Wednesday, 24 March 2021 00:00

“ሀገራዊ ምርጫው በብሔርና በሃይማኖት ምክንያት በኢትዮጵያውያን መካከል የተፈጠረውን ቁርሾ የሚያጠፋ ሊሆን ይገባል” ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዶ/ር (የጅቡቲና ድሬደዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኃላፊ)

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
 በዓለማችን ያሉ ብዙ ሀገራት በየአራት ወይም በየአምስት ዓመታት ልዩነት ሀገራዊ ምርጫ ያካሄዳሉ። በየሀገራቱ ያሉ ሕዝቦችም “ይበጀናል ለውጥ ያመጣልናል” ያሉትን የፖለቲካ ድርጅት በካርዳቸው አማካይነት ይመርጣሉ። የፖለቲካ ድርጅቶችም ከምርጫው ጊዜ ቀደም ብሎ “ሕዝብን ያሳምንልናል፤ እንድንመረጥ ያግዘናል” የሚሉትን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም በዐደባባይ ወጥተው ያስተዋውቃሉ። አንዳንዴ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁና በምርጫው አሸናፊ የሆነውን አካል እንኳን ደስ አለህ/ አለሽ ተባብሎ የመለያየቱ ጉዳይ ግን አሳሳቢ ይሆናል። በምርጫ ወቅት የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ ሀብት ንብረት ይወድማል፤ የሀገር ሉዓላዊነትም አደጋ ላይ ይወድቃል። በተለይ በአፍሪካና በአንዳንድ ታዳጊ ሀገራት ሀገራዊ ምርጫ ያለስጋትና ያለፀጥታ ችግር የሚጠናቀቅባቸው ጊዜያት ውስን ይሆናሉ። በሀገራችን ባለፉት አምስት ዙር የተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ለፀጥታ ችግር የተጋለጡ ሆነው አልፈዋል። በምርጫዎቹ ወቅት የሰው ሕይዎት ያለአግባብ የጠፋበት፤ በተለይ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በአንዳንድ ዕብሪተኛ የፖለቲካ ኃይሎች ሥርዓቷ፣ቀኖናዋ፣ዶግማዋ፣ክብሯና መብቷ  የተጣሰባቸው ዓመታትን አሳልፈናል። ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ኃይል በስሑት ትርክት ተነሣሥቶ ቤተ ክርቲያንን “በጠላትነት” በመፈረጅ እውነተኛ አገልጋይ አባቶችና ምእመናን ተሸማቀው እንዲኖሩና በእምነታቸው እንዲያፍሩ ሲደርግ ቆይቷል።   በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ በሀገራችን ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ መርሐ ግብር አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚህ ወሳኝ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በየዐደባባዩ እየዞሩ ፖለቲካዊ አማራጭ ሐሳባቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንም የሀገሪቱ አካል ናቸውና በምርጫው ወቅት ሊኖራቸው ስለሚገባው ድርሻ አስመልክቶ ከጅቡቲና ድሬደዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኃላፊ ከሆኑት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዶ/ር ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ። ስምዐ ጽድቅ፡- በሀገሪቱ ሊካሄድ የታሰበው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በምን ሁኔታ ሊከናወን፣ በምርጫው ወቅትስ ምእመናን ምን ዓይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ? ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ሀገራዊ ምርጫ ማለት ሕዝብን ለማስተዳደርና ለመምራት የሕዝብን እውነተኛ ድምፅ ለማግኘት የሚካሄድ አንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። የሀገራዊ ምርጫ ዋናው ግብ ሕዝባዊ ይሁንታን አግኝቶ ሀገርንና ሕዝብን መምራት ነው። በሀገራዊ ምርጫ ወቅት ገዥው የፖለቲካ ድርጅትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የየራሳቸውን ሐሳብ ለኅብረተሰቡ በመግለጽ የፖለቲካ መንበርን የሚይዙበት ሂደትም ነው። ስለዚህ በሀገራችን ሊደረግ በሂደት ላይ ያለው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን እንመኛለን።  ምርጫው የኢትዮጵያዊነትን ዕሴት፣ አንድነት፣ ፍቅርንና መተሳሰብን የሚሸረሽር ሆኖ መከናወን የለበትም። የፖለቲካ ድርጅቶች አለን የሚሉትን አማራጭ ሐሳባቸውን ለኅብረተሰቡ በመግለጽ በፍትሐዊነት የመንግሥትን መንበረ ሥልጣን የሚይዙ፤ የሀገርን ሰላምና ዕድገት ለማሻሻል ጥረት የሚያደርጉ መሆን አለባቸው። ሀገራዊ ምርጫው በብሔርና በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት በኢትዮጵያውያን መካከል የተፈጠረውን ቁርሾና የኢኮኖሚ ውድቀት የሚያስወግድ ምርጫ ሊሆን ይገባል። በሕዝቦች መካከል ጠብ የሚዘሩና መለያየትን የሚሰብኩ አካላት ጭምር ሥርዓት የሚይዙበትና ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ኃያልነቷ ተመልሳ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ብቻ ሳትሆን ለሌሎች ክፍላተ አህጉር ምሳሌ የሆነ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድባትም የሁሉም ፍላጎት ሊሆን ይገባል።  የሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ተከብሮ ሰው በፈለገው ቦታ ሆኖ  ማምለክ የሚችልበት ዘመን  እንዲመጣ እንመኛለን። በተለይ ከዚህ ቀደም የነበረው መንግሥታዊ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን የተበደሉበትና የተገፉበት ሥርዓት ነበር። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በስሑት ትርክት ተነሣሥስተው ቤተ ክርስቲያንን “በጠላትነት” ከመፈረጅ ባሻገር “የጭቆና፣ የድህነትና የኋላ ቀርነት” ምሳሌ አድርገው ሲያቀርቧት ይስተዋሉ ነበር። ይህ ግን የተሳሳተ፣ ቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ለወገን የከፈለችውን ታላቅ ዋጋ  የካደ ልዕልናዋንም ያላከበረ ትርክት ነው።  በመጭው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ተወዳድረው የሚያሸንፉ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳሳቱ ትርክቶችን የሚያርሙና ቢቻል በስሑት ትርክት ምክንያት ላለፉት ፵ ዓመታት ጉዳት የደረሰባትን ቤተ ክርስቲያን የሚክሱና ይቅርታ መጠየቅ የሚችል ቅን ልቡና ያላቸው መሆን አለባቸው። በዚህ ዘመን ያለን ሕዝበ ክርስቲያንም የስሑት ትርክት ማወራረጃ መሆን እንደሌለብን ጠንቅቀን በማወቅ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያበቃንን ካርድም በመውሰድ በግብታዊነት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያናችንና ለምእመናን የሚጠቅመውን የፖለቲካ ድርጅት መምረጥ ይጠበቅብናል።  በሀገራችን ለምርጫ ውድድር የቀረቡት የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ፖለቲካዊ አማራጭ ሐሳብ ምእመናን በትክክል መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ከመምረጥ ባሻገር በምርጫው ወቅት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማገዝና ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። የዘመኑ አሰላለፍ መቀየሩን አውቀን ህልውናችንን ሊያስጠብቅልን የሚችለውን የፖለቲካ ድርጅት መምርጥ የማንችል ከሆነ ዘላለም የችግር ሁሉ ገፈት ቀማሽ፤ አቤቱታ አቅራቢና ኀዘንተኞች እንሆናለን። ለኀዘናችን ማስታገሻ ስንልም በእምነትና በምግባር ለማይመስለን መንግሥት “ተገፋን” ብለን ድምጻችን ስናሰማ ለሀገር ከምናበረክተው ድርሻ እንወጣለን።  ስምዐ ጽድቅ፡- ቤተ ክርስቲያን የተከፈተባትን ስሑት ትርክት ለማረም፤ የቤተ ክርስቲያንንና የምእመናንን ደኅንነትም ለማስጠበቅ ስለ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ነው?  ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡-  ቤተ ክርስቲያንን በስሑት ትርክት የመወንጀል ምንጩ ምዕራባውያን ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗንና በአድዋ ድል ላይ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ስለሚያውቁ ያን መበቀል ይፈልጋሉ። ለሀገር ውስጥ ፀረ-ኦርቶዶክስ ኃይላት የገንዘብ ድጎማ በማድረግ ጭምር ቤተ ክርስቲያንን በስሑት ትርክት የመወንጀል ሥራ ይሠራሉ። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማስተዋል አለባቸው፤ የስሑት ትርክት ምንጩ የትና እነማን መሆናቸውን በመለየት ለእርሱ የሚሆን ስልት መንደፍ አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ግንባታና አንድነት ትልቅ ሚና እንደተጫወተች ምእመናንም ሆኑ የመንግሥትን የሥልጣን መንበር የሚይዙ አካላት ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል። ሆን ተብሎ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲነዙ የነበሩ የሐሰት ትርክቶች የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት ከግምት ውስጥ ያላስገቡና የኢትዮጵያንም ሉዓላዊነትና ነፃነት ለመናድ የሚቀነቀኑ ሴራዎች ነበሩ።  የቤተ ክርስቲያን ኃያልነትና ለሀገር ያበረከታችው አስተዋፅኦ አንድ ቀን ይገለጣል፤ ዓለምም ዐይኑን ገልጦ ልቡናውንም ከፍቶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ ልቡ ይቀበላታል። ቤተ ክርስቲያን ፍትሐዊነትን ያስተማረችና ድኃ እንዳይበደል ፍትሕ እንዳይጓደል ጠንክራ የሠራች ናት። ቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ሕዝብ ጠቃሚ የሆነችና ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝብም የነፃነት ፋና ወጊ የሆነች እንዲሁም ለዓለም ሕዝብ ታሪክን፣ ቅርስንና ሃይማኖትን ጠብቃ ያቆየች ናት። የሀገራችን የማኅበረሰብ አንቂዎችም ሆኑ የፖለቲካና የታሪክ ምሁራንም ይንን ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ተረድተው ለእውነት መቆም አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ የሐሰት ትርክት ሰለባ ብትሆንም ክብሯና ለሀገር የምታበረክተው ድርሻ አይቀንስም። ሰዎች ዓይናቸውን ገልጠው እስኪያዩ ድረስ እውነቱን በተገቢ መንገድ ማስረዳት የእኛ አባቶች ድርሻና የምእመናን ሊሆን ይገባል። ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያን የነበራትን ሀገራዊ ድርሻ ለማስቀጠል መጪው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሓዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻዋን ትወጣለች፤ ምእመናንዋም በድጋሜ ዋጋ እንዳይከፍሉ  በምርጫው ወቅት በጥንቃቄ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ትመክራለች።  ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ሕልውና  አስመልክቶ በሀገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ውይይት አለ? ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- እስካሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ሕልውና አስመልክቶ በሀገሪቱ ከሚገኙ  የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ምንም ዓይነት ውይይት የለም። ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ድርጅቶችን ጠርታ ማነጋገሩ ጠቃሚ ነው ብላ ባለማመኗ ውይይት አላደረገችም። ነገር ግን በምርጫ ወቅት የምርጫ ሕጎችና ደምቦች እንዳይጣሱ፣ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድምና የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት የሚሸረሽሩ ጉዳዮች እንዳይከሠቱ ቤተ ክርስቲያን የመካሪነትና የአስተማሪነት ድርሻዋን በሚገባ ትወጣለች።  የፖለቲካ ድርጅቶች የሕዝብን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ መጭውን ምርጫ እንዲያካሂዱ ቤተ ክርስቲያን ትመክራለች። ለምእመናንም ያመኑበትንና መብታቸውንና ጥቅማቸውን ሊያስከብርላቸው የሚችለውን የፖለቲካ ድርጅት እንዲመርጡ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ ታስተላልፋለች፤ እንዲሁም በምርጫው ወቅት ከሁከትና ብጥብጥ እንዲቆጠቡና ከግርግር እንዲርቁ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች።  ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያን ልጆች በሀገሪቱ የፖለቲካ ሱታፌ ውስጥ የፖለቲካ ውክልና የማያገኙት ቤተ ክርስቲያን  የፖለቲካ ተሳትፎን “በመጥፎ ስላ ስለምትመለከተው ነው” ይባላልና በዚህ ላይ ምን ሐሳብ አለዎት?  ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ይህ ሐሳብ ከእውነታው ጋር በተቃርኖ የቆመ ነው። በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ ከነበሩ መንግሥታት ጋር ትወግን ነበር ይባላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆቿ የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖራቸው ክልከላ አድርጋለች ይባላል። እውነታው ግን ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳያደርጉ አልከለከለችም፤ ከልክላም አታውቅም። የፖለቲካ ተሳትፎንም በጎ ባልሆነ ዕይታ ቃኝታ አላስተማረችም። ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎን በራሳቸው ምክንያት ሸሽተው ‹‹ቤተ ክርስቲያን ናት የከለከለችን›› ብሎ ማቅረብ ፍጹም ስሕተት ነው። ከዚህ በኋላ ሁላችንም ፖለቲካን የምናይበት ዕይታ የተስተካከለ መሆን አለበት። ፖለቲካን አስፈሪ በሆነ መንገድ መመልከት መቆም አለበት።  በአሁኑ ሰዓት መብትንና ጥቅምን ለማስከበር የግድ የፖለቲካ ተሳትፎን የሚጠይቅ ወቅት ላይ እንገኛለን። ቤተ ክርስቲያን እጅግ ሊቅ የሆኑ ልጆች አሏት፤ እነዚህ ራሳቸውን ሳይደብቁ በዐደባባይ በመውጣት በፖለቲካ ተወክለው የቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን መብትና ጥቅም ሊያስከብሩ ይገባል። ዕውቀታቸውን ለሕዝባቸው ሰላምና ልማት ሊያውሉት ያስፈልጋል። የሀርን ልማት፣ አንድነትና ሰላም የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ርዕዮተን ዓለም ይዘው በመቅረብ ተመራጭ የፖለቲካ ሰዎች እንዲሆኑ ጠንክረው መሥራትም ይጠበቅባቸዋል።  አንዳንድ የዓለማችን ሀገራት ‹‹ክርስቲያናዊ የፖለቲካ ድርጅት›› መሥርተው የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ሁሉ የእኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችም የሀገሪቱን ሕግ መሠረት አድርገው ኦርቶዶክሳዊ የፖለቲካ ድርጅት መሥርተው እስከ መንቀሳቀስ ደረጃ መድረስ አለባቸው። በአንዳንድ የዓለማችን ሀገራት ማለትም በኖሮዊ፣ ጀርመን እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት  ካህናት አባቶች በምርጫ ተወዳድረው አሸንፈው የሀገር መሪ እስከመሆን  ደርሰዋል። በእኛ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ካህናት በፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ባይፈቀድም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን ተሳታፊ መሆን አለባቸው። ካህናት አባቶች ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ትኩረት እንዲሰጡ ከማድረግ ውጪ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ እንዲሳተፉ አትፈቅድም። የቤተ ክርስቲያን አስታራቂነት ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ ልጆቿ ፓርላማ ውስጥ ገብተው በሀገሪቱ በሚወሰኑ ማንኛውም ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ ታግዛለች። ይህ ካልሆነ ግን በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ላይ የሚወሰኑ የፖለቲካ ውሳኔዎችን እንደማንኛውም ገለልተኛ አካል በቴሌቭዥን ከማየት የዘለለ ዕድል አይኖራቸውም።  መንግሥት ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሃይማኖት የሚወስነው ውሳኔ የሚኖር ከሆነ በፓርላማ ውስጥ ተገኝተው የሚከራከሩና ሐሳብ የሚሰጡ ተወካዮች ከሌሉ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንቱ ጉዳቷ የበለጠ በዚህ ዘመን ትጎዳለች። በራስ ድክመትና ቸልተኝነት ቤተ ክርስቲያንን መውቀስ ግን ተገቢ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ መሪዎቿን እየቀባች ስታነግሥ ኖራለች። በኋላ ላይም ርዕዮተ ዓለሙ ተቀይሮ ስትገፋ ቆይታለች።  አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጫናውን መቋቋም ሲያቅታቸው ክርስትናን ሳይቀር በድብቅ ማስፈጸም መጀመራቸውን እናቀውቃለን። ከዚህ በኋላ የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቤተ ክርስቲያን ስትገፋ፣ ክብሯና መብቷ ሲገፈፍ በታዛቢነት ማየት የለባቸውም። ሊሟገቱላት፣ ሊከራከሩላት ክብሯንና መብቷን ሊያስጠብቁላት ይገባል።  ቤተ ክህነቱን ባሉባልታ ከመተቸት ይልቅ የፖለቲካ ተሳታፊ የሆኑ ምእመናን የራሳቸውን ድርሻ መወጣት፤ የቤተ ክህነቱን ጉድለት ደግሞ እንዲስተካከል የተጠናና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ አስተያየት መስጠት አለባቸው። ልጆቻችን ከአባቶች ጋር አላስፈላጊ የሆነ ንትርክ ከማድረግ ወጥተው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን በጠቅም ከሚችል የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ መግባት አለባቸው። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በዚህ ወቅት በሚኒስቴር ደረጃና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ጭምር በከፍተኛ ኃላፊነት እያገለገሉ ያሉ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አሉ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከፖለቲካ ውክልና እንዲርቁ አታደርግም።  በተለይ በአገልግሎት ተቋማት በኃላፊነት ላይ ያሉ ልጆቻችን እምነታቸውን በነፃነት የማምለክና የመግለጥ ድክመት አለባቸው። በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ በእምነታቸው በማፈር በመሸማቀቅ እንዲሁም ኦርቶዶክስ መሆናቸው እንዳይታወቅባቸው ሆነው ሥራን የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ኦርቶዶክሳዊነታቸውን ሳይደብቁ በኩራት አውጥተው ገልጠው የሚሠሩም በርካቶች ናቸው። ቤተ ክርስቲያንም እንደነዚህ ያሉ ልጆቿን በደንብ ታበረታታለች፤ በቅርበትም ትከታተላለች፣ ትመክራለች፣ ታስተምራለችም። በሌላ የእምነት ተቋማት ሥር ያሉ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች በዐደባባይ ሳይፈሩ ሳይሸማቀቁ እምነታቸውን ያስተዋውቃሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ ወደጎን ትተው ለሚከተሉት እምነት ያድራሉ። የእኛ ቤተ ክርስቲያንና ልጆቻችንም ከእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ትምህርት መውሰድ አለባቸው።      ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻም ቀረ የሚሉት ነገረ ካለ? ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- ሀገራዊ ምርጫ ሲባል ሀገርን የሚወክልና የሀገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስን በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብተው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ድርጅት ለመምረጥ መዘጋጀት አለባቸው። ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን የፖለቲካ ድርጅት ከምርጫ በፊት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ሀገራችን መልካም ስሟና አንድነቷ ተጠብቆ እንድትዘልቅ እንፈልጋለን። ሁሉም ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን እንመኛለን። ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ባሉ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ የሚሠራባትና የሃይማኖት ነፃነትን የምታከብር እንድትሆንና መጪው ምርጫ ፍትሓዊና ተአማኒ እንዲሆን መሥራት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል።  ገዥው መንግሥትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመልካም ዕይታ እንዲያዩና ለሀገርና ለወገን ያበረከተችውን ድረሻ እንዲረዱ እናሳስባለን። የፖለቲካ ድርጅቶች ቢሆኑ ቤተ ክርስቲያን ማንንም እንዳልበደለችና እንዳልጨቆነች መረዳት ይኖርባቸዋል። ከአርባ ዓመታት ወዲህ ሆን ተብሎ የጭቆና ማዕከል ስትደረግ እንደቆየች መገንዘብ ተገቢ ነው። ቤተ ክርስቲያን  በሀገራችን በኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ባልነበረበት ወቅት ፊደል አስቆጥራለች፤ ታሪክ አቆይታለች፤ ሥነ ጥበብን፣ መድኃኒት ቅመማን፣ የዘመን አቆጣጠርን አስተምራለች። በሀገራችን አራቱም አቅጣጫዎች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አሻራዎች አሉ፤ እነዚያ ሁሉ የሀገር ሀብት ናቸው።  በሀገራችን ውስጥ እተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲካሄዱ የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ባለመቀበል፤ ከቤተ ክርስቲያን ጎን በመቆም ለማረም ጥረት ቢያደርጉ መልካም ነው። ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስሕተቶች ድጋሜ እንዳይፈጸሙ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በምርጫው ወቅት ብጥብጥ እንዳይፈጠር ከዚህም ጋር ተያይዞ  በወገኖቻችን ላይ ሃይማኖት ተኮር ጥቃት እንዳይፈጸም የፀጥታ አካላት ቀድመው ሊሠሩ ይገባል። በአንዳንድ አካባቢዎች ምርጫን ጨምሮ የፖለቲካ ለውጥ ሲካሄድ ቤተ ክርስቲያንና ኦርቶዶክሳውያን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ከዚህ ቀደም ካየናቸው ተግባራት እንገነዘባለን። በዚህ ወቅት ጥቃት የሚያደርሱ አካላት በስሑት ትርክት የተሞሉና ‹‹የእኔ›› የሚሉትን ሃይማኖት በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ ለመጫን የሚያልሙ ኃይላት ናቸው። ይህ ተግባር እንዳይፈጸም መንግሥት ከወዲሁ የሀገራችንን ችግር ስስ ብልት ለይቶ በማወቅ ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ምርጫ ቦርድም የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል ማድረግ ያለበትን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል።   ስምዐ ጽድቅ፡- አባታችን  ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ  ውድ ጊዜዎትን ሠውተው ለቃለ መጠይቃችን ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን። ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ፡- እኔም አመሰግናለሁ።      
Read 521 times