Monday, 05 October 2020 00:00

ዓይን የላቸውም ዓይን ያለንን ግን ይመሩናል፣እጅ የላቸውም ያሰሩናል . . .  ክፍል ሁለት

Written by  ከቆየ እትም የተወሰደ

Overview

በ፲፱፻፹፰ዓ.ም የተሠራው የዳንዴ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ታሪካዊ ቢሆንም የአካባቢው ምእመናን በተለያዩ ምክንያቶች ወደሌሎች ከተሞች በመሔዳቸው ያሉትም ባለባቸው ችግር በሚገባ ሊንከባከቡት ባለመቻላቸው በመፈራረስ ላይ ይገኛል፡፡ የሚያስፈልገው እርዳታ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሀገረ ስብከቱ አስታውቀናል፡፡ አቅማችን በፈቀደ ግን እየረዳን ነው፡፡ ለምሳሌ የነበሩት ካህን ደሞዛቸውን ሊያገኙ ባለመቻላቸው ወደሌላ ከተማ ሔደው ስለበረ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ወደቦታው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም አንድ ሌላ ካህንና ዲያቆን በማምጣት ደሞዛቸውን እየከፈልን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡   ሌላው የአቡነ ኤውስጣቴዎስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በሸበዲኖ አካባቢ ከአረንጃ መድኃኔዓለም ቀጥሎ በ፲፱፻፳፮ ዓ.ም የተሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፲፱፻፷፮ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ወቅት ይረዱት የነበሩት ባላባቶች በመበተናቸው ችግር ላይ ወድቋል፡፡  ይህ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳው ተሰነጣጥቆ ስለበረ ተለስኖ ቀለም ተቀብቷል፤ ወለሉም ዙሪያው ውኃ ልክ ተሠርቶለት ሊሾ ሆኗል፡፡ የመቅደሱም ጣራ ስለሚያፈስ ጥላ ተዘርግቶ ነበር የሚቀደሰው ስለዚህም የመቅደሱን ቆርቆሮ አስለውጠናል፡፡ አዲስ የታቦት መንበርም አሠርተናል፡፡ የተጓደሉ አልባሳትንና ንዋያተ ቅድሳትም እንዲሟሉ አድርገናል፡፡ የልዑካኑም አልባሳት የተሟሉ ባይሆንም ለአንድ ካህን እየከፈልን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡  የአቡነ ኤውጣቴዎስን ገድልም ካለበት ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል በማፈላለግ በብራና አጽፈን አስመጥተናል፡፡   

 

በሀገረ ሰላም የሚገኘው ታሪካዊውን የሁርሶ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምም እየረዳን ነው፡፡ በ፲፱፻፹፰ዓ.ም ሽፍቶች የአካባቢውን ሕዝብ ሲገድሉና አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥሉ ይህንንም ገዳም ለማፍረስ ሞክረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የነብር መንጋ ስላሳደዳቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በተለይ አንድ ነብር ጽላቱ ወደ ሀገረ ሰላም ማርያም ሲሄድ እዚያው ድረስ አጅቦ አንደ አደረሰውና በኋላም ጽላቱ ሲመለስ ቤተ ክርስቲያኑ ሲከፈት በመቅደሱ ውስጥ ተኝቶ መገኘቱን ሲሔድም ሰላምታ ሰጥቷቸው መሔዱን ካህናቱና የአካባቢው ምእመናን መስክረዋል ያ ነብር አሁንም በየቀኑ ይመጣል፡፡ 

ይህ ቤተ ክርስቲያን እስከ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ ችግሩን የተመለከቱ የአካባቢው ምእመናን በገለጹልን መሠረት ለ፲፱፻፹፱ ዓ.ም ፍልሰታ ማስቀደሻ የሁለት ካህናት፣ የሦስት ዲያቆናት አስፈላጊ ወጪዎችና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች በማሟላት አሥራ ስድስቱንም ቀናት ሰዓታት ተቆሞና ተቀድሶ በዓሉ ተከብሯል፡፡ ከዚያም አንዱን ካህንና ሁለቱን ዲያቆናት ቀጥረን እያገለገሉ ነው፡፡ 

ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ጀምሮ ወጥቶና ነግሦ የማያውቀውንም ታቦተ ሕግ መጋቢት ፭ ቀን፲፱፻፺ዓ.ም የንግሥ በዓሉን አክብረናል፡፡ ወደሌላ የእምነት ድርጅቶች ሔደው የነበሩ ምእመናንም በየጊዜው በሚላኩት መምህራን በተሰጠው ትምህርት እየተመለሱ ነው፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤትም ተቋቁሞ አበረታች እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ 

ቀደም ሲል ተፈጥሮ በነበረው ግርግር በየመንደሩ ተቀምጠው የነበሩ ብዙ ንዋያተ ቅድሳትና አልባሳት ጠፍተዋል፡፡ ያሉትም በመጎዳታቸው አገለግሎት መስጠት አይችሉም፡፡ ይህን ችግር ለማቃለል ለጊዜው የአምስት ልዑካን ልብስ ገዝተን አስገብተናል፡፡ ችግሩ ግን በቀላል የሚወገድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጻሕል፣መቁረርት፣ መጎናጸፊያም፣ መጻሕፍትና የመሳሰሉት አልተሟሉም፡፡ ሕንፃውም የሲሚንቶና የባለሙያ ችግር ስለገጠመው እንጂ ለመጠገን በዝግጅት ላይ ነን፡፡  በጅምር የቀሩ በሮችንና መስኮቶችንም ለማጠናቀቅ ዕቅድ ይዘናል፡፡ 

ከአዋሳ ብዙም የማይርቀው ሌላው ቤተ ክርስቲያን የጻድቁ የገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በሸበዲኖ ወረዳ በሞርቾ አካባቢ የሚገኘው ይህ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ሲሆን በመቃኞ መልክ የተሠራ ነው፡፡ በመንገድ ዳር የሚገኝ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ‹‹ችግር አይኖርበትም›› እያልን እያለፍነው እንሄድ ነበር፡፡ ውስጡን ስናየው ግን በጣም የተጎዳ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የአካባቢው ምእመናንም ቁጥር ጥቂት ነው፡፡ 

ስለዚህም በግንቦት ፲፱፻፹፱ ዓ.ም የበፊቱን መቃኞ በማፍረስ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ተጀምሮ አሁን ሥራው ወደመጠናቀቁ ነው፡፡ በዚህ ሥራ በአዋሳና በይርጋዓለም  የሚገኙ ምእመናን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ የአቡነ አረጋዊ ጽላት በድርብነት እንዲገባ የቀረበው ሃሳብም የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስን መልካም ፈቃድና ጥረት በማግኘቱ የሕንፃውን መጠናቀቅ በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡ 

በይርጋዓለም የማስተባብራቸው ምእመናንም ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በ፲፱፻፹፱ዓ.ም የካቲት ወር ለጸበል ይርጋዓለም ሔጄ በነበረበት ወቅት የአዋሳውን እንቅስቃሴ የነገርኳቸው አባቶችና ወጣቶች አብረውን ለመሥራት በመፍቀዳቸው በጀመሪያ በአቅራቢያው የምትገኘውን የሺሻ ማርያምን ለማደስ ወሰንን፡፡ ሺሻ ማርያም በይርጋዓለም አካባቢ በዳሌ ወረዳ የምትገኝ በተራራ ላይ የሠራች ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ 

ለትራንስፖርት አስቸጋሪ በመሆኗ ይህች ቤተ ክርስቲያን ለማደስ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁስ በሸክም በማውጣት እናቶች ሳይቀሩ አስተዋጸኦ አድርገዋል፡፡ ብዙ እናቶች አሸዋ በአንስራ እየሞሉ አውጥተዋል፡፡ በዚህም ወለሉ ሊሾ ተደርጓል፣ ተጎድቶ የበረው ግድግዳ ተጠግኗል፡፡ በርና መስኮቶችንም ከከተማ በማስመጣት አስገጥመናል፡፡ የምእምናኑ ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑም አዲስ መንበርና ሙሉ አልባሳት ለማሟላት ተችሏል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱም እየተጠናከረ ነው፡፡  

በሸበዲኖ ወረዳ ወንዶ ጢቃ አካባቢ የሚገኘውን የጋንጌሶ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንም በመርዳት ላይ ነን፡፡ በ፲፱፻፵፰ዓ.ም በመቃኞ መልክ ተሠርቶ ከእርጅና የተነሣ አጋድሎ የሚታይ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ለመግባት እንኳን ያስቸግር የነበረውን ይህን መቃኞ በማፍረስ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቷል፡፡ ሥራው ግን ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡ ኮርኒሰ፣ አጥርና ሌሎችም ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ በሰበካ ጉባኤ እንዲቋቋምና እንዲጠናከር፣ በየሳምንቱ እሑድና በዕለተ ቅዱስ ሚካኤል እንዲቀደስ፣ የነበሩትም ካህን አንድ ብቻ ስለበሩ አንድ ካህንና አንድ ዲያቆን በተጨማሪ ወጪያቸውን በመሸፈን ለማሠራት ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ የይርጋዓለም እንቅስቃሴ አነሣስና አካሔድ ይህን ይመስላል፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- የምትረዷቸው አብያተ ክርስቲያናት ባሉበት አካባቢ የሚገኙትን ምእመናን ስለ አገልግሎታችሁ ምን አስተያየት አላቸው?   

አባ ዜና ገብርኤል፡- የአካባቢው ምእመናን በጣም ነው የሚደሰቱት፡፡ በገንዘብም በጉልበትም ይረዱናል፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ሲያገኙን ያለቅሳሉ፡፡ ችግራቸውን የሚያይ ሰው ይፈልጋሉና ደሰተኞች ናቸው፡፡ 

ለምሳሌ በሲቄ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የምእመናን ብዛት አናሳ ነበር፡፡ በሰንበት እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ ሰው አይገኝም ነበር፡፡ የነበሩት ካህንም ብቻቸውን መታግል ተስኗቸው ነበር፡፡ በኋላ ከእኛ አገልግሎት መጠናከር ጋር ግን ሁሉም ተነሣሱ፡፡ በሚሰጠውም ትምህርት የምእመናን ቁጥር እየበዛ ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤውም እየተጠናከረ ነው፡፡ በሌሎችም ቦታዎች ያለው ሁኔታ የሚያበረታታ ነው፡፡  

ስምዐ ጽድቅ፡- ለምእመናን የሚያስተላልፉት መልእክት አለ? 

አባ ዜና ገብርኤል፡- አዎ ማለት የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ምእመናን የሚደነቁትንና በብዛት የሚታወቁትን ብቻ ሳይሆን በየገጠሩ የሚገኙትን ብዙ ቅርሶችን የያዙትንና በመፈራረስ ላይ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ሊያስታውሱ ይገባል፡፡ በተለይ ወጣቶች በየገጠሩ ለመናፍቅነትና ለሱስ የተዳረጉትን ወንድሞቻችን ፈለግ ተከትሎ በየገጠሩ ማስተማርም ይገባል፡፡ ዛሬ ብርቅና ድንቅ የምንላቸውን አብያተ ክርስቲያናት አባቶቻችን ባይጠብቁልን ኖሮ አናያቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም ለተተኪው ትውልድ የምናወርሰው እንዳናጣ መትጋት ይኖርብናል፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻ ወደ ግል ሕይወትዎ ለመለስና አካል ጉዳተኝነትዎ በአገልግሎትዎ ላይ የፈጠረብዎት ችግር አለ?

አባ ዜና ገብርኤል፡- እውነት ለመናገር አካል ጉዳተኝነቴ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ብዙም ችግር አልፈጠረብኝም፡፡ ምክንያቱም ወንድሞቼና እኅቶቼ ልጆቼ ሳይጸየፉና ሳይኮሩ የሚያስፈልገኝን ሁሉ ያደርጉልኛልና ነው፡፡ መሔድ በምፈልግበት ጊዜ እየተሸከሙ ወደመኪናዬ በማውጣትና በማውረድ በመሳሰሉት ይደግፉኛል፡፡   

ይልቅ ከሚሠሩት አድካሚ ሥራ በተጨማሪ እኔን እየተሸከሙ ሲወጡና ሲወርዱ ቅሬታ ይሰማኛል፡፡ ሙሉ አካል ኖሮኝ እኔም እንደእነሱ ብሠራ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ድሮ ድሮ ስለ በሽታዬ አስብ ነበር፡፡ አሁን ግን የማስበው ‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጀምራለች መቼ ትፈጸም›› ይሆን? ወንድሞቼንና እኅቶችን አስቀይሜያቸው ይሆን? እያልኩ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኔን ደካማውን ምክንያት አድርጎ ወገኖቼ ለእግዚአብሔር ቤት ሥራ ሲተጉ ስመለከት ደስታ ይሰማኛል፡፡ ደግሞም እኮ እንዲህ ባልሆን ኖሮ አሁን የምሠራውን አልሠራ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ለበጎ አድርጎታል፡፡ 

 

ስምዐ ጽድቅ፡- አባታችን እግዚአብሔር ረጅም ዕድሜን ያድልልን፡፡ በአገልግሎትዎ ያጽናልን፡፡ ቃለ ምልልሳችንን የምናቆመው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መምህር ኃይለ ሥላሴ ስለ አባ ዜና ገብርኤል የተናገሩትን ጠቅሰን ነው፡፡  

‹‹እጅ የላቸውም እጅ ያለንን እየሠሩ ያሠሩናል ዐይን የላቸውም ዐይን ያለንን ይመሩናል እግር የላቸውም እግር ላለን እንዴት እንደምንራመድ ያስተምሩናል››

ከአባ ዜና ገብርኤል ሕይወት ብዙ ነገር እንማራለን፡፡ እጅ፣ እግር፣ ዓይን ባይኖራቸውም እግዚአብሔርን አላማረሩም፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ›› /መዝ፡)"፬.፮/ ያለው በጸጋ ተቀበሉት እግዚአብሔርም በአኰቴት ፈቃዱን መቀበላቸውን ዓይቶ የበለጠ ሥራ አሠራቸው፡፡ 

ዛሬ ሙሉ አካል፣ ጊዜው፤ ዕውቀቱና ሀብቱ ኖሯቸው በእምነት ጸንተው በመከራ ታግሠው፣ እምነታቸውን በመልካም ሥራ የሚገልጡ ሰዎችን ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ስለጉድለቱ፣ ስለመከራው ይቅርና በየዕለቱ በሕይወቱ ውስጥ ሰለተደረጉ የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራዎች የሚያመሰግኑ ከናፍር ነጥፈዋል፡፡ 

ሀብት፣ ንብረት ያላቸው የሰጣቸውን ተመልክተው በተሰጣቸው ለቤተ ክርስቲያን፣ ለወገንና ለሀገር የሚበጅ በምድርም በሰማይም ክብርና ዋጋ ያለውና የሚያሰጥ ሥራ ከመሥራት የአካላቸውን ውበት የሀብታቸውን ብዛት፣ የዕውቀታቸውን ምጥቀት በማየት የሥጋ አንቱዎች የነፍስ ጐስቋሎች ብዙዎች አሉ፡፡ 

ስለዚህ እንደ አባ ገብርኤል የበኩላችንን እግዚአብሔር እንደፈቀደልን ለመሥራት ሙሉ ፈቃደኛ የሆነ ልብ ይኑረን እግዚአብሔር ደግሞ የበለጠ ያሠራናል፡፡ የልብ መዘጋጅት ከሰው ነው የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ነው እንዳለ ከሁሉ አስቀድሞ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተዘጋጀ ልብ ይኑረን፡፡ በመጨረሻ ይህን ቃለመጠይቅ አድርገው ከተሟሉ መረጃዎች ጋር ለዝግጅት ክፍላችን ያደረሱንን የአዋሳ የንዑስ ማዕከል አባላትን ከልብ እናመሰግናለን፤ ይልመድባችሁ ሌሎች ይከተሏችሁ፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Read 223 times