ከኃያላን መሪዎችም ሆነ ከሌሎች ሀገራት የሚጎሰመውን የጥፋት ጥሪ በአንድነት በመከባበርና በመመካከር መመከት እንደሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳሰበ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫውን የሰጠው ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ጄ ትራንፕ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ሀገራትን ወደ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የሚያስገባ የጥፋት መልእክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የዶናልድ ትራፕን ግጭት ቀስቃሽ መልእክት በሐዘን እንደተመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቆ ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ታፍራና ተከብራ የኖረችና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነች ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቡ ደግሞ ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑ ነው ሲል በመግለጫው አስታውሷል፡፡
ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በሀራችን ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከመሆኑ በቀር ሀገራችን ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔርና በሕዝቦቿ አንድነት ተከብራና ተጠብቃ ትኖራለች ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ አስገንዝቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በሀገራችን ላይ ያስተላለፉትን የጦርነት ጥሪ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጦ መላው የዓለም መንግሥታትና ሕብረተሰብ ችግሩን በጥልቀት እንዲገንዘቡ አሳስቧል፡፡
ሀገርን የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው የፌዴራልና የክልል መሪዎች እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግልና የቡድን አመለካከቶችን ወደጎን ትተው አንድነታቸውን አጠናክረው ለሀገራቸው ህልውና ዘብ እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡