በቤተክርስቲያንና ‹‹በኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ›› መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ልዩነት በእርቀ ሰላም መፍታቱን አስመልክቶ ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ‹‹ጽርሐ ተዋሕዶ›› አዳራሽ የጋራ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” ሰብሳቢ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንና የሽማግሌ ቡድኑ ሰብሳቢ ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ መግለጫውን በጋራ የሰጡ ሲሆን በኦሮምያ ክልል ያለችው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መዳከም ያሳሰባቸው ወገኖች ችግሩን ለመፍታት ሲሉ ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነትን›› ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደቆዩ በመግለጫው ተነስቷል፡፡
“የኦሮምያ ቤተ ክህነት” ይዟቸው የተነሳው የአገልግሎት ችግሮች በአብዛኞቹ አባቶች፣ ሊቃውንትና ምእመናን የታመነባቸው ቢሆንም ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነትን›› ማቋቋም መፍትሔ ይሆናል የሚለው አሳብ ግን በቤተ ክርስቲያንና በአደራጅ ኮሚቴው መካከል ከፍተኛ ልዩነት ፈጥሮ እንደቆየ ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ልዩነቱን ለማጥበብና በመካከላቸው ያለውን ችግር ለመፍታት በአደራጅ ኮሚቴውና በሽማግሌዎቹ መካከል ላለፉት ስድስት ወራቶች ውይይቶች ሲካሄዱ እንደነበር በመግለጫው የተመለከተ ሲሆን ለስኬታማነቱም የሽማግሌ ቡድኑ “የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ” አመራሮችን፣ ቋሚ ሲኖዶስንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን እንዳነጋገረ ተገልጿል፡፡
በቀጣይም በኦሮምያ ክልል ያጋጠመውን የአገለግሎት መዳከም ለማሻሻል በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የሚቋቋም አካል ተጠናክሮ በአንድነት መሥራት የሚችልበትን ሂደት መፍጠር የተሻለ መሆኑ እንደታመነበት በመግለጫው ተነስቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረትም በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰጠውን አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ባለድረሻ አካላት አንድ ሆነው እንዲሠሩም ጥሪ ቀርቧል፡፡