Monday, 02 November 2020 00:00

ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ የውስጥ ልዩነትን ማስወገድ ይገባል

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን
የ፳፻፲፫ ዓ.ም ፴፱ኛ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገሪቱ ላይ የመጣውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ እንዲሁም በየጊዜው ሲከሰቱ የነበሩና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ግኑኝነት የሌላቸውን ሁነቶች መነሻ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጥቃት ዒላማ ሆና መቆየቷን አስረድቷል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሀገረ ስብከቶች በምእመናን ሕይወት እና ንብረት ላይ ፣ በአገልጋይ ካህናት እና በቤተ ክርስቲያን የደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት ታሪክ የማይረሳ መሆኑን ገልጿል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃት እና ውድመት ፣ በንብረት እና በሕይወት ላይ የደረሰው ጥፋት ከዚህም ባሻገር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የነበረውን የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ንጥቂያ ብሎም በዓላቱ እንዳይከበሩ የተፈጠሩ አሉታዊ ተጽእኖዎች ብዙዎችን ሲያነጋግር የሰነበተ አሁንም ድረስ እያነጋገረ ያለ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በተከታይ ምእመናንዋ ላይ እየተካሄደ ያለው የጥፋት ዘመቻ በአካራሪ ኃይል ፣ በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ሀገርን እንደ ሀገር እንድትቀጥል ትልቁን ድርሻ የያዘችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማጥፋት ዋና ተልእኮዋቸው አድርገው በተነሱ አንዳንድ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት አማካይነት አንዳንዴ በድብቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግልጽ ሲካሄድ መቆየቱ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ፣ ካህናት እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጉዳዩን ከሥር ከሥር እየተከታተሉ ግድያውን፣ የንብረት ውድመቱን ፣ ዝርፊያውን እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋት ዘመቻ ሲቃወሙ ፣ ሲያወግዙ እንዲሁም ሀገሪቱን ለሚመራው የበላይ አካል በመረጃ የተደገፈ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተቃጣ ያለው የጥፋት ዘመቻ ከመቀነስ ይልቅ እየባሰ መምጣቱን ከዳር ሀገር ወደ መሀል መግባቱ እታየ ነው፡፡ ይህ በተቀናጀ መልኩ እየተካሄደ ያለ የጥፋት ተልእኮ በተለይም ወቅት ጠብቆ፣ ምክንያት ፈልጎ፣ አሳቻ ጊዜን ተገን አድርጎ በኦርቶዶክሳውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘመቻ ለመከላከል ፣ ለተጎዱት ለመድረስ ብዙዎች በግልም በማኅበርም ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲረባረቡ ቆይተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜም የተቃውሞ መግለጫ ፣ማሳሰቢያ ፣ ሲሰጥ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ተጎጅዎችን ምስክር ያደረገ ጥፋት እና የጉዳት ጥልቀት በተለያዩ ጊዜያት ወደ መንግሥት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደርሰዋል፣ በየሀገረ ስብከቱ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት የጥፋት ዘመቻውን ስፋት፣ ከጥፋት ዘመቻው ጀርባ ያሉትን ስውር አንጀንዳዎች እና እቅዶች፣እንዲሁም በዚህ ሁሉ ጥፋቶች ውስጥ መንግሥት ያሳየውን ቸልተኝት ጭምር በግልጽ ተችተዋል፡፡ ይህ እየተጠራቀመ፣ በላይ በላይ እየተደራረበ ፣ የመጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም ብሎም የማጥፋት ዘመቻ ከቃል ፣ ከውግዘት ፣ከማሳሰቢያ ፣ ከማስጠንቀቂያ እና ከቃላዊ ተቃውሞ ያለፈ እና መሬት ላይ የወረደ ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ተደራጅተው ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው የሚለው የቅዱስ ፓትርያርኩ  የ፴፱ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት መዋቅሩን ጠብቆ በተግባር የተገለጠ የተደራጀ ኃይል ኑሮት ከመልእክትነት ያለፈ ቁም ነገር ሊኖረው ይገባል፡፡  በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር ባሉ ተቋማት በተለያየ ጊዜ የወጡ የአቋም መግለጫዎች ፣የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ሊያስከብሩ ይገባል የሚሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያዎች ከወረቀት ባለፈ መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከደረሱት ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ማኅበራት አባቶች እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት የአቋም መግለጫዎች መውጣታቸው ፣የተለያዩ ማሳሰቢያዎች መተላለፋቸው ይታወቃል ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተቃጣ ያለውን ጠንካራ የጥፋት ዱላ መመከት አልተቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የአቋም መግለጫዎቹ ፣ ማስጠንቀቂያዎቹና ማሳሰቢያዎቹ  በተላለፉ ማግስት የጥፋት ዘመቻው በእጥፍ መጨመሩ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የሚመለከተው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አካል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ ምእመናኑ ድረስ በ፴፱ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለተላለፉት ውሳኔዎች ተግባራዊነት የበኩሉን አስተዋጸኦ ሊያደርግ ይገባል፡፡  በዚህ ወቅት በኅብረት መቆም ፣ በተለይም የውስጥ ልዩነትን አስወግዶ ባንድ ሐሳብ በመቆም ቤተ ክርስቲያንን በዘላቂነት ከጥቃት የመከላከል ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡     
Read 612 times