Monday, 02 November 2020 00:00

የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታን በመንጠቅ በዓላቱን የማደብዘዝ ድብቅ ሴራ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው ዐበይት በዓላት መካከል የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ እነዚህን የአደባባይ ሕዝባዊ በዓላት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ከዘመን ዘመን ስታከብር ቆይታለች፡፡ በእነዚህ የአደባባይ በዓላት አማካይነት ቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷን ለመላው ዓለም ከማስተዋወቅ አልፋ የሀገርን ባህልና ዕሴት ማሳየት ችላለች፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሀገራችን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገቢ ምንጭ ሆናለች፡፡ በዓላቱን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ ዜጎች በሀገራችን በሚኖራቸው ቆይታ የሚገኘው ገቢ ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ማስተዋል ይቻላል፡፡   ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ዜጎችም በሚያዩት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተደስተው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓትና ሀገሪቱን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው  ያስተዋውቃሉ፡፡ በዚህም በየዓመቱ በዓላቱን ለመታደም የሚመጡት የውጭ ሀገር ዜጎች ከጊዜ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህንን የተመለከተውና የበዓላቱን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በደንብ የገመገመው ዩኒስኮ የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላት የዓለም ቅርስ ሆነው እንዲመዘገቡ አድርጓል፡፡ በዓላቱ በዩስኮ ከተመዘገቡ በኋላም የጎብኝው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ሁለተናዊ ጥቅም ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡  በዓላቱ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለየ ድምቀት ከመከበራቸው ባለፈ ኦርቶዶክሳውያን ባሉበት የዓለም ክፍል ሁሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ ይከበራሉ፡፡ አሁን ላይ በዓላቱ በሌላው ዓለም የሚከበሩትን ያህል በኢትዮጵያ በአንደንድ ቦታዎች በነጻነት እየተከበሩ ነው ለማለት  አያስደፍርም፡፡ በዓላቱ በአንዳንድ የኢትዮጰያ ክፍሎች በሚከበሩበት ወቅት የበዓሉን ድባብ ለማበላሸት ፀረ ክርስቲያን ኃይሎች ሁልጊዜ ሁከትና ብጥብጥ ይፈጥራሉ፤ በታቦተ ሕጉ ላይ ድንጋይ ይወረውራሉ፤ የምእመናን ነጠላ ይነጥቃሉ፤ ያሳድዳሉ እንዲሁም “ታቦተ ሕጉ በእኛ አካባቢ አይሄድም” በማለትም መንገድ ይዘጋሉ፡፡ እነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በአመዛኙ በድሬደዋ፣ በሐረር፣ በምዕራብ አሩሲና በባሌ አካባቢዎች ይስተዋላሉ፡፡   በበዓላቱ ላይ እየተፈጸሙ የመጡ ትንኮሳዎች ተጠናክረው በመቀጠላቸው የመንግሥት ሹማምንቶች የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን ማክበሪያ ቦታዎችን እስከመንጠቅ ደርሰዋል፡፡  በተለይ በአሁኑ ወቅት በዩኒስኮ የተመዘገቡ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ያለአግባብ መንጠቅ የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የአደባባይ በዓላት ማክበርያ ቦታዎች እየነጠቁ ያሉት የበዓሉን ጥቅምና ጣዕም ያልተረዱ አንዳንድ የመንግሥት ሹማምንቶች እንደሆኑ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች ምእመናን በኩል ከሚመጡ መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን በተመለከተ በአብዛኛው ቅሬታ ከሚስተናገድባቸው ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በግንባር ቀደምነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡  የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከአንድም ሁለት የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን የየአካባቢው የመንግሥት ኃላፊዎች እንደነጠቁ ከሀድያና ጋሞ ጎፋ አህጉረ ስብከት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሀድያ ዞን የመንግሥት አመራሮች ደግሞ የዚህ ተግባር ማሳያዎች ናቸው፡፡ የሀድያ ዞን የመንግሥት አመራሮች ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን ትተው ‹‹የእኔ›› ለሚሉት የሃይማኖት ተቋም በመሥራታቸው የተነሳ ኦርቶዶክሳውያን ለረጅም ዘመናት የአደባባይ በዓላትን የሚያከብሩባቸውን ይዞታዎች እንደተነጠቁ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በቅርቡ በመግለጫቸው ማስረዳታቸው ይታወቃል፡፡  በሆሣዕና ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ‹‹ጎፈር ሜዳ›› የተባለውን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታ የመንግሥት አካላት መንጠቃቸውን ተከትሎ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን በዓላቱን ማክበሪያ ቦታ ከማጣታቸው ባለፈ ለከፍተኛ ሥነ ልቡናዊ ጫና እየተዳረጉ እንደሆነ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ አንዳንድ የዞኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ለቤተ ክርስቲያኗ ካላቸው ጥልቅ ጥላቻ የተነሳ ቤተ ክርስቲያኗ ያነሳችውን የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ‹‹ወራሪ›› እያሉ መሳደብ የሚቀናቸው እንደሆኑ ብፁዕነታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡ የተጠየቀውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ተገቢ ሆኖ ሳለ የሕዝበ ክርስቲያኑንና የቤተ ክርስቲያንን መብት በኃይል በመጨቆን በሕዝቦችና በመንግሥት መካከል መጠራጠር፣ ግጭትና ሁከትን ለመፍጠር የሚተጉ የዞኑ አመራሮች እየተከራከቱ መምጣታቸውንም ከብፁዕነታቸው ንግግር መረዳት ይቻላል፡፡ እስከአሁን ድረስ በሀድያ ዞን ሆሣዕና ከተማ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ችግር እንዳልተፈታ ይታወቃልና የቤተ ክርስቲያኗንና የአካባቢውን ምእመናን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ካልተቻለ ለሀገር አንድነትም ሆነ ሰላም እንቅፋት መሆኑን መርዳት ያስፈልጋል፡፡  በሀድያ ዞን በሆሣዕና ከተማ አስተዳድር ያለው ችግር መፍትሔ ሳያገኝ በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ የላሃ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለ፶፫ ዓመታት ያህል ለአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ሲጠቀሙበት የነበረውን ቦታ የወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች መንጠቃቸውን የመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚሁ ሀገረ ስብከት የሚገኘውን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታን የወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች ያለአግባብ መንጠቃቸውን አስመልክቶ የአካባቢው ምእመናን ድርጊቱን በማውገዝ ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግሥት አቤቱታ ያቀረቡ ፳፪ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ያለ አግባብ በእስርና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡ በሐሰት ክስ ከ፯-፱ ዓመታት ከመታሰራቸው ባለፈ በእያንዳንዳቸው ላይ የተወሰነ መቀጮ በአጠቃላይ ሲደመር ፻፹፱ ሺህ ፭፻  ብር ሲሆን የእስር ትእዛዙም ሆነ የብር መቀጮው ተፈጻሚ ሆኖ የሐሰት ክስ የቀረበባቸው ምእመናን በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ እንደሚገኙ የመሎ ኮዛ የወረዳ ቤተ ክህነት ለዝግጅት ክፍላችን የላከው መረጃ ያሳያል፡፡    በጋሞ ጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ላይ በመንግሥት ኃላፊዎች አማካይነት እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል የወረዳው ቤተ ክህነት በቀን ፲፪/፲፩፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት በጻፈው ደብዳቤ በዝርዝር ለሀገረ ስብከቱ ማሳወቁን ተከትሎ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መመሪያ እንዲሰጡ ቢጠየቁም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ውሳኔ ሳይሰጡ በመቅረታቸው ድርጊቱን የተቃወሙ ከ፳፪ በላይ ንጹሓን ምእመናን ለከፍተኛ እስር፣የገንዘብ መቀጮና  እንግልት ተዳርገዋል፡፡  ጉዳዩ ሳይጠነክርና ሳይከፋ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በቀን ፪/፱/፳፻፲ ዓመተ ምሕረት በጻፈው ደብዳቤ የምእመናኑ ጥያቄ እንዲመለስና የሃይማኖት ነጻነት እንዲረጋገጥ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ይህ ሁሉ  ሕጋዊ መንገድ ታልፎም ታድያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ የመንግሥት ሠራተኞች “ሃይማኖታችሁን ደግፋችኋል” በሚል ሰበብ ደምወዛቸውን መቁረጥ፣ የትምህርት እድል ውድድር መከልከል እንዲሁም ሃይማኖታቸውን ለማስለወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉባቸው ነው ሲሉ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በቀን ፲፯/፭/፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት  ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በአግባቡ ተረድቶ የምእመናንን ጥያቄ በመመለስ ምእመናኑ በቀድሞ ቦታቸው የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን በነጻነት እንዲያከብሩ እንዲደረግ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡  ምእመናኑ ተከሰው በፍርድ ቤት ቅጣት የተበየነባቸው ‹‹የበዓላት ማክበሪያ ቦታችን ለምን ይነጠቃል?›› ብለው በመጠየቃቸው ብቻ እንደሆነ የወረዳ ቤተ ክህነቱ አስታውቋል፡፡ በአንጻሩ በወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች በኩል በቀን ፲፰/፭/፳፻፲ ዓመተ ምሕረት በተጻፈ ደብዳቤ “ምእመናኑ የተከሰሱበት ለመናኸሪያ ተብሎ በተወሰነው ቦታ ላይ ሕገ ወጥ ግንባታ በመገንባታቸው ነው” ብለዋል፡፡ ምእመናኑ በተጠቀሰው ቦታ ሕገ ወጥ ግንባታ እንዳያከናውኑ ቢነገራቸውም እምቢተኛ በመሆን በኃይል ግንባታውን በማካሄዳቸው በክሱ መሠረት የእስራትና የገንዘብ መቀጮ እንደተጣለባቸው የክሱ ዝርዝርም ያስረዳል፡፡  ይሁን እንጂ በ፲፪/፲፩/፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከጋሞ ሀገረ ስብከት የደረሳቸውን ቅሬታ ተቀብለው ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ በደብዳቤውም በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳደር የሚገኘው የላሃ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ከ፶ ዓመታት በላይ ሲገለገሉበት የነበረውን የጥምቀትና የመስቀል ማክበሪያ ቦታ የመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ለሌላ አገልግሎት በማዋሉ ማኅበረ ምእመናኑና ካህናቱ የይገባናል ጥያቄ በማንሳታቸው ለከፍተኛ እስራትና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ በደብዳቤው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ታይቶ አመራር እንዲሰጥበት ቅዱስነታቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን የመሎ ኮዛ ወረዳን ፓሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ይስሐቅ ጩርጋ እና የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ኤርምያስ ወሰንን የጠየቅን ቢሆንም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ ነገር ግን የወረዳውን የብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ስባቱን አናግረን “ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ወረዳው ከሕግ ውጭ የሆነ ሥራ እየሠራ ከሆነ አጣርተን መፍትሔ እንሰጣለን”  የሚል ምላሽ ሰተውናል፡፡    ሁለቱ የአደባባይ በዓላት መከበራቸው ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመገንዘብ መንግሥት የበዓላቱን ማክበሪያ ቦታዎች የይዞታ መብት ቢያረጋግጥ መልካም ነው፡፡ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ላሉ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ ሰነድ አዘጋጅቶ ሲሰጥ ሀገሪቱ ከብጥብጥና ሁከት ትድናለች፡፡ በዓሉን በዩኒስኮ ያስመዘገበው ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በመከበሩ ነውና የበዓላቱ ማክበሪያ ቦታዎች ሕጋዊ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗንና የምእመናንን ድምፅ መስማትም ተገቢ ነው፡፡ በየአካባቢው ያሉ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ጥያቄ ያለመመለስ በሀገሪቱ ሰላምና ፍቅር እንዲሁም መረጋጋትን ስለማያመጣ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል እንላለን፡፡    
Read 582 times