Thursday, 08 October 2020 00:00

የአርመንያው ፓትርያርክ የእስራኤልን መንግሥት አሳሰቡ 

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
  የአርመንያው ፓትርያርክ በኢየሩሳሌም ኖሩህን ማኖልያን ለእስራኤሉ ፕሬዜዳንት ሚስተር ሪውቩን ሪቪሊን በጻፉላቸው ደብዳቤ የአርመን ግዛት በሆነችው ኖጎሮን ካራባክህ የአዘርባጃን መንግሥት እስራኤል ሠራሽ በሆኑ የጦር መሣሪያዎች ታግዞ ንጹሓን ዜጎችን እያጠቃ መሆኑን  ማስታወቃቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡  በአዘርባጃንና በአርመን ጦር ሠራዊት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ንጹሓን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ጥቃት እየተጋለጡ እንደሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ በደብዳቤው አንሥተው የአዘርባጃን ሠራዊት በወሰደው የኃይል ርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎችና ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለከፋተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡  የአዘርባጃን ጦር ሰራዊት በንጹሓን ላይ የወሰደው የኃይል ርምጃ እስራኤል ሠራሽ የሆኑ አውሮፕላኖችንና ድሮኖችን ተጠቅሞ መሆኑን በእስራኤል ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በድንገት ሲነገር መስማት ያሳዝናል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረው፤ የአዘርባጃን መንግሥት የተጠቀማቸው ጦር መሣሪያዎች ሁሉ ከእስራኤል የተላኩና በናጎሮ ካራባክ የሚገኙ ንጹሐንን  ለሞትና ለአካል ጉዳት እየዳረጋቸው ነው ሲሉ ፓትርያርኩ ለፕሬዝደንቱ በጻፉት ደብዳቤ ቅሬታ አቅርበዋል፡  ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም እስራኤል ሰላም ወዳድ ሀገር መሆኗ ቢታወቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፀረ ሰላም ከሆነችው አዘርባጃን ጎን መቆሟ ጦርነቱ በአዘርባጃን የበላይነት እንዲጠናቀቅ ከመፈለግ ውጭ በሀገሪቱ መካከል ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ፍላጎት ያላት አይመስለኝም ብለዋል፡፡  እስራኤል ለአዘርባጃን መንግሥት የምታደርገውን  የመሣሪያ ድጋፍ  ከዚህ በኋላ እንድታቆም ቅዱስ ፓትርያርኩ ጠይቀው እስራኤል የሰላምን ዋጋ ከማንም በላይ ጠንቅቃ የምታውቅና ስቃይን በቅጡ የምትረዳ ሀገር ናት ሲሉም ተናግረዋል፡፡  በመጨረሻም ለአርመንያ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ለሆነው የአዘርባጃን መንግሥት የሚደረገው የመሣሪያ ድጋፍ በናጎሮ ኮራባክ በሚኖሩ ንጹሐን ላይ ሞት ማወጅ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ያስረዱት ቅዱስ ፓትርያርኩ የእስራኤሉ ፕሬዝደን ጉዳዩን በደንብ በማጤን ለቅሬታው አስቸኳይ  ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡   የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኦርንታል ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት አባል ስትሆን በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በርሳሲድ ገዥ ንጉስ ተሪዳተስ ሦስተኛ አማካይነት ክርስቲያናዊ መንግስትን የመሠረተች ብቸኛዋ ሀገር ናት እንዲሁም ኖጎሮን ካራባክህ የተባለችው ሀገር ደግሞ በአዘርባጃን ግዛት የምትገኝና በአብዛኛው የአርመንያ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የሚኖሩባት እራስ ገዝ ሀገር መሆኑኗ ይታወሳል፡፡         
Read 718 times