ኤስኤኤቲ በተሰኘው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የተመለከተ ውይይት መካሄዱን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
የፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሚስተር ጆርጅ አሌክሳንደር በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም አማካይነት ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁፅ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል፣ ለሩሲያ ሕዝብና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ የተካሄደ ውይይት መሆኑን ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዘህ ቀደም በዋና ጸሐፊው በኩል የቀረበላትን ጥሪ በአዎንታ የተመለከተችው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እተፈጸመ ያለ የታቀደ ጥቃት›› በሚል ርዕስ ተጋባዥ ኢትዮጵያውያን እንግዶች፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የሩሲያ ቤተክርስቲያን ጋዜጠኞችና የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ በተገኙበት በኤስኤኤቲ በተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያዋ ላይ ውይይት እንዲካሄድ ማድረጓን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ጉዳይ እየተከታተሉ ለፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ድርጅት ሪፖርት ለሚያደርጉት ዲያቆን ሰሎሞን ክብርያና አቶ ምንተስኖት ደስታ በውይይቱ ምስጋና እንደቀረበላቸው ዘገባው አስረድቷል፡፡
ፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ የተባለው ድርጅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንን ሰቆቃ ለሩሲያ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ያቀረበ ብቸኛው ድርጅት እንዳደረገው ዘገባው አስታውቆ “ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት የወንጀሎችን እየተከታተለ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቋል” ብሏል፡፡
የፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ጆርጅ አሌክሳንደር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የተመለከቱ ሪፖርቶችን ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንዳስገቡ ከዘገባው ለመዳት ተችሏል፡፡