Tuesday, 13 October 2020 00:00

‹‹በሃይማኖታችን ምክንያት እየተገፋንና እየተሳቀቅን መኖርን አንፈቅድም” ብፁዕ አቡነ ናትናኤል 

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
“በምንከተለው ሃይማኖት ምክንያት እየተገፋንና እየተሳቀቅን መኖርን አንፈቅድም” ሲሉ የምዕራብ ሸዋ፣ ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ተናገሩ፡፡  ብፁዕነታቸው ይህንን የተናገሩት በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ አስቦ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል በአክራሪዎች በግፍ የተገደሉ ሰማዕታትን ለማሰብ በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ነው፡፡  ብፁዕነታቸው በወቅቱ ክርስትናና መከራ ተለያይተው እንደማያውቁ አስረድተው “በተለይ በሃይማኖታችን ምክንያት መጠቃታችንና መገለላችን አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡ “ነገር ግን  ማዕተቤን፣ ክሬን አልበጥስም ብሎ መሞት ግን ክብር ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡  ብፁዕነታቸው አያይዘውም በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው የተቀነባበረ ጥቃት የማይቆምና የሰላምን ዋጋ የማያውቁ እጃቸውን በደም የታጠቡ ባለሥልጣናትንና አክራሪ ኃይሎችን መንግሥት አደብ ማስገዛት የማይችል ከሆነ ውሎ ሲያድር ዋጋ እንደሚያስከፍለው ገልጸዋል፡፡  የምዕራብ አሩሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ በበኩላቸው አንድነታችንን በማጠናከር በኦርቶዶክሳዊነታችን የሚደርስብንን መከራና ሥቃይ ልናስቆም ይገባናል ካሉ በኋላ ሲደርስብን የነበረው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በመንግሥት መዋቅር በተሰገሰጉ ጫካ ያልገቡ ሽብርተኞች አማካይነት ሲደገፉና ስምሪት ሲሰጥበት የነበረ ነው ብለዋል፡፡  ብፅዕነታቸው አያይዘውም በኦርቶዶክሳውያን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል በአክራሪዎች ሲፈጸም ቆመው ያዩ የነበሩ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር በመኖራቸው መንግሥትም ይህንን ተገንዘቦ መዋቅሩን እንዲያጸዳ ጠይቀዋል፡፡  “በሃይማኖታችን ምክንያት ጥቃት እየደረሰብንና እየተሳቀቅን በራሳችን ሀገር መኖር የለብንም” ያሉት ብፁዕነታቸው መንግሥት የደኅንነት ዋስትና ሊያረጋግጥልን ይገባል ብለዋል፡፡ ምእመናን እየሞቱ ያሉት በሃይማኖታቸው ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ የእነርሱን ጽናትና ትዕግሥት መላበስ እንደሚያስፈልግ ለሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡    
Read 1036 times