር አናሳ የሆነው በመጨረሻ አሸንፈን ጠላቶቻችን አፍረው ተመልሰዋል። በዚህም ምክንያትም ገዳማዊ ርስቶቻችንን ማስከበር ችለናል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገዳሞቻችን እየተፈጸመ ያለው ችግር ዘመን የማይፈታው እየሆነ መጥቷል።በዓላት በቀረቡ ቁጥር ዕብሪተኛ ግብጻውያን “የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮቻቸው” ትንኮሳ ይፈጽሙብናል። እግዚአብሔር ራሱ መፍትሔ እስካላመጣ ድረስ በግብጻውያኑ እየተፈጸመብን ያለው ጥቃት የሚቆም ወይም የሚቀንስ አይመስለኝም። ለጆሮ የሚከብዱ ለዓይን የሚያስጨንቁ በደሎች ተፈጽመውብናል። የፈረሱ ገዳማትን የመጠገን፣ የማደስና የመንከባከብ  መብታችን ተነጥቆ ስንገፋ ቆይተናል።

 

በዴርሡልጣን ገዳማችን ላይ ድንገተኛ ወረራ በተካሄደበት ወቅት እኛ የገዳሙ አባቶችና ኢትዮጵያውያን ካደረግነው ጥረት በተጨማሪ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምሳደር የሆኑት ክቡር አቶ ረታ ዓለሙ እና የእስራኤል የሀገር ውስጥ ደኅንነት ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ጋዲ ይቨርኮን ያደረጉት አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ ነው። በተለይ አቶ ጋዲ ይቫርከን የፀጥታ ኃይሉን አዘው ወራሪውን የግብጽ ኃይል ከቦታው ለቆ እንዲወጣ ያደረጉበት መንገድ ምስጋና የሚገባው ነው። እርሳቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ቤተ ክርስቲያን ታመሰግናቸዋለች፤ ዕውቅናም ትሰጣቸዋለች። በወቅቱ በተደረገልን የተጠናከረ የፀጥታ ሥራ የትንሣኤ መዳረሻ በዓላት በአግባቡና በሰላም እንድናከብር ሆኗል። አቶ ጋዲ ይቫርከንም የትንሣኤ መዳረሻ በዓልን ስናከብር በቦታው ተገኝተው የበዓሉ ታዳሚ ከመሆናቸውም ባሻገር ንግግር አድርገዋል።በንግራቸውም በቀጣይ የገዳመቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን አርጋግጠውልናል።በዘህም ምክንያት ኃዘናችን ርቆ ደስታችን ተመልሶ የትንሣኤ በዓልን በድምቀት  አክብረናል።

ስምዐ ጽድቅ፡- ግብጻውያኑ በየጊዜው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ላይ ወረራና ትንኮሳ ይፈጽማሉ፤ወረራውንና ትንኮሳውን ያገናዘበ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ያልተቻለው ለምንድን ነው?

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- ችግሩ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። በመሆኑም ከችግሩ ስፋትና ጥንካሬ አንፃር በእኛ አባቶች አቅም ብቻ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስለኝም።የእኛን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በመላው ዓለም ያሉ የሕግ ባለሙያዎችን አሳትፎ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። ቤተ ክርስቲያን ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጋር የሀገራችን መንግሥት ደግሞ ከመንግሥታት ጋር በጋራ በመሥራት በውይይትና በምክክር መፍትሔ ማምጣት ካልተቻለ ሁልጊዜ ሲቆራቆሱ መኖር ነው።እስከዚያ ድረስ ግን ገዳማችንን ለመውረር የሚጋበዙ አካላትን ባለ አቅማችን ለመከላከል ጥረት እያደረግን እንቆያለን። ወራሪዎቹም ከወረራ ተግባራቸው አይታቀቡምና ዘላቂ መፍትሔ ግን ሊመጣ ይገባል እላለሁ።

በቤተ ክርስቲያናችንና በመንግሥታችን ቸልተኝነት በርካታ ጥንታዊ የገዳማት ይዞታዎቻችን በግብጾች ተወስደዋል። ከወረራ የተረፉ ስድስት ገዳሞቻችንን ጨምሮ ሌሎች ይዞታዎቻችንን ለመውረር አሁንም ድረስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።በሕግ የያዝነውን ይዘን እንድንቀጥል ቢደረግና ከዚህ ቀደም በወረራ የወስዷቸውን ደግሞ በሕግ አግባብ የሚመልሱበት መንገድ ቢፈልግ መልካም ነው። እኔ ሁሌም አዝናለሁ፤ አለቅሳለሁም።መከራችን የሚቀጥለውም እስከመቼ ነው? ብዬም እጠይቃለሁ፤ እጸልያለሁም። ሁሉም እገዛ የሚያደርገው ለእነርሱ ነው። እኛን የሚያግዘን ምድራዊ ኃይል ባይኖርም የሰማዩ አምላክ ግን ሁልጊዜም አሳፍሮን አያውቅም።ገዳሞቻችን ለመውረር ሲመጡ ፈጣሪያችን አፍረው እንዲመለሱ ይረዳናል።

ስምዐ ጽድቅ፡- የገዳማቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- ዴርሡልጣንን በተመለከተ በቋሚነት ሥራ ለመሥራት ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ከመንግሥት ዲፕሎማቶች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተውጣጡ አባላት የሚመሩት ተቋም  ቢመሠረት ሀገርን የሚያኮራ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ያግዛል።የተቋሙ ሥራም የቤተክርስትያንን ቅድስና፣ ያላትን ታሪካዊ ይዞታ፣ የሀገራችንን ዲፕሎማሲያዊ አቋም ለማሳወቅና ጥንካሬያችንን ለማሳየት ይጠቅማል።

ተቋሙ የራሱ የሆነ የጥናት ዘርፍ የሚኖረው ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ታሪክ እያስጠና በዓለማቀፍም በኢትዮጵያ ቋንቋዎችም እያሳተመ የውጭውን ዓለም የሚያስገነዝብ፣ የተሳሳተውን የሚያስተካክል፣ የተጣመመውን የሚያቀና ተግባር ለመፈጸም ያስችለዋል።ከዚህ በተጨማሪ ካለአግባብ የተወሰዱብንን ይዞታዎች ታሪክ ጠቅሶ፣ ሰነድ አቅርቦ ተከራክሮ የሚያስመልስ የእኛ የሆነውን ካልሆነው የሚለይ፣ በግብፆችና በኢትዮጵያውያን መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ለዓለም ኅብረተሰብ ኢትዮጵያውያን ምን እንዳላቸው የሚያሳውቅ ቢሆን ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን ምን እንደነበራቸውና እንዴት ያላቸውን ጠብቀው ማቆየት እንደሚጠበቅባቸው የሚያስገነዝቡ ምርምሮችን፣ ዐውደ ጥናቶችን፣ የውይይት ኮንፍረንሶችን የሚያዘጋጅ ክፍል እንዲኖረው ቢደረግ ውስብስብ ችግሮች ይቃለላሉ።

ጋዜጦችን፣በራሪ ወረቀቶችን፣ የምርምር መጽሔቶችንና መጻሕፍትን በማዘጋጀት ኢትዮጵያውያን ለበለጠ ሥራ እንዲነሣሡ ማድረግ የተቋሙ ተግባር ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን መሥራት የሚገባትን፣ መንግሥት መፈጸም የሚኖርበትን፣ ምሁራን ማበርከት የሚጠበቅባቸውን ለይቶ ማሳት የሚችል መሆን አለበት። በአንድ በኩል የተወሰዱብንን ማስመለስ፣ በሌላ በኩል ባለ ሀብቶችን፣ በጎ አድራዎችን፣ የታሪክና የቅርስ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉትን በማሰባሰብ ዴርሡልጣን ይዞታችን ከሆነ ጀምሮ እስከ ዘመናችን የተጓዘበትን የታሪክ ውጣውረድ፣ በምስልም በድምፅም ሊገልጡ የሚችሉ ሙዚየሞችን፣ ቤተ መዘክሮችን፣ የምርምር ማእከላትን ማቋቋም ይኖርበታል። ያለንን ከማልማትና የተወሰደብንን ከማስመለስ በተጨማሪ አዳዲስ ገዳማትን ለመመሥርት የሚያስችሉ ቦታዎችን መግዛትም የተቋሙ ሥራ ይሆናል።ኢትዮጵያውያም እንዲህ አይነት ዓለምን የሚያስደንቅ ተግባር የማንፈጽምበት  ምክንያት የለንም።ሥራችንን የዘመቻ ከማድረግ ወጥነትና ተከታታይነት ያለው ማድረግ ይኖርብናል።በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገራትም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለልደትና ለትንሣኤ ኢየሩሳሌም ይሔዳሉ። መሔዳቸው መልካም ነው። በዚያ ያትንና የሰሙትን በመቅረጽ በማኅበራዊ ሚዲያ ከመልቀቅ የዘለለ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል። በልዩ ልዩ አስጐቢኝዎች ቦታውን የረገጡ ምእመናን ለጧፍ፣ ለአልባሳት ለሌላም የጎደለ ነገር ማሟያ ከማዋጣት ባለፈ በቋሚነት ገዳማቱ የሚተዳደሩበትን ሥራ ማሰብ አለባቸው። በዴር ሡልጣን በሚገኘው ገዳም የሚኖሩ መነኮሳት የገዳሙን ሥርዐትና ትውፊት ሊጠብቁ፣ ለሌላውም ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል። የሚመለከተው አካልም የገዳሙንና የምንኵስናን ክብር ሊያስጠብቅ ይገባል።የአካባቢውን ሰላም የሚነሡትን እያስወገዱ በሥራ አርአያ የሚሆኑትን እና አባቶቻቸው ምን እንደሠሩ ጠይቀው በመረዳት እነሱም በቀደምቶቻቸው ፈለግ ለመጓዝ የሚፈልጉትን ወደ ቦታው መውሰድ ይገባል።ስምዐ ጽድቅ፡- በዚህ ወቅት በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የእናንተ ሥጋት ምንድን ነው?

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- እውነት ለመናገር ጦርነቱ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮብናል። በእኛና በገዳሞቻችን ላይ ምን ይደርስብን ይሆን እያልን ጠዋት ማታ እንጨነቃለን። ክፉውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያርቅልን እየጸለይን ነው። ጦርነቱን ተከትሎ በአካባቢው የሚያሳዝኑ ነገሮች ተፈጥረዋል። ምንም እንኳን በእኛና በገዳማቱ ላይ የደረሰብን ጉዳት ባይኖርም ሰላምና አንድነት ለሁሉም አስፈላጊ ነውና በአካባቢው ሰላም እንዲመጣ እንፈልጋለን።

ስምዐ ጽድቅ፡- ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- ግብጾች ወረራ የሚያደርጉባቸውን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ ገዳሞቻችንን በተመለከተ በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥበብ በተሞላበትና መረጃን መሠረት ባደረገ መንገድ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር ይኖርበታል። ገዳማችንን በመጠበቅ ታሪክ የማይረሳው ሥራ በመሥራት ሀገራችንን ማስከበር የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ቀደምቶቻችን ጠብቀውት የኖሩትን በእኛ ዘመን አሳልፈን መስጠት የለብንም። በዕውቀት እና በእምነት በመመራት የሀገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ጥቅም ማስጠበቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ መሆኑን በመረዳት ለትውልድ በሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ተግባር መፈጸም በዚህ ዘመን ከምንገኝ ኢትዮጵውያን ሁሉ የሚጠበቅ ነው።

በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም እየደረሰባት ያለው መከራ የከፋ ሆኗል። የችግሮቹን መጠንና ስፋት በአጭር ጊዜ ዘርዝሮ ለመጨረስ እጅግ አስቸጋሪ ነው። በምእመናንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አስነዋሪ ድርጊቶችን ለማስቆም አንድነትን ማጠናከርና እግዚአብሔርን በጸሎት መለመን ያስፈልጋል። ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር እንደሆነች እንድትቆይ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን። በዚህ ወቅት በሀገራችን በተለየዩ አካባቢዎች እየሰማነው ያለው ነገር እጅግ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭና አሳፋሪ ነው። በየገዳሙ በየበረሃው ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት የሚያለቅሱ የሚያዝኑ አሉና የእነርሱ አምላክ ደግሞ ሀገራችንን ለክፉ ነገር አሳልፎ አይሰጥም።ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችንን ሰላም ያድርግልን።አሜን!   

ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን ስለነበርን አጭር ቆይታ እግዚአብሔር ይስጥልን።

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- የገዳሞቻችን ጉዳይ አሳስቧችሁ የማውቀውን መረጃ እንድሰጣችሁ ለቃለ መጠቅ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ።

 

Read 427 times

Related items