Saturday, 24 October 2020 00:00

ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ አደጋ ያጋለጣት የአክራሪዎች እንቅስቃሴ መሆኑ ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ አደጋ ያጋለጣት የአክራሪዎችና የተቃራኒዎች እንቅስቃሴ መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መክፈቻ ዕለት ባስተላለፉት መልእክት ገለጡ፡፡  የቤተ ክርስቲያኗ አሠራርም በክፍተት የተሞላ መሆኑ ከተቃራኒና ከአክራሪ አካላት ጥቃት ባልተናነሰ ሁኔታ አገልግሎትን እያስተጓጎለ እንደሆነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው በቤተ ክርስቲያን የሚታዩ የተለያዩ የአሠራር ጉድለቶች ማለትም የአስተዳደር፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ሊስተካከሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  የቤተ ክርስቲያኗ ያልተስተካከለ አሠራር ምእመናንን እያሳዘነ እንደሆነ ያስታወቁት ቅዱስነታቸው ‹‹ያልተስተካከሉ አሠራሮችንና ሌሎች ችግሮችን ጭምር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል ዕውቀቱ፣ልምዱና ችሎታው ያላቸው ባለሙያዎች ተመድበው በጥናት ላይ የተመሠረተና መሪ እቅድ ያለው አሠራርን መዘርጋት አስፈላጊ ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡  በሰላሣ ዘጠነኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ከባድ ፈተና ላይ መሆኗን ቅዱስነታቸው አንስተው ሁሉም የጥፋት ድርጊት እንዲቆም ሁነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡  ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም የተከፈለው ዋጋ ሁሉ ተከፍሎ ያለአንዳች ግጭትና ደም መፍሰስ ሁሉም ነገር ወደ ዕርቅ፣ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ መሠራት አለበት ካሉ በኋላ ሁሉም ነገር የውይይት ጊዜና ትሥግስት ከታከለበት እየዋለ እያደረ መልካም ይሆናል ብለዋል፡፡   
Read 798 times