Wednesday, 28 April 2021 00:00

“ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመበረዝ በተነሡ ቡድኖች ላይ እስካሁን የተወሰደ ተጨባጭ ርምጃ የለም” - ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ (የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ባለፈው እትማችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ እትማችን ደግሞ ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ ቀርበናል። ትከታተሉ ዘንድ ግብዣችን ነው። ስምዐ ጽድቅ፡- በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የሚኙት ‹‹የቅባት እምነት›› አራማጆች በርስዎ ሀገረ ስብከት ላይ ያደረሱት ተፅእኖ ካለ ቢገልጹልን? ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- ሀገረ ስብከታችን ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ቀሳጥያኙ በተለይም በደጋ ዳሞት በኩል እየገቡ ሕዝበ ክርስቲያኑን ሊከፋፍሉና ባዕድ አስተምህሯቸውን ሊያስፋፉ ሲሞክሩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክልከላ በማድረግ በአካባቢው እንዳይንቀሳቀሱ ስናደርግ ቆይተናል። የአካባቢው ምእመናንም ሆኑ ካህናቱ ችግሩን በደንብ የተረዱ፣ እምነታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸውና ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና በመገመት በሀገረ ስብከታችን ከሙከራ የዘለለ የተጠናከረ እንቅስቃሴ አያድርጉም። በሀገረ ስብከታችን ውስጥ ሰርገው በሚገቡበት ወቅት በተቆጡ ምእመናንና አገልጋዮች አማካይነት ችግር ውስጥ እንዳይገቡ እኔም ምእመናንና ካህናትን በመሰብሰብ ችግር ሳይፈጠር በዓይነ ቁራኛ ብቻ ተከታትለው በሰላም እንዲወጡ የማድረግ ሥራ ብቻ እንዲሠሩ እነግራቸዋለሁ። አልፎ አልፎ ወደ ሀገረ ስብከታችን በሚመጡበት ወቅት በምእመናን በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት አፍረውና ተሸማቅው ይመለሳሉ። 

 

በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በሕዝቦች መካከል ሊፈጥር የሚችለውን ችግር አስቀድመው የተረዱት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር የሆኑት ክቡር አቶ አገኘው ተሻገርም የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ ጽፈዋል። እርሳቸው የጻፉት ደብዳቤም በጣም አስፈላጊና የክልሉ መንግሥት ምን ያህል ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጠው ያመላከተ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የክልሉ መንግሥት በዚህ ምክንያት ችግር ከመፈጠሩ በፊት ጉዳዩን ተረድቶ ለመፍታት ያደረገው ጥረት የሚመሰገንና ሌሎች አካባቢዎችም ከዚህ አርቆ አሳቢነት ሊማሩ ይገባል። የክልሉ መንግሥት ላደረገው አስተዋፅኦ ለቅዱስ ሲኖዶስ በጻፍኩት ደብዳቤ ላይ አመስግኛለሁ፤ ለወደፊቱም አመሰግናለሁ። የክልሉ መንግሥትና የእኔ ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ገብቷል። በቀጣይም ከአባቶችና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በመሆን ችግሩን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ያለሠለሰ ጥረት አደርጋለሁ። 

በሃይማኖትና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጉዳይ የሚደራደር ትውልድ ሊኖር አይገባም። መንግሥት የቤተ ክርስቲያኗ አንድነትና ሥርዓት መጣስ አሳስቦት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ካደረገ እኛ ቤተ  ክርስቲያንን እና ምእመናንን የምናስተዳድር የቤተ ክርስቲያን አባቶች ደግሞ ችግሩ በሰከነ መንገድ እንዲፈታ መታለፍ ያለበትን ውስብስብ መንገድ ሁሉ ማለፍ ይጠበቅብናል። የክልሉ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን እንደዚህ ካለ አሳሳቢ ችግር እየጠበቃት በመሆኑ እኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ከክልሉ መንግሥት ጎን በመቆም የድርሻችን ልንወጣ ይገባል። 

አሁን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ያለበት ሁኔታ በጣም የሚያሳዝንና የሚያስለቅስ ነው።በአካባቢው የተወሰኑ ‹‹መነኰሳት›› ነን የሚሉ ግለሰቦች ተነሥተው ራሳቸውን ‹‹ፓትርያርክና ሊቀ ጳጳስ›› አድርገው ሾመዋል። የቤተ ክርስቲያንን ስያሜም ከኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ‹‹ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን›› ቀይረውታል። እነርሱ በራሳቸው የሰየሟቸው ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ንብረቶች ናቸው። ይህንን ግፍ የተመለከቱ ምእመናንም በጣም እያዘኑና እያለቀሱ ይገኛሉ። እኔ ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ የጻፍኩት ስለ አካባቢው ችግር በርቀት ከሰው በሰማሁት ተነሣሥስቼ ሳይሆን በአካባቢው ተገኝቼ ችግሩን ተዘዋውሬ ከተመለከትኩ በኋላ ነው። 

ባለፈው ጥቅምት ወር በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ የችግሩን ጥልቀትና ሥፋት በሚገባ አስረድቻለሁ። ራሳቸውን ‹‹ፓትርያርክና ሊቀ ጳጳስ›› አድርገው የሾሙ ግለሰቦችም ‹‹ክህነት እንሰጣለን” በሚል ሕዝቡን እየሰበሰቡ ለሁሉም ሰው እነርሱ ‹‹ክህነት›› ያሉትን እያደሉ እንደሆነ አረጋግጫለሁ። ይህ ድርጊት እንኳን ለኔ ለመንጋው ጠባቂ ይቅርና ለማንም ሌላውም ሰው  እጅግ ያሳዝናል፤ ያስለቅሳልም። ‹‹በእግዚአብሔር ጸጋ ተሹመናል›› የሚሉት ግለሰቦች የክብር ቆብ የሆነውን አስኬማ እንዳይጠቀሙ፣ ልብሰ ተክህኗቸውን እንዲያወልቁ እና ዘመናቸውን በሙሉ በመረጡትና በወደዱት ገዳም ውስጥ ሆነው የንስሓ ዕድሜያቸውን እንዲጨርሱ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት አፈጻጸሙንም ሊከታተሉት የሚገባቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ነበሩ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ችግሩ እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት የለም። ብፁዕነታቸው የሀገረ ስብከታቸውን ችግር ቶሎ እንዲያስተካክሉ በተደጋጋሚ ሐሳብ ሰጥቻለሁ፤ ቤተ ክርስቲያን ስትፈርስ ቆመው እንዳይመለከቱ ተናግሬአለሁ። የተሐድሶ የግብር ልጆችና ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ጊዜያት ያወገዘቻቸው ግለሰቦች ከክፉ ተግባራቸው ጋር በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ነው። እነዚህም አካላት ባዕድ አስተምህሮን ያስተምራሉ፤ ሥልጠናም ይሰጣሉ፤ ካህናቱን ሳይቀር በእነርሱ መንገድ እንዲጓዙ ጥረት ያደርጋሉ፤ ካህናቱም ጉዳዩ ይመለከተዋል ለሚሉት አካል ሁሉ ችግሩ እንዲስተካከል በየጊዜው ይጮሃሉ። እኔም ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ካህናትንም ሆነ ምእመናንን እየመከርኩ፣ እያጽናናሁ እንዲሁም እያስተማርኩ እገኛለሁ። ሰዎች በፈቃዳቸው ተሰባስበው የመንግሥትን ፈቃድ ካገኙ የራሳቸውን አዲስ ሃይማኖት ሊመሠርቱ ይችላሉ። እሱ ችግር የለውም፤ ምክንያቱም ሰው የመሰለውንና ያመነበትን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ መከተል ይችላልና። ነገር ግን በእኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ ሌላ የተለወጠ ሃይማኖት እመሠርታለሁ ማለት ግን አይቻልም፤ ወንጀልም ነው። በዚህ ሀገረ ስብከት የተፈጠረው ችግርም ይኸው ነው። የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ችግር ለረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ እኔም ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሪፖርት አቅርቤአለሁ። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም በቅርቡ ጉዳዩ መፍትሔ አግኝቶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቀደመ  አስተምህሮዋ ትቀጥላለች፤ ልማቷም ይፋጠናል ብዬ አስባለሁ። 

ብፁዕነታቸው ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በሀገረ ስብከታቸው ላይ እያጠፉት ባለው ጥፋት በካህናትና በበርካታ ምእመናን ዘንድ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል። በጥንታዊው ገዳም ዲማ ጊዮርጊስን ጨምሮ በጉንደ ወይንና በሌሎች አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በሚያስተምሩበት ወቅት ከእውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ የሆነውን በማስተማራቸውና የሥነ ምግባር ግድፈት ከማሳየታቸው ባሻገርም በሕዝቦች መካከል ቁርሾና መለያየትን በሚሰብኩበት ወቅት ማስጠንቀቂያ የሰጣቷቸውን ፖሊስ ሳይቀር በመገላመጥና ሕዝቡ ጥቃት እንዲያደርስ የማነሣሣት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል። ሀገረ ስብከቱ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ያለበት በመሆኑ በርካታ ካህናትና መምህራነ ወንጌል ከአገልግሎታቸው ያለ በቂ ምክንያት ታግደዋል፤ ተሰናብተዋልም። ለመታገዳቸው ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው ደግሞ ‹‹የቅባት እምነትን ካልተቀበላችሁ” የሚል ነው። 

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ ክፍል ችግሩ እንዲፈታ እያደረጋችሁ ላላችሁት አስተዋፅኦ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። እኔ ደብዳቤ ከመጻፍ አልፌም ገና ክስ እመሠርታለሁ። ለሃይማኖቴ እስከመጨረሻው ድረስ እታመናለሁ። ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከዲቁና እስከ ጵጵስና አስተምራ ኮትኩታ ለዚህ ያበቃችኝ ቤተ ክርስቲያን ችግር በገጠማት ወቅት እርሷን ከችግር ለማዳን አስፈላጊውን ሁሉ አደርጋለሁ። ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊትና ሐዋርያዊት የሆነች መሰልና ወደር የሌላት፣ በሥርዓቷ፣በቅርሶቿና በቀደምትነቷ ዓለም የሚቀናባት እንዲሁም መርምሮ ያልደረሰባት ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ካላት ዕውቅና ባሻገር በየጊዜው በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ጭምር ካላት የጥንታዊነት ባሕርይ የተነሣ መጀመሪያ በሥርዓተ ጸሎት እንድትከፍት ይደረጋል። ስለዚህም ዓለም አቀፍፋዊ ክብር ያላት ቤተ ክርስቲያናችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት ማንኛውም ሰው ዝም ሊል አይገባም፤ ይሉኝታ ሊኖረንም አይገባም፤ ችግሩን በፍጥነት ማስተካከል ይኖርብናል። 

ስምዐ ጽድቅ፡- በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በተፈጠረው ችግር መነሻነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ ያገኙት ምላሽ ምንድን ነው? 

በፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- ደብዳቤውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ካስገባሁ በኋላ ተሰብስበው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሰጡ ነግረውኛል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ቶሎ መፍትሔ እስካልተሰጠው ድረስ ቤተ ክርስቲያንን ከጥፋት ለመታደግ አቅሜ የፈቀደውንና ማድረግ ያለብኝን ሁሉ  አደርጋለሁ። 

ጉዳዩ እኔን ብቻ ሳይሆን መላው ሕዝበ ክርስቲያንና አገልጋዮችን ያስጨነቀ ነው። በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ያለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጣም ተረብሻለች። በሃይማኖታቸው ምክንያት ከአገልግሎት የታገዱና የወር ደመወዛቸው የተቆረጠባቸው በርካታ ካህናትና መምህራን በመኖራቸው ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ነው። ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ችግር ባለባት በዚህ ጊዜ ያሉትን ሊቃውንት ማሳደድና ማንገላታት ተገቢ ካለመሆኑም በላይ አሁን ላይ ያለው ችግር ቤተ ክርስቲያንን ያለ አገልጋይ የሚያስቀር፣ በበረት ያሉ በጎችንም የሚበትን ነው። ቤተ ክርስቲያን አንድ ሊቃውንት ለማፍራት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድበት ይታወቃል። እነዚህን ሊቃውንት ተንከባክቦና ጥያቄያቸውን መልሶ መያዝና በአገልግሎት ተግተው እንዲቀጥሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ጥልቅና ውስብስብ ችግር ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቶ የማያዳግም የርምት ርምጃ ወስዶ ዘላቂ መፍትሔ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። 

ይህ ችግር የዶግማና የሥርዓት ጥሰትን መነሻ ያደረገ ስለሆነ ጉዳዩን በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል። የቀናች ሃይማኖታችን እንዳትጠፋና እንዳትበረዝ ሁሉም የሚመለከተው አካል በትጋት በጋራ ሊሠራ ይገባል። ከዚህ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በእኔ አቅም መደረግ ያለበትን ሁሉ የማድረግ ሲሆን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የጻፍኩትን ደብዳቤ አያይዤ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደብዳቤ እጽፋለሁ። ቤተ ክርስቲያናችን የባዕዳን መነገጃ ተቋም ልትሆን አይገባም። የማይቀየር የማይለወጥ ሥርዓትን ሠርታ ያስቀመጠችና በሥርዓቷም እየተጠቀመችበት ያለች እንዲሁም በውስጧም ዶግማዋንና ቀኖናዋን ተንቅቀው ሚያውቁ ሊቃውንት ያሏት ናትና ሊቃውንቷ  ይህንን ጉዳይ በዝምታ አያልፉትም። ስለዚህ ይህ ባለበት ሁኔታ ለምን በባዕዳን አስተምህሮ ትበረዛለች? እነዚህ የቤተ ክርስቲያናችንን እውነተኛ አስተምህሮ ሊበርዙ የሚሯሯጡ ጥቂት ግለሰቦች ከክፉ ድርጊታቸው ቢቆጠቡ መልካም ነው። 

ስምዐ ጽድቅ፡- የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ችግር ሳይፈታ እስከ ዛሬ ድረስ የቆየበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ? 

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- ችግሩ እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ ቆራጥ ውሳኔ አሳልፏል። ቢሆንም ግን የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመበረዝ በተነሡ ቡድኖች ላይ የተወሰደ ተጨባጭ የርምት ርምጃ የለም። ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ቡድኖች የምትቀጣበት የፖሊስ ኃይልም ሆነ ፍርድ ቤት የሏትም። እነዚህ ኃይሎችም ‹‹ሰው የወደደውን እምነት መከተል ይችላል›› የሚለውን ሀሳብ በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ኃይሎች በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩት ከላይ በተጠቀሰው እሳቤ መሠረት “የሕግ ከለላ አለን ብለው ስለሚያስቡ” ነው። ርግጥ ነው ሰው የወደደውን ሃይማኖት የመከተል መብት አለው ነገር ግን በእኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ የቤተ ክርስቲያንን ዕውቀትና ንብረት እየተጠቀሙ ከሆነ ግን ከወንጀል በላይ ወንጀል ነው። ችግሩ ከፍቶ በመላው ጎጃም ያሉትን ሕዝበ ክርስቲያኖች እንዳያጠቃ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ውሳኔዎችና ውግዘቶች ተላልፈዋል። በዚህ ሳቢያ ችግሩ የረገበ ይመስልና ከጊዜ በኋላ ደግሞ አጥፊ ቡድኑ አይዞህ ባይ ሲያገኝ የቅሳጤ ሥራውን መልሶ ይጀምራል።

ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?

 በፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- ሃይማኖታችንን ሳትበረዝና ሳትከለስ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለበት። የሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነት እንዲጠበቅና በሃይማኖት የተነሣ ጠብና እልቂት እንዳይኖር ሁላችንም የየድርሻችን ልንወጣ ይገባል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን የባዕዳን አስተምህሮ እንዳያጠቃት ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ አለብን። 

ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን ለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ። 

በፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፤ ተባረኩ።

Read 888 times