Saturday, 15 May 2021 00:00

“ ራስን መከላከል የጦርነት አዋጅ አይደለም” “ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በሀገራዊ ፖለቲካ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ መምከርና ማስተማር አለባት” ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ ክርስቶስ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ክፍል አንድ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ተደጋጋሚና ሁሉን አቀፍ የሆነ ጥቃት ሲፈጸምባት ቆይቷል። እየተፈጸመባት ያለውን ተደጋጋሚ ጥቃት በሆደ-ሰፊነት ከማለፍ ውጭ በጠላቶቿ ላይ የአፀፋ ርምጃ ልውሰድ ጉዳቱንም ለዓለም ላሳውቅ ሳትል ጉዳቷ እንደተዳፍነ ዘመናትን ተሻግሯል። ጠላቶቿም ከጊዜ ወደ ጊዜ የልብ ልብ እየተሰማቸው በማናለብኝነት በበደል ላይ በደል ይጨምራሉ። ጉዳቷን የሚቀንሱ ልትሠራቸው የሚገቡ የውስጥና የውጭ ጉዳዮች እንዳሉባት ቢታወቅም እየደረሰባት ያለውን ጥቃት በቅጡ ገልጾ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳት የሚያግዛትን አሠራር ቤተ ክርስቲያኗ ባለመዘርጋቷ ከገጠማት ፈተና በቶሎ ለመውጣት ተቸግራለች። ይህ ደግሞ በዋናነት የሚዲያ አጠቃቀሟ ደካማ መሆንና የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ያለመመሥረቷ ውጤት ነው።  ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ አቋቁማ እስካሁን ድረስ የተወሰነ እንቅስቃሴ እያደረገች ቢሆንም የታሰበውን ያህል እየሠራ ነው ለሚለው ግን ጥያቄ ያስነሳል። የሚዲያውን ድክመት የሕዝብ ግንኙነት ተቋምን በማቋቋም ማካካስ እንደሚቻልም ከተለያዩ አሠራሮች መረዳት ይቻላል። ይህንን ቤተ ክርስቲያኗ የተረዳችው በሚመስል ሁኔታ በቅርቡ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያን አቋቁማለች። የተቋቋመውን የሕዝብ ግንኙት መምሪያ የሥራ ሂደትን እና የቤተ ክርስቲያኗን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ከሆኑት ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ ክርስቶስ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው  አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።  ስምዐ ጽድቅ፡- የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው አመሠራረትና የአገልግሎት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ይግለጹልኝ? ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ክርስቶስ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንደ አዲስ የተቋቋመው ከሦስት ወራት በፊት ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ትኩረት ሰጥተን ተቋሙን የማደራጀት ሥራ ሠርተናል። ቢሮዎች በጥሩ ሁኔታ ተደራጅተዋል፤ የዋና መምሪያ ኃላፊ፤ የምክትል መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የጸሓፊ ቢሮዎች ተስተካክለው ተዘጋጅተዋል። ሁሉም ቢሮዎች በተሟላ ቁሳቁስ ተደራጅተዋል። የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ከተቋቋመ በኋላም ሁሉም አህጉረ ስብከት የራሳቸውን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዲያቋቁሙ በተላለፈው መመሪያ መሠረት እንዲያቋቁሙ እና ያቋቋሙትን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያለበትን ሁኔታ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተደርጓል። በደብዳቤ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት እስካሁን ድረስ አሥራ ስድስት አህጉረ ስብከት ምላሽ ሰጥተዋል። የቀሩ ሌሎች አህጉረ ስብከትም ያቋቋሙትን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እስከ ጥቅምት የ፳፻፲፫ ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በሪፖርት አሳውቀዋል። ከዚህ በኋላ የሃምሳ አራቱ አህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ላይ ሥልጠና የሚሰጣቸው ይሆናል። ሥልጠናው የሕዝብ ግንኙነት መመሪያና አሠራር ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። ሥልጠናውን የወሰዱ የመምሪያ ኃላፊች ወደየሀገረ ስብከቶቻቸው ሲመለሱ በወረዳና በአጥቢያ ደረጃ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያን ያቋቁማሉ። በወረዳና በአጥቢያ ላሉ አገልጋዮችም ተመሣሣይ ሥልጠና ይሰጣሉ። በቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነትና በአጥቢያዎች መካከል የተጠናከረ የግንኙነት መረብ ይዘረጋል። ይህ የግንኙነት መረብ የመረጃ ልውውጡና ፍሰቱ የተጠናከረ እንዲሆን ያግዛል። ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች በተዘረጋው የመገናኛ መረብ አማካይነት እንድንለዋወጥ ይረዳል። ስለሆነም የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ አጥቢያ ድረስ መዘርጋት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫችን ይሆናል። መመሪያው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ለመቆጣጠር፤ የቅርብ ክትትል ለማድረግና በየአህጉረ ስብከቱ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በአጭር ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት የሚያግዝ አሠራር ይኖረዋል። ለሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ግብዓት ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰቡ ጉዳዮች ሁሉ  በመምሪያው በተዘረጋው መረብ አማካይነት በየሳምንቱ የምንለዋወጥ ይሆናል። የመምሪያው አገልግሎት እጅግ የተሣካና የተፋጠነ እንዲሆን በዓለማችን አሉ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሁሉ እንጠቀማለን። የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የተሻለ ተግባር እያከናወን እንገኛለን።  ስምዐ ጽድቅ፡- ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት የአሠራር ሂደትን በትክክል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ለመተግበር ማስተባበሪያው ምን ያህል ዝግጁ ነው? ሊቀ ሥዩማን እስክንድር፡- የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ስለተቋቋመ ብቻ መደበኛ የቢሮ ሥራ ብቻ አድርገን አናየውም። መምሪያው በዋናነት የቤተ ክርስቲያን አንደበት ነው የሚሆነው። ትልቁ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ክፍልም ነው የሚሆነው። መምሪያው የቤተ ክርስቲያኗን ታላቅነት በሚመጥንና በተቀመጡ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሂደቶች የሚመራ ይሆናል። የመተዳደሪያ ደንቡም ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የሕዝብ ግንኙነት መመሪያዎችን መሠረት ያደረገ ሲሆን ደንቡ ተዘጋጅቶ በቋሚ ሲኖዶስ ጸድቆ ለአገልግሎት እንዲውል ለማስተባበሪያው ገቢ ተደርጓል። መመሪያውን መሠረት አድርጎም የማስፋትና የማደራጀት ብርቱ ሥራ ይጠይቃል። ይህ ሥራም እጅግ ፈታኝና ከባድ ይሆናል፤ በተወሰነ የአገልጋይ አቅምም የሚሠራ አይሆንም። የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው በደንብ እንዲጠናከር ከአባቶች ጀምሮ የሁሉን ባለድርሻ አካል ርብርብ ይጠይቃል። የበጀት ድጋፍና የተባባሪ አካላት እገዛ ያስፈልገዋል። ተባባሪ አካላት ተቋሙን ለማሳደግ የራሳቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በዚህ ረገድ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በጋራ  እየሠራን ነው። ከማኅበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን። በተለይ የቁሳቁስና የሥልጠና ድጋፍ በዋናነት ይደረግልናል ብለን እናምናለን። ተቋሙን ለማሻሻል ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንዲሁ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ይሆናል።  ለሦስት ወራት ያህል ማስተባበሪያውን የማደራጀት ሥራ ላይ ትኩረት አድርገን ስንሠራ የቆየን ቢሆንም ከሥር ከሥር ግን የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ናቸው ብለን ያመንባቸውን ተግባራት ስናከናውን ቆይተናል። ለሕዝበ ክርስቲያኑ እውነተኛና ታማኝነት ያለውን መረጃ ስናደርስ ቆይተናል።  ስምዐ ጽድቅ፡- የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያው በሰው ኀይል ሲደራጅ ምን ምን ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገባል ይላሉ? ሊቀ ሥዩማን እስክንድር፡- የሰው ኃይሉ ሲደራጅ የግድ በሕዝብ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ወይም ማስተርስ ዲግሪ ያላቸውን አጥቢያ ላይ ወይም በሌሎች መምሪያዎች ላይ በኃላፊነት እናስቀምጣለን ማለት አደለም። የቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የሚደራጀው ቤተ ክርስቲያኗ ባላት የሰው ኃይል አቅም ልክ ሲሆን ትምህርታቸውን በተቀራራቢ የትምህርት ዘርፍ ያጠናቀቁና በቤተ ክርስቲያኗ ባሉ መንፈሳዊ ኮሌጆች ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ወንድሞች እና እኀቶች በመምሪያው ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው የሚያገለግሉ ይሆናል። ይህ ማለት በዘመናዊና በመፈንሳዊ ትምህርት በቂ እውቀት ያላቸውና መሠረታዊ የኮምፒውተር ክህሎት ያካበቱ ሊሆኑ ይገባል። የሰው ኃይሉም በነዚህ መስፈርቶች የሚደራጅ  ይሆናል። ቅጥር ከተፈጸመ በኋላም ተደጋጋሚ የሆኑ የአቅም ማጎልበቻ የሕዝብ ግንኙነት ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የተቋቋመው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በሀገረ ስብከትና በአጥቢያ ደርጃ የሚቋቋሙ መምሪያዎችን የሰው ኃይል፤ የቁሳቁስና የሥልጠና ድጋፍ ያደርጋል።  በአንድ ጊዜ የሕዝብ ግንኙነት ተግባራት ማማ ላይ ለመውጣት የታሰበ ሳይሆን ቀስ በቀስ በማደራጀት ፍጹም ሙያዊ ተግባራት ብቻ የሚከናወኑበት መምሪያ የማድረግ እቅድ ተይዞ ነው ወደ ሥራ የተገባው። ቤተ ክርስቲያኗ በዚህ ሰዓት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዲደራጅ መወሰኗ በራሱ ትልቅ ርምጃ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን ደረጃ በሚመጥን መልኩ መምሪያውን ለማደራጀት ግን ትጋትና ጠንካራ ሥራን ይጠይቃል። የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውን በደንብ በማደራጀት ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግና ፍጹማዊ የሆነ መዋቅራዊ አሠራርን የተላበሰ እንዲሆን  በኛ በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።  
Read 533 times