Monday, 02 November 2020 00:00

በአሜሪካ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ኅብረት በጋራ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በአሜሪካ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ኅብረት በኦርቶዶክሳዊ አንድነትና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተው ውሳኔ ማሳለፋቸውን ኦርቶዶክስ ኦግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡  በአሜሪካ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን መንፈሳዊ ፍላጎትን ለማሟላት ሃይማኖታዊ ሥርዓትና አገልግሎት እንዲፈጸም ለማድረግ ኅብረቱ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ውሳኔውም በጋራ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡  የአሜሪካ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ኅብረት ም/ኃላፊ ሜትርፓሊቲያን ዮሴፍ ፳፻፲፫ ዓ.ም ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በትክክለኛ መንፈሳዊ ሕይወትና መስመር የሚገኙበት ማድረግና   የኅብረቱ  የጋራ  እቅድ የሚፈጸምበት ዓመት ይሆናል በማለት እንደተናገሩ ዘገባው አመልክቶ ‹‹ወጣቶች የእኛ የዛሬና የወደፊቶች ናቸው›› ሲሉ አክለው እንደተናገሩም አስረድቷል፡፡  የጳጳሳቱ ኅብረት ባካሄደው ጉባኤ የተመሠረቱ አዳዲስ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበራት ሲኖሩ እነዚህም የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበርና የኦርቶዶክሳውያን በጎ አድራጎት ማኅበር ናቸው፡፡ እነዚህ ማኅበራት በልዩ ልዩ ኦርቶዶክሳዊ የአገልግሎት ዘርፍ በ፳፻፲፫ዓ.ም ወደ ሥራ እንደሚገቡም ከዘገባው ለመርዳት ተችሏል፡፡  ማኅበራቱ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን መንፈሳዊ ሕይወት የመቅረጽ ሥራ የሚያከናውን ሲሆን ያለውን አቅምና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም የሚሠራ ይሆናል ተብሏል፡፡ የጳጳሳት ኅብረቱ በማኅበራቱ ቆይታ ላይ የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም የማኅበራቱን ጥልቀትና ተቀባይነት ለማረጋግጥ ይጠቅማል ሲል ዘገባው አስረድቷል፡፡ ዓመታዊ ኦርቶዶክሳዊ ጉባኤ እንዲሁም የወጣቶች ሠራተኛ ጉባኤ በዚሁ ዓመት እንዲካሄድ መወሰኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡  
Read 560 times