Monday, 05 October 2020 00:00

‹‹አንገቱ ላይ ማዕተብ ያሰረ ኦሮሞ አናውቅም››  ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኦሮሚያ ፖሊስም ሕይወት ከማዳን ይልቅ በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ላይ ቀጥታ ጥይት በመተኮስ ለአክራሪው ቡድን ከለላ ሰጥቷል፤ የመሣሪያና የስንቅ ትጥቅ ድጋፍም አድርጓል፡፡ ሕግን እንዲያስከብር ጥሪ ሲደረግለት “ትዕዛዝ አልተሰጠኝም” በማለት የሰው ሕይወት ሲጠፋ በታዛቢነት ተመልክቷል፡፡ እነዚያ ግፍ የተፈጸመባቸው ምእመናን በአሁኑ ሰዓት በሕይወት የተረፉት በሕክምና ቦታ፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አንዳንድ ምእመናን እንደሚናገሩት ከሆነ የተፈጸመው ጥቃት የተቀናጀና በግልፅ የመንግሥት የፀጥታ አካላትም ተሳትፎ ያደረጉበት ነበር፡፡ በአክራሪ ኃይሉ የተፈጸመው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ሃይማኖት ተኮር ሲሆን በኦርቶዶክሳውያኑ ላይ ሆን ተብሎ ታቅዶና ታስቦ የተፈጸመ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ በዝርዝር ተናግረዋል፡፡  የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የፀጥታ ኃይሎችና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ባሉበት መፈጸሙ ደግሞ  ጥቃቱ ቀደሞ የታቀደ እንደሆነ አመላካች ነው በማለት ምዕመናኑ ያክላሉ፡፡ የደረሰው ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት መከላከልም ሆነ መቀነስ ይቻል እንደነበር የገለጡት ምእመናኑ ነገር ግን የመንግሥት መዋቅሩ የተሳተፈበት በመሆኑ  በሕይወታችንና በንብረታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብናል ይላሉ፡፡ አንዳንድ የ ፀጥታ ኃይሎች ሁሉም ነገር ከወደመ በኋላ ለይስሙላ ጥፋቱን ለመከላከል ጥረት እያደርጉ እንደነበረ የተናገሩም አልጠፉም፡፡ 

 

በሻሸመኔ ከተማ ብቻ እስካሁን ደረስ ከ100 በላይ የኦርቶዶክሳውያን የንግድ ተቋማት ወድመዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰም በኋላ ምእመናኑ ያለምንም አጋዥ እርስ በእርሳቸው ብቻ እየተደጋገፉ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ተጠልለው ለሚገኙ ምእመናን ደግሞ የአካባቢው ምእመናን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛሉ፡፡ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችም የርዳታ እጃቸውን እየዘረጉ ይገኛሉ፡፡  የአካባቢው የመንግሥት አካልም ምእመናንን ለተጨማሪ ጥቃት ከማመቻቸት ውጭ የሕግ ከለላም ሆነ ማኅበራዊ ድጋፍ እያደረገላቸው አይደለም፡፡ ንብረታቸውም ሆነ ሕይወታቸው የተረፈ ምእመናን አሁንም ድረስ በከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዴም አክራሪ ቡድኑ ‹‹ገንዘብ ካላመጣችሁ ቤታችሁንና ንብረታችሁን እናቃጥላለን፤ እንዘርፋለን›› በማለት ምእመናኑ ላይ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረሰባቸው እንደሆነ ከምእመናኑ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህንን የፈሩ በርካታ ምእመናን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ አጎራባች ክልሎች ተሰደዋል፡፡ 

ጥፋት ያደረሰ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድንም ሆነ በግብረ አብርነት ሲያገለግሉ የነበሩት የፀጥታ ኃይልና  ሌሎች የመንግሥት አካላት ተይዘው ለፍርድ እየቀረቡ ነው የሚል ሀሳብ ቢኖርም የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ለአክራሪ ኢስላማዊ ጽንፈኛ ኃይል በመወገኑ በፀጥታ ኃይሉ ምንም ዓይነት እምነት እንደሌላቸውና ራሳቸውንና ንብረታቸውን ከጥቃት ለመከላከል አደረጃጀት እየፈጠሩ እንደሆነ ምዕመናኑ ያስረደሉ፡፡ 

በኦርቶዶክሳውያን ሕይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው እልቂት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየተፈጸመ ያለው ሕዝበ ሙስሊሙ በሚበዛባቸው አካባቢዎች እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህ ድርጊት የሚፈጸመው በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ቢሆንም በተደጋጋሚ እየተከሠተ ያለው ግን በኦሮሚያ ክልል  ነው፡፡ ይህ ደግሞ እስላማዊ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድኑ ለዘመናት ሲያልመው የነበረውን ከኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የፀዳ ክልልና ሀገር ለመመሥረት ያለውን የቀን ቅዠት ሕልሙን  ዕውን ለማድረግ እያደረገው ያለውን ጥረት የማያሳይ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ደግሞ ተለያዩ ሥልታዊ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በነደፈው ሥልታዊ ዕቅድ መሠረት በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናንና በንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሚጠቀመውን ስልት በመለዋወጥ ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል በተናጠል ክርስቲያኖችን እያሳደደ ሲያርድ፤ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥል እንዲሁም  ማዕተብ ሲያሥበጥስ አስገድዶ ሲያሰልም ነበረ፡፡

 የሰሞኑን ደግሞ ጽንፈኛ ቡድኑ ስልቱን ቀይሮ ምእመናኑን በአሠቃቂ ሁኔታ ከመግደል እንዲሁም በኢኮኖሚ እንዲጎዱና ተስፋ ቆርጠው አካባቢውን ጥለው እንዲሄዱ ከትንንሽ የንግድ ተቋማት ጀምሮ ትልልቅ ተቋማትን እያወደመ ይገኛል።  ይህ የሚሆነው ምእመናኑ የሚበሉትና የሚጠለሉበት ቤት ከሌላቸው ተማረው ሀገሩን  ጥለው ይሄዳሉ በሚል እሳቤ ነው፡፡  ይህ ከተሳካ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን  ያለ ምእመናን ባዶ ናትና እስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን ለመቆጣጠር መንገድ ይጠርግለታል፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት በኦርቶዶክሳውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ደባና ሴራ በቀላል ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሊነቃና ሕይወቱንና ንብረቱ ሊታደግ ይገባል፡፡ የምእመናንን ደኅንነት በመጠበቁ ረገድም መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ 

መንግሥት በራሱ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች መኖሩን ቢያውቅም ለቤተ ክርስቲያን ያለው ትኩረት አናሳ መሆኑን ነው እስከ አሁን ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሔዱ ያሉ ነገሮች በተጨባጭ የሚያሳዩት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች በእስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን የተጠለፉ በመሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም  እስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን ወንጀል በሚፈጽምበት ወቅት ከፍተኛ ሽፋን ሲሰጥ ተስተውሏል ፤ የምእመናንን ሞት እንዳላየ ታልፏል፡፡ አለፍ ሲልም ንጹሓን ኦርቶዶክሳውያንን በጥይት ይገደላሉ፡፡ መንግሥት ያለፈውን የኦርቶዶክሳውያንን ሥቃይ በትምህርትነት በመውሰድ በክርስቲያኖች ላይ ጭካኔ የተሞላበትን ጭፍጨፋ የሚፈጸሙ አክራሪዎች ላይ በማያዳግም ሁኔታ የሕግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ፣ ለተጎዱ ምእመናንም በጉዳታቸው ልክ ተመጣጣኝ ካሳ ሊሰጣቸ፣ ከዚኽ በተጨማሪም መንግሥት ወንጀልን ቀድሞ የመከላከል አቅሙን  ሊያጎለብት ይገባዋል፡፡ 

ከቤተ ክርስቲያን አንጻር ስንመለከት ደግሞ ምእመናንና ንብረታቸውን ከጥቃት ለመከላከል ምንም የተሠራ ሥራ እንደሌለ መመልከት እንችላለን፡፡ ስለሆነም ቤተክርስቲያን የተጠራቀመ የቤት ሥራ አለባት፡፡ እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን በብርሃን ፍጥነት ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንን እያወደመ፤ ቤተ ክርስቲያን ግን እስካሁን ድረስ ሌላ አዲስ የኀዘን ዘመንን ትጠብቃለች፡፡ ምእምናንና ንብረታቸው ከሌለ ሀገርም ቤተ ክርስቲያንም እንደሌለች መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ዋና ዋና መሠረታዊ ተግባራትን ልታከናውን ይገባታል፡፡ ተደጋጋሚ ግፍ ከእንግዲህ አልሸከምም በቃኝ ማለት አለባት፡፡ 

ምእመናንም የተቀናጀ አደረጃጀት ፈጥረው ራሳቸውንና ንብረታቸውን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያናቸውን ከእስላማዊ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድን ስልታዊ ጥቃት ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ይህ ታዲያ ዘመኑን የዋጀ አደጃጀት መሆን አለበት፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ የመረጃ መረብ  ፈጥሮ ወንጀልን ቀድሞ መከላከልና ወንጀሉ ሲከሠትም በንቃት የመመከት አቅምን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አደረጃጀቱ እውነተኛ የሆኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን ያሳተፈ ቢሆንም ይመከራል፡፡ 

ዋናውና መጀመሪያ መሠራት ያለበት ምእመናን ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲከላከሉ ለሚፈጥሩት አደረጃጀት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ከላይ እስከታች ያለውን አደረጃጀትም ቤተ ክርስቲያን በዋናነነት ልትመራው ይገባል፡፡ አደረጃጀቱን በንዋይ፣ በሀሳብና በቁስ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ በየዘርፉ ያሉ ምሁራን የቤተ ክርስቲያንም ልጆች መእመናንን እንዲያግዙና እቅድ እዲያወጡ ማድርግ አስፈላጊ ነው፡፡ 

የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ምሁራንም ለሚፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ቅደመ ትንታኔና ድኅረ ትንታኔ እንዲሰጡ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ከእነዚህ ዋና ዋና ተግባራት በተጨማሪ  ቤተ ክርስቲያን ለሞቱባት ምእመናን ለጠፋው ሀብትና ንብረት የሚሆን ተመጣጣኝ ካሣ  መንግሥት እንዲከፍል ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ በየጊዜው በእስላማዊ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን የሚያሳዩ የተደራጁ መረጃዎችን ለሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ ለውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች፤ መንግሥታት እንዲሁም ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ማስገባት ይገባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንንና ምእመናንን ከእስላማዊ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድን የተቀናጀ ጥቃት የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ በቸርነቱ ይጠብቅልን፡፡ አሜን!!! 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

 

Read 624 times