Monday, 02 November 2020 00:00

“ወራሪ እየተባልን ከመገደልና ከመሰደድ ወጥተን የሀገር ባለቤትነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል”                     (አቶ ፋንታሁን ዋቄ በማኅበረ ቅዱሳን የህዝብ ግንኝነት ኃላፊ)    ክፍል አንድ               

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ኦርቶዶክሳዊያን ክርሰቲያኖች ለአሰቃቂ ግድያና ስደት ተዳርገዋል፡፡ በተለይም የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎና የፓለቲካ ትርክት ታክሎበት ክርስቲያኖች በየጊዜው የችግሮች ሁሉ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ግፍ ግን እስካሁን ከደረሰው ግፍ ሁሉ በዓይነቱም ሆነ በመጠኑ የተለየና እጅግ አሰቃቂ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ/ም በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከተፈጸመው ጥቃት አንስቶ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችና በደቡብ ክልል በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች እጅግ ጭካኔ የተሞላባቸው  ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ በተለያየ ጊዜያት በአሰቃቂ ሁኔታ በገጀራ ተቀልተው፣ በቆንጨራ ተቆራረጠው፣ በጦር ተወግተው፣ በጩቤ ተዘክዝከው፣ በሜንጫ ተተልትለው፣በዱላ ተቀጥቅጠው እንዲሁም በድንጊያ ተወግረው ሞተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ሕገ አራዊት ባለበት ሀገር ሳሆን ሰዋዊ ሕግ ባለበት ሀገር ነው፡፡ ክርስቲያኖች በየአካባቢው በሕይዎት የመኖር ተፈጠሮዊ መብታቸው ተነፍጎ በሚከተሉት እምነት ብቻ ተለይተው መገደላቸው ለምን ይሆን? ስንል እንጠቃለን፡፡ የተከበራችሁ አንባቢያን “ለምን ይሆን” ስንል  ለጠየቅነው ጥያቄ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል የትብብርና የሕዝብ ግንኝነት አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ የሆኑትን አቶ ፋንታሁን ዋቄን ለቃለመጠቅ ጋብዘናል፡፡ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ሁለንተናዊ ጥቃቶች የጀመረው መቼ ነው?  አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንዋን ማጥቃት የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዘመናት ይፋዊ ጥቃት የተከፈተባት ቢሆንም ያንን ሁሉ በደል በጥበብ ተሻግራ እየኖረች ያለች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመጀመሪያውን የቤተ ክርስቲያን ጥቃት የፈጸመችው ዮዲት ጉዲት  ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ በኦቶማን ቱርክ ቀለብ ይሰፈርለት የነበረው የአዳሉ ግራኝ አሕመድ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት ነው፡፡  ይህ ግለሰብ (ግራኝ አሕመድ) በወቅቱ ኢትዮጵያን አፍርሶ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት ወደ ቱርክ ያግዝ የነበረ ፀረ ኢትዮጵያ ነበረ፡፡ ፀረ ቤተ ክርስቲያን በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጸመው ጥቃት ዘመን የማይሽረው ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ከግራኝ አሕመድ ጥፋት በኋላ ደግሞ ጣሊያኖችና ፓርቹጋሎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ከፋፍለው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ታሪክ የማይዘነጋው ግፍ ተፈጽሟል፡፡ ፋሽስት ጣሊያኖች ሁለት ጊዜ ሀገራችንን ሲወሩ የኢትዮጵያ የአንድነትና የማንነት ምስጢራዊ ቋጠሮ የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ዘመናዊ መሣሪያን ከመጠቀም በተጨማሪ በምእመናን ላይ የመርዝ ጋዝን ተጠቅመዋል፡፡ በነዚህ የግፍ ዘመናት ሁሉ ባንዳ ሙስሊሞችና ሌሎች ከጠላት ጋር አጋርነት ፈጥረው ቤተ ክርስቲያን ሲያጠቁና ሲያስጠቁ ነበር፡፡  ከአርባ ዓመታት ወዲህ ‹‹የብሔር ነፃ አውጭ ነን›› የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት በመፈረጅና በርዕዮተ አለማቸው ጭምር በማካተት ማታገያ ሲያደርጓት ቆይተዋል፡፡ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የተባለው የፓለቲካ ድርጅት “የኦርቶዶክስን አከርካሪ መስበር” የሚል ርዕዮተ አለም ይከተል እንደነበረ ያዘጋጀው ሰነድ ምስክር ይሆናል፡፡ በዚሁ ፓለቲካ ድርጅት በከፍተኛ አመራርነት ይሠሩ የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የተባሉ ግለሰብ ሳይቀር በመጻሕፋቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን “አከርካሪ መስበር” የፓለቲካ ድል እንደሚያስገኝ ገልጠዋል፡፡ “የኦሮሞ ሕዝብ ነፃ አውጪ ነኝ” ብሎ የተነሳው የፓለቲካ ቡድን ደግሞ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የወራሪዎች ፊት አውራሪ ነች›› ብሎ ተነሳ፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሮምያ ክልል ተብሎ በተከለለው የሀገሪቱ ክፍል በሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ ይፋዊ በደል መፈጸም ጀመረ፡፡ “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለችው በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ነው እንጂ እኛጋ ያለችው ባህላችንና መሬታችንን የወረረችው ነች” የሚል የሀሰት ክስም ያቀርባሉ፡፡ በክልሉ ያደጉ ሕፃናትም ይህንን መሰል የጥፋት መርዝ ሲጋቱ በመኖራቸው ካደጉ በኋላ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እያየን ያለነውን ጥፋት ያለምንም ርህራሄ እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ አንደንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሯት ሌላ አካላት ናቸው ብለው ስለሚያስቡ “ከጭቆና ለመውጣት ቤተ ክርስቲያንን ማጥፋት ነው” የሚል ትርክት በትውልዱ አእምሮ ውስጥ ስለገባ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ የጥቃት ኢላማ ትሆናለች፡፡  “የኦሮሞን ሕዝብ ከጭቆና ነፃ አወጣለሁ” የሚል “የኦሮሞ ምሁር ነኝ” ባይ ሕዝብን ከጭቆና ለማውጣት ቤተ ክርስቲያን እንደጨቋኝ በመቁጠር ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያልተገባ ግብግብ ውስጥ ይገባል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ኃይላት በሙሉ ሆን ብለው ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ይረባረባሉ፡፡ የቀኝ ገዥዎቻቸውን ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ እውን ለማድረግ በዳይ ያልሆነችን ቤተ ክርስቲያን ያልሆነ ሥም በመስጠት ዛሬም ትናንትም ሁለንተናዊ ጥቃት እያደረሱባት ይገኛሉ፡፡  የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥቃት ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን ከበደኖ እስከ በሻሻ፣ ከሊሙ ገነት እስከ ዶዶላ፣ ከኮፈሌ እስከ ሻሸመኔ እንዲሁም ከካራሚሌ እስከ ጅግጅጋ ድረስ በጥናት የተደገፉ ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ግፍ ሲፈጸም ነበር፡፡ በነዚህ ቦታዎች ሁሉ የተፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባራት ሁሉ ከላይ በተገለጠው አስተሳሰብ ምክንያት የተፈጸሙ የግፍ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አንዳንድ አካባቢዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተግባር ርዕዮተ አለማዊ አመራር ያለው ነው፡፡ በክልሉ የደረሰውን ጥፋት ወደ ግጭት ዝቅ አድርጎ የሚመለከት አካልም ጥፋቱን ደብቆ ሆን ብሎ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ያለመ ፀረ ኦርቶዶክስ ነው፡፡ በዚህ ዓመት በተከታታይ የተከሰተው ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባር የታቀደ፣ ፍልስፍና ያለው እንዲሁም ኦርቶዶክስን ሀገር አልባ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በምእመናንና በንብረታቸው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያን መግለጫ እንዳወጣች ይታወሳል፡፡ ይህንን መግለጫ እርስዎ እንዴት ገመገሙት? አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ያወጣችው መግለጫ በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት መንግሥታዊ መዋቅርን የተላበሰ፣ በርዕዮተ ዓለም የታገዘ እንዲሁም በፍልስፍና የታጀበ ጥቃት መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ያወጀችበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችው መግለጫ ማስመሰል የለሌበትና በአደባባይ ወጥታ ለተከታዮቿ መሬት ላይ ያለውን እውነት ያስረዳችበት ነው፡፡ እንደምናስታውሰው ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ መግለጫዎች አብዛኛውን ጊዜ እውነቱን ከመግለጽ ይልቅ መንግሥትን ወደ መማጸን ያደሉ ነበረ፡፡ በዚህ ጊዜ የወጣው መግለጫ ግን ጠንካራና እውነቱን ያወጣ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡  ቤተ ክርስቲያንን እያጠቃ ያለው ጥቂት የስርዓቱ ደጋፊዎች ሳይሆኑ ራሱ መንግሥታዊ ሥርዓቱ  እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠችበት መግለጫም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የመንግሥት ኃይል እያጠቃት እንደሆነ የሚያመለክተው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተፈጸሙ አንዳንድ ጥቃቶች የመንግስት ኃላፊዎችና የፖሊስ አዛዦች ሳይቀር የጥፋቱ ተባባሪዎች መሆናቸው ነው፡፡ በአንጻሩ እራሳቸውን በሚከላከሉ ክርስቲያኖች አጥቂዎች ጉዳት ሲደርስባቸው አምቡላንስ ሲላክላቸው ተጠቂዎች ደግሞ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ይደርጋል፡፡ ከሞት የተረፉ ምእመናን ደግሞ የደረሰባቸውን በደልና መከራ እንዳይናገሩ እና ሰብአዊ ድጋፍም እንዳይደረግላቸው የየአካባቢው ባለሥልጣን መከልከላቸውንም መግለጫው በሚገባ አሳይቷል፡፡  አባቶቻችንም ይህንን በይፋ መናገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምእመናን የመግለጫው ሐሳቡ በደንብ እንዲገባቸው የመተንተንና የማብራራት ሥራ ኦርቶዶክሳዊ ሚዲያዎችና የሃይማኖት አባቶች ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምእመናንን በማስተባበር ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው እንዲጠበቁ የሚያደረግ ምክረ ሀሳብ አባቶቻችን ማቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት የኦርቶዶክስ ጠላት እንዲሆን ማድርግ ሳይሆን ኦርቶዶክስ የመንግሥት እንድትሆን የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ምእመናን በትኩረት እንዲሰሩ የማስተባበርና የማንቃት ኃላፊነት ያለው ከአባቶች ትከሻ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም አባቶች ሳይፈሩና ሳያስመስሉ እውነታውን መጋፈጥ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ዘረኝነት ቦታ ሥለሌለው በአባቶች መካከል በዘረኝነት የተለከፉ ካሉ በጥንቃቄ  ወደ እውነተኛው መሥመር በመመለስ በጋራ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን ዘረኝነትን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠርና የልጆቻቸውን አንድነት መጠበቅ አለባቸው፡፡    
Read 482 times