Monday, 02 November 2020 00:00

“የአብነት መምህራን ከሌሉ ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያ ማንነት ያሰጋኛል” መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈወርቅ ተክሌ    ክፍል አንድ  

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን በዛሬው የቤተ አብርሃም ዓምድ ዝግጅታችን በደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን የአብነት መምህር የሆኑትን ታላቅ አባት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ አብዛኛውን የዕድሜያቸውን ክፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ያሳለፉት በተማሪነት ከዚያም በአብነት መምህርነት መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ተክሌ የተወለዱት ዋግ የሚባል አካባቢ  ሰቆጣ ውስጥ ነው፡፡ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን ሁል ጊዜ ታታሪ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከነበሩት አባታቸው ቀሲስ ወልደ ተክለሃይማኖት እና ከእናታቸው አበባ ማርዋ መጋቢት ፳፭ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ  ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከዚያው የተወለዱበት አካባቢ ደብረ ሰላም በለዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከቀኝ ጌታ ተኮላ ዘንድ ከፊደል እስከ መዝሙረ ዳዊት ፤ ከግብረ ዲቁና አልፎ አርያም ሠልስቱን ተምረዋል፡፡ አሁን በደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘመናቸው ውስጥ ከልጅነት እስከ እውቀት ያለፉበትን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸው እንደሚከተለው ነግረውናል፡፡    ስምዐ ጽድቅ ፦ በአብነት ትምህርት ቤት እስከምን ድረስ የት የት አካባቢ ተዘዋውረው ተማሩ?   መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ፦  መጀመሪያ የተማርኩበትን አካባባቢውን ለቅቄ ለመማር ከወጣሁ በኋላ ዝቋላ ወረዳ ውስጥ ከምትገኘው ዲስቁ ማርያም የኔታ መኮንን ከሚባሉ የቅኔ መምህር ዘንድ ነው የሄድኩት፡፡ የኔታ መኮንን ፪፻ የሚደርሱ ተማሪዎች ነበሯቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅኔ የተቀኘሁት ከእርሳቸው ዘንድ ነበረ፡፡ ሰምና ወርቅ ጥሩ ችሎታ ነበራቸው፡፡ የኔታ መኮንን ከጊዜ በኋላ ላሊበላ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ሆነው ተቀጥረው ብዙ ዘመን  አገልግለዋል፡ ገድለ ላሊበላን ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትም እሳቸው ናቸው። ከእርሳቸው ዘንድ ከተማርኩ በኋላ ወደ ሰቆጣ ከተማ ሄጄ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ደብር ከሚገኙት የመጻሕት እና የቅኔ መምህር ከሆኑት ባሕታዊ አባ ዓለሙ ዘንድ ቅኔን ከነአገባቡ በሚገባ ቀጸልኩ፡፡ ከዚያ መልስ ወደ ዳሃና ዓምደ ወርቅ ልዩ ቦታው ጉራምባ ጊዮርጊስ በመሄድ የኔታ ታምራት ከሚባሉ ሊቅ ዘንድ  ዝማሬ  መዋሥዕት፣  ጾመ ድጓ፣ ድጓና ምዕራፍን ተምሬአለሁ፡፡ በኋላም ወደ ናአኩቶ ለአብ በመሄድ የድጓና የቅኔ መምህር ከሆኑት የኔታ ኃይለ ማርያም ቅኔውን አጠናቀቅሁ፡፡   ከየኔታ ኃይለ ማርያም ዘንድ ቅኔውንና ዜማውን ካጠናቀቅሁ በኋላ  ዓይኔን ታምሜ ስለነበር ቦሩ ሜዳ የዓይን ሐኪም አለ ስለተባለ አባቴ ከላስታ ወደ ዋድላ ደላንታ ይዞኝ መጣ፡፡  ቦሩ ሜዳ/ከደሴ ከተማ ወጣ ያለ ነው/ ስንደርስ ግን ሐኪሙ ለዓመት ስለቀጠረን አባቴ ወደ ሀገሩ ሲመለስ እኔ ህክምናውን መጠበቅ ስለነበረብኝ ደሴ ውስጥ ደብረ ቤቴል ሥላሴ ከየኔታ ዕንቁ ባሕርይ /መምህር ኃይለ ማርያም/ ዘንድ ትምህርት ቤት ቀረሁ፡፡ መምህር ኃይለ ማርያም አራቱ አይናማዎች ከሚባሉት አንዱ ናቸው፡፡ አራቱ አይናማዎች  ዓይነ ስውሮች ናቸው፡፡ አራቱም በአንድ ወቅት የወጡ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሊቃውንት ነበሩ። እኔም የሕክምናዬን ቀጠሮ እየጠበቅሁ  እሳቸው ዘንድ ክብረ በዓልን፣ወርኀ በዓልን ተማርኩ፡፡ ከዚያም ደሴ ከተማ ውስጥ ከነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቼ ትርጓሜ ሐዲሳትን ተማርኩ፡፡  በዚያው በትምህርት ላይ እንዳለን ወቅቱ ፲፱፻፸፯ ዓመተ ምሕረት ደሴ ላይ ረኀብ ጸንቶ ነበርና መምህራችን የኔታ ዕንቁ ባሕርይ ከዚህ ከከተማው ገጠሩ ይሻላል ወደ ኤልሻማ መድኃኔ ዓለም ሄዳችሁ ብትማሩ ጥሩ ነው ብለው ደብዳቤ ጻፉልን፡፡ እኔ ከሌሎቹ ትንሽ ከፍ እል ነበርና የሰጡኝን ደብዳቤ ይዤ ስድስት ተማሪዎችን አስከትዬ  ቅኔውንም አቋቋሙንም እያስቀጸልኩ ወደ ኤልሻማ መድኃኔ ዓለም ስንጓዝ ያገኙኝ ገበሬዎች መንገድ ለመንገድ /አስፋልቱን/ ስትሄድ ጓደኞችህን ደርግ ይነጥቅህና ብቻህን ትቀራለህ  አንተ ደካማ ነህ ወደዚህ ወደ ገጠሩ ነው እንጂ  ወደ ኤልሻማ መድኃኔዓለም አስፋልቱን አትሂዱ ብለው  ወደ አማራ ሳይንት እንድመለስ ነገሩን፡፡ በጊዜው መምህር ዕንቁ ባሕርይ ያዘዙንን ትተን ወደ አማራ ሳይንት ወደ ላይ ሄድን፡፡ አማራ ሳይንት የኔታ መንግሥቱ የሚባሉ የአቋቋም መምህር ነበሩና ከእርሳቸው ዘንድ ገባን ሆኖም ወቅቱ የረኀብ ነበርና ከዚያም የጠበቀን የከፋ ችግር ነበር።    ከዚያ ብዙም ስላልተመቸን በሽሎውን ተሻግረን ስማዳ ከተማ ጃምባ ተክለ ሃይማኖት የተክሌ አቋቋም መምህር ከነበሩት ከየኔታ ኪዳነ ማርያም ዘንድ ለመማር ገባን፡፡ እኔ የተማርኩት ጎንደሬ ነው እሳቸው ደግሞ ተክሌ ስለሆኑ በጊዜው መግባባት አልቻልንም፡፡ ብዙም ሳንቆይ መምህራችን የኔታ ኪዳነ ማርያም “ስለተጠራሁ ወደ ወለጋ ልሄድ ነውና ደብረ ኤልያስ ጠብቁኝ‘  ብለው ደብዳቤ ጽፈው ሰጡን፡፡ እንደገና ስድስቱን ጓደኞቼን እንደያዝኩ የአባይን በረሃ በእግራችን ተያያዝነው፡፡ ከወንዙ ስንደርስ ውሃው ከብብታችን እየደረሰ መሻገር አቅቶን ነበር ሆኖም እንደምንም በአካባቢው የነበሩ ዋናተኞች አሻግረውን  ደብረ ወርቅ ጉንደ ወይንን አልፈን ደብረ ማርቆስ ደረስን፡፡ መምህራችን ያዘዙን ደብረ ኤልያስ እንድንጠብቃቸው ቢሆንም በየመንገዱ የሚያገኘን ሰው ሁሉ ሲጠይቀን ”ክህነት ልንቀበል ነው‘ እያልን አልፈናቸው  እንሄድ ነበር፡፡   ደብረ ማርቆስ ደርሰን ደኅና የቅኔ መምህር መፈለግ ጀመርን፡፡ የሚያስተምረን  ደኅና የቅኔ መምህር  እንፈልጋለን የት እናገኛለን ብለን ሰዎችን ስንጠይቅ መምህር ጥበቡ ደስታ የሚባሉ ሊቅ በደንበጫ /ከደብረ ማርቆስ ወጣ ያለች ትንሽ ከተማ/ አሉ ብለው ስለጠቆሙን ፈልገን ከየኔታ ጥበቡ ዘንድ ገባን፡፡ በዚያም የጎንጅ ቅኔ፣አገባብ እርባ ቅምር ተምሬ የምስክር ወረቀት ተቀብያለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋሸራውን  ወደ ጎንጅ እየገለበጥኩ ብዙ ጊዜ በተማሪነት የኖርኩ ከእርሳቸው ዘንድ ነው፡፡ ዋናው መምህሬ እርሳቸው ናቸው ማለት ነው።  ስምዐ ጽድቅ ፦  በቀሰሙት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የት የት አካባቢ ተዘዋውረው አገለገሉ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ፦   እንደሚታወቀው  ተማሪ ትምህርት ቤት ገብቶ የቤተ  ክርስቲያኒቱን ዕውቀት ለመቅሰም ፴ እና ፵ ዓመት ይማራል የሚያገለግለው ግን ውስን ነው በትምህርት ቤት የሚያሳለፈው ጊዜ ይበልጣል፡፡ በአገልግሎቱም ጠንካራም ደካማም ጎን ሊኖረው ይችላል፡፡ እኔ  ከየኔታ ጥበቡ አስተምር ተብዬ የምስክር ወረቀት ከተቀበልኩ በኋላ  አቋቋም ለማስመስከር እፈልግ ስለነበር ወደ ጎንደር ነው የኔድኩት፡፡  ለተወሰነ ጊዜ ገጠር አስተምሬ  አዘዞ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ማርያም ደብር የምትባል አለች እዚያ  የኔታ ኤርምያስ ጋር የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፡፡ ብዙ ተማሪዎች ስለነበራቸው ብዙም አልተመቻቸልኝም እንደገና ወደ ጎንደር ተመልሼ አዘዞ አቢየ እግዚእ ኪዳነ ምህረት ደብር  ነው የገባሁት፡፡  በዚያ የነበሩት መምህር የኔታ አክሊሉ ይባላሉ የአቋቋም መምህር ናቸው እሳቸው ጋር ተጠግቼ  እየተማርኩ ሳለ የደብሩ አለቃ አለቃ ገዳሙ ይባላሉ ፶ ብር እንክፈልህና ቅኔ አስተምር ስላሉኝ  አቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ቀን ቀን  እያስነገርኩ ማታ ማታ ቅኔ እየዘረፍኩ ብዙ ተማሪዎች አስተምሬአለሁ፡፡ በዚያ ቅኔ ብቻ ሳይሆን አቋቋምም አስተምር ነበር። በደብሩ መምህር አክሊሉ እና መምህር ዳዊት  የሚባሉ በአካባቢው የሚያስተምሩ በአንድ ደብር ሁለት የአቋቋም መምህራን ነበሩ፡፡ እኔም በዚያ ተቀምጬ እያስተማርኩ ያልተማርኩትንም እማር ነበርና ብዙ ጥቅም አግኝቼበታለሁ፡፡  ከዚያ በኋላ አቋቋም አስመሰክራለሁ ብዬ  ከየኔታ ሄኖክ /መጋቤ አዕላፍ/  አሰፈቅጄ ነበረ ነገር ግን ወንበር ተይዞአል ስለተባለ ወንበር አላገኘሁም እንዲሁ በተመላላሽ  ከእርሳቸው እማር ነበረ፡፡ እንግዲህ በዚያ ዘመን የተወሰነ ጊዜ አስተምሬ ነበር ፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ እንዴት ሊመጡ ቻሉ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦   አጋጣሚ ሆኖ መምህር ሰሎሞን የሚባል ቅኔ ቤት አብረን የነበርን ጓደኛዬ ቀደም ብሎ አዲስ አበባ መጥቶ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም በቅኔ መምህርነት ተቀጥሮ ነበረ፡፡ ወደ እኛ መጥቶ  በተገናኘን ጊዜ አዲስ አበባ ለመምጣት ፈልጋለሁና እባክህ ቦታ ፈልግልኝ ብዬው ስለነበረ ሌላ ጊዜ ስልክ አስደውሎ “አዲስ አበባ ቦታ ተገኝቶልሃልና አሁን ና ” ብሎ መልእክት ላከብኝ ፡፡ መልእክቱ በደረሰኝ ጊዜ ለመሄድ ብነሳም ምንም መጓጓዣ  አልነበረኝም ያው እንደሚታወቀው ለምነን የተገኘውን  ከተማሪ ጋር ነው ተካፍለን የምንበላው እንጂ ምንም ጥሪት የለንም፡፡ የተማርኩባቸውን መጻሕፍት ሽጬ ሁለት ተማሪዎች አስከትዬ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ ስደርስ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ መምህር ሰሎሞን ተቀብሎ  ከብፁዕ አቡነ ገሪማ ጋር አገናኘኝ፡፡ ብፁዕነታቸው  ያኔ የጅማና የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ብዙ ጥያቄዎችን ከጠየቁኝ በኋላ ”መቱ ከተማ የካህናት ማሰልጠኛ አለ በዚያ ለካህናቱ ቅኔ እንድታስተምር ነው የጠራሁህ፡፡ ቅኔ ፣ አቋቋም ፣ዝማሬ መዋሥዕት፣ ዜማ ትችላለህ?‘ ብለው ጠየቁኝ፡፡ ”አዎን እችላለሁ‘ አልኩአቸው፡፡ እንግዲህ በብፁዕነታቸው መልካም ፈቃድ ወደ ኢሊባቡር እንድሄድ ሆነ ወዲያውኑ ከቤተ ክህነት ደብዳቤ ተጻፈልኝ  ሁለት ተማሪዎችን ይዤ ወደ ጅማ ከዚያ ወደ ኢሉባቡር ሄድኩ፡፡ ከ፲፱፻፹፫ እስከ ፲፱፻፹፮ ዓመተ ምሕረት ድረስ የተቀጠርኩበት መደቤ በቅኔ መምህርነት ስለነበር ቅኔ እያስማርኩ ቆይቻለሁ፡፡ ማሠልጠኛው በዓመት ፻ ካህናት ያሠለጥናል፡፡ ስልጠናው በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ነው በመጀመሪያው ዙር ከመስከረም እስከ የካቲት ፶ ካህን እናሠለጥናለን፤ በሁለተኛው ዙር ከየካቲት እስከ ሰኔ ፶ ካህናት እናሰለጥናለን፡፡ በዚህ ረገድ ከሥልጠናው ጋር ተያይዞ የእኛን ማሠልጠኛ ጨምሮ ሌሎች መሰል የካህናት ማሠልጠኛዎች በአኃት አብያተ ክርስቲያናት ይረዱ ነበር፡፡ ከዚያ የሚመጣው ገንዘብ ነው የማሠልጠኛው በጀት፡፡ ለምሳሌ የጎንደርና የጎጃም ካህናት የሚሠለጥኑት ባሕር ዳር ፤ የወሎ እና የትግራይ ካህናት መቀሌ፤ ምስራቅ ሸዋና ሐረር ዝዋይ፤ እንዲሁም  የወለጋ፣ የጅማ የኢሊባቡር ካህናት ደግሞ እኔ ከነበርኩበት መቱ ማሰልጠኛ ነበር የሚሠለጥኑት።  ጥሩ ትምህርት ተሰጠ የምለው ያን ዘመን ነው።    በዚያ ብዙ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡  እኔ ቅኔ ሳስተምር ሁሉም መምህራን አሉ የሐዲስ ኪዳን መምህር ፣ የብሉይ ኪዳን መምህር፣ የአቋቋም መምህር ፣ የቅዳሴ መምህር ፣ የዜማ መምህር ይገኛሉ፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ክፍል ቢያስተምሩም ሌላው ሲያስተምር  ደግሞ ቁጭ ብለው ይማራሉ፡፡ ሁሉም ሰው መምህርም ተማሪም ነው፡፡ ሁሉንም በማዋሐድ የወንጌል ትምህርት በደንብ የተሰጠበት ትምህርት ጊዜ ነበር፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው ለሚሠለጥኑት ካህናት ብቻ አይደለም በአካባቢ ለነበሩት ምእመናን እና የምእመናን ልጆች ሁሉ ነበር ፡፡ ዘመኑ መናፍቅ የጠፋበት ዘመን ነበረ፡፡ ተሳትፎው በጣም ጥሩ የነበረበት ጊዜ ነበር ፡፡ እነዚህ አሁን የቆጠርኳቸው ማሠልጠኛዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አንደበቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ እነርሱ ቢኖሩ ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ባልተቃጠለችም ነበር መናፍቃንም ባልበዙ ነበር፡፡  ስምዐ ጽድቅ ፦  ማሠልጠኛዎቹ መቀጠል አልቻሉም ነበር ? ምን ነበር ምክንያቱ ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦   ከተወሰነ ዓመታት በኋላ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ለማሠልጠኛዎቹ የሚመጣው በጀት ቆመ ተባለ፡፡ ምክንያቱን ስንጠይቅ ርእሰ መምህሩ ሰብስበውን በጀቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወደ ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ማዞራቸውን ነገሩን፡፡ ለምሳሌ እኔ ከማሠልጠኛው የማገኘው ገንዘብ ፻፶ ብር ነበረ ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ስለምቆም ፶ ብር አገኝ ነበረ አንድ ላይ ፪፻ ብርማለት ነው፡፡ ደሞዙ ትንሽ ቢሆንም ምግብ እዚያው ስለሚሠራ የምንመገበው ከማሠልጠኛው ነበረ ደቀ መዛሙርቱም ከዚያ ይመገቡ ነበረ፡፡  በጊዜው በጀቱ ወደ ቅድስት ሥላሴ እስኪዞር ድረስ ሁሉ ነገር የተመቻቸ ነበረ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ድርጅቱ ሲዞር መምህራን እና ተማሪዎች እንዲበተኑ ምክንያት ሆነ፡፡  በጊዜው እንደ ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የነበሩ የካህናት ማሠልጠኛዎች ራሳቸውን የቻሉ ቀደም ሥራ ሰርተው የነበሩ በራሳቸው ገንዘብ ለመቀጠል በቅተዋል፡፡ እንደነ መቱ የካህናት ማሠልጠኛ እኔ የነበርኩበት ማለት ነው እና  ሌሎች ማሠልጠኛዎች  ደግሞ  አቅም ስላልነበራቸው መምህራንን ደቀ መዛሙርትንም ለማሰናበት ተገደዋል፡፡ “የምንከፍላችሁ ደሞዝ የለም ወደ የመጣችሁበት ወደ ሀገራችሁ ሂዱ‘ ብለው አሰናበቱን፡፡  ሁሉም መምህር ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ እኔም ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ መጥተን  የምናስተምርበት ማሰልጠኛ ጠይቀን ነበር አዲስ አበባ ላይ ማሠልጠኛ ሳይሆን ደብር ነው የምንሰጣችሁ የሚል መልስ ተሰጠን ሆኖም ቦታውን ሳናገኝ እስከ ስድስት ወር ቆየን፡፡   በዚህ መሃል ብፁዕ ወቅዱስ  አቡነ ጳውሎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት  መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም አስቀድሰው ሲወጡ ሦስት ቀን በተከታታይ አገኙኝ በሦስተኛው ቀን ግን ቆም ብለው “ይህ ሰውዬ ችግሩ ምንድነው'' ብለው ጠየቁ ሊቄ ብርሃኑ መኮንን ችግሬን  እና ያለሥራ መቆየቴን ያውቁ ስለነበር ”የቅኔ መምህር ነው ቦታ ይሰጠው ሌላ ቸግር የለበትም ‘ ብለው አስረዱልኝ በዚህ ጊዜ ብፁዕነታቸው ”እኛ እንፈልገዋለን እዚህ ቅደስት ማርያም ቶሎ ይጻፍለት‘ ብለው ፈቀዱልኝ፡፡ይህን ሲሉኝ ደስታዬ  ወደር አልነበረውም፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  ስለዚህ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ሥራውን ጀመሩ ማለት ነው?  መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦   አልጀመርኩም ቅዱስነታቸው እንዳዘዙ ለጊዜው ይጻፍልሃል ተብዬ ነበር በማግሥቱ ወደ ሊቄ ብርሃኑ ስሄድ ግን የብፁዕነታቸው ቃል ተፈጻሚ አልሆነም ”እኔ ለቅድስት ማርያም አልጽፍልህም  ሂድ ወደ ሀገረ ስብከቱ ብፁዕ  አቡነ ማትያስ እዚያ ይጠብቁሀል‘ አሉኝ፡፡ አሁን ካናዳ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ማትያስ በወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ በነገሩኝ መሠረት ወደ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሄድኩኝ ፡፡ እሳቸውም ገና እንዳዩኝ ”ለምንድነው ፓትርያርክ ሲመጣ አላስገባ አላስወጣ እያልክ የምትጮኽ?‘  አሉኝ ፡፡  እኔም ”አባታችን ምን ላድርግ ራበኝ መልአክ አይደለሁ ሰው ነኝ ምን ልብላ? የት ልደር? ይዤ የመጣሁትን ገንዘብም ጨርሻለሁ እና ቸግሮኝ ነው‘ አልኳቸው፡፡ ”ምነው ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም አስኮ ገብርኤል፣ ምልክት አድርጌልህ ነበር ለምን አልገባህም?‘ አሉኝ ፡፡ እኔም ”ይኸው ርእሰ መምህሩን ይጠይቋቸው ሁለቱም ቦታ አልጽፍም ብለው አስቀርተዋል‘ አልኳቸው፡፡  ብፁዕነታቸው ካሳሁን የሚባሉትን  /ያን ጊዜ የሀገረ ስብከቱ ርዕሰ መምህር / ጠርተው ሲጠይቁ ገነተ ጽጌ በራሳቸው ሰው ስላመጡ ሌላ ተጨማሪ አንፈልግም ብለው ነው፣ አስኮ ገብርኤልም በጀቱ ተመልሷል ስላሉ ልጽፍላቸው አልቻልኩም አሉ፡፡ አቡነ ማትያስም ”ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲቀጠሩ ስላዘዙ ነገ ባስቸኳይ እንዲጽፉላቸው ብለው ተቆጡ፡፡ ርእሰ መምህሩም ጽፍልሃለሁ ከነገ ወዲያ ና ብለው አዘዙኝ፡፡ በተባልኩት ቀን ሄድኩ፡፡ በሥራ አስኪያጁ በሊቀ ካህናት አለማየሁ ኀይለ ሥላሴ  የተፈረመ ፻፴ ብር እያገኙ ደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ  ቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ አዲሱ ገበያ ያለው ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው፡፡    ደብዳቤው እንደደረሰኝ  ወዲያው ወደ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ፡፡ ደሞዙ ብዙም ባይሆን ቦታው ጥሩ ቦታ ነበረ ፤ እኔም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ እዚያ አለቃ ኤልያስ የሚባሉ ታላቅ ሰው ነበሩ በወቅቱ  ከአለቃ አያሌው ታምሩ ጋር  በጠቅላይ ቤተ ክህነት የጉባኤ ሊቃውንት ዋናዎች ነበሩ፡፡ አለቃ ኤልያስ እግዚአብሔር አብ  ቤተ ክርስቲያን እሑድ እሑድ ወንጌል የሚያስተምሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡ በጊዜው የማታ ስብከተ ወንጌል አይሰጥም ነበርና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ተነጋግሮ ደብዳቤ በመጻፍ እንድጀምር ኃላፊነቱን ለኔ ሰጡኝ፡፡ እኔም ከካህናት ማሰልጠኛ ከኮርስ ስለሄድኩ የደብሩ የአቋቋም መምህር ከሆነው መምህር ዳንኤል ጋር እየተፈራረቅን  ለመጀመሪያ ጊዜ የማታ ስብከተ ወንጌል ጀመርን፡፡  በጊዜው ብዙ ሕዝብ እየመጣ መማር ጀመረ፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ወንጌል የተጠማ ሕዝብ ነበርና እየበዛ ሄደ፡፡ በኋላ ላይ አለቃ ኤልያስ ”እንደግዲህ እኔ ደክሞኛል በኔ ቦታ እየገባህ አስተምር ብለው‘ ሁሉንም ወደ እኔ አስተላለፉ፡፡ ሕዝቡም ተቀበለው በየተራ እየገቡ የመድኃኔ ዓለም ዝክር፣ የእግዚአብሔር አብ ዝክር ይዘክሩ ነበር እኔም በየወሩ እየገባሁ አስተምራለሁ፡፡ የእግዚአብሔር አብ ሕዝብ እንደ ከተማ  ሕዝብ ሰምቶ ሂያጅ አይደለም ትምህርት ተቀባይ ጠንካራ  መንፈሳዊ ፣ ቅዱስ ሕዝብ ነው፡፡ ከስብከተ ወንጌሉ በኋላም  ማታ ማታ የቅኔ ትምህርት ነበር በተለይ  ከጎጃም እና ከጎንደር የሚመጣው ወደ ከተማ መግቢያው በሩ በዚያ ስለሆነ ብዙ ተማሪዎች ወደ እኛ እየመጡ ያርፉ፣ይማሩም ነበረ፡፡ ብዙዎች  ቅኔ ተቀኝተዋል፣ ትልቅ ደረጃም ደርሰዋል፡፡ እንግዲህ እዚያ ብዙ ጊዜዬን ያሳለፍኩት በስብከተ ወንጌል እና ቅኔን በማስተማር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አገልግሎት እጅግ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር፡፡ አንዴ ሌቦች የጽሕፈት ቤቱን ጣሪያ ቀደው ገብተው ገንዘብ ሰረቁ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥበቃ ሠራተኞች  ሰበካ ጉባኤ ላይ ተጠርተው ሲጠየቁ መምህር አፈወርቅ ጋር የሚመጡ፣ መቃብር ቤት የሚያድሩ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ብዙ ተማሪዎች ስላሉ ግቢውን መቆጣጠር አልቻልንም አሉ፡፡ መቃብር ቤት ያሉት ይልቀቁልን የሚል አቤቱታም በጽሑፍ ለጽሕፈት ቤቱ አስገቡ፡፡ ሰበካ ጉባኤውም ሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም መቃብር ቤቱን ለቅቄ እንድወጣና አንድም የአብነት ተማሪ እንዳይገኝ የሚል ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ እውነት ለመናገር እጅግ ያዘንኩበት ጊዜ ቢኖር ያኔ ነው ምክንያቱም እኔም ኾንኩ የማስተምራቸው በርካታ የአብነት ተማሪዎች ሊበተኑ መሆኑ ነው ያሳዘነኝ፡፡ በመሠረቱ ቦታው ከ፲፱፻፹፮ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ያገለገልኩበት ቦታ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ከዚያ ቦታ ስለመሄድ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ አንዴ አስታውሳለሁ ጓደዬ ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሊያስቀጥረኝ ወስኖ ነበር በጊዜው ግን ”አባቴ አለቃ ኤልያስ ከቦታው እንዳልሄድ ቃል አስገብተውኛልና አልሄድም‘ ጥሪውን አልቀበልም ብየው ነበር፡፡  አሁን ግን በደብዳቤ ጭምር መቃብር ቤቱን ለቅቄ እንደወጣ ስለታዘዝኩኝ ወደ ሌላ ቦታ እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክን ”ደሞዝ አልልም ሰው ካለበት ብቻ አድርሰኝ‘ እያልኩ በጸሎት እማጸነው ነበር፡፡   
Read 270 times