Monday, 09 November 2020 00:00

“የአብነት መምህራን ከሌሉ ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያ ማንነት ያሰጋኛል”

Written by  በመጽሐፈ ሲራክ

Overview

“የአብነት መምህራን ከሌሉ ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያ ማንነት ያሰጋኛል”    መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈወርቅ ተክሌ   ክፍል ሁለት      እንደአጋጣሚ ሐምሌ ፭ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከበር ነበርና እዚያ ላይ ቅኔ እንድቀኝላቸው ስለተነገረኝ በዚያ ተገኝቼ ነበር፡፡ ለብፁዕነታቸው ቅኔ ተቀኝቼ ስወጣ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን የማውቀው ጓደኛዬ ከዚያው ደብር የቅኔ መምህር የነበሩት አባት ጡረታ ስለወጡ ለመቀጠር እንድጠይቅ ጠቆመኝ እኔ ግን እጅግ ፈራሁ፡፡ ቅዱስ ኡራኤልን የሚያህል ትልቅ ደብር ይቅርና ወደ ገጠር ለመሄድ ነበር ሐሳቤ፡፡ በጊዜው ስምንት ተማሪዎች ይዤ በኪራይ ቤት ውስጥ ነበርኩ የነገረኝን አድምጬ ”እስኪ እግዚአብሔር ያውቃል‘ ብዬው ተለያየን፡፡ በኋላ እሱው ነግሮ ይመስለኛል የደብሩ ጸሓፊ ሊቀ ሥዩማን ኪዳነ ማርያም ለደብረ ሲናው ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ጸሓፊ በመደወል ”መምህር አፈወርቅ ወደ ደብረ ጽጌ መምጣት ይፈልግ እንደሆን ጠይቅልኝ በእርሱ ስም ወደ ሀገረ ስብከት ደብዳቤ ጽፈናል‘ በማለት ነገረው፡፡ ጸሓፊው ሲነግረኝ ምንም ሳላንገራግር ሀገረ ስብከት መከታተል ጀመርኩ፡፡ በአጋጣሚ ግን ጸሓፊው ለሀገረ ስብከቱ እኔን እንደሚፈልጉ ደብዳቤ ሲጽፍ አለቃው ደግሞ በጎን ቀጨኔ ያሉት መምህር እንዲመጡ ጽፈው ኖሮ ሁለት ተቀጣሪዎች ሆነን ተገኘንና በፈተና ይለዩ ተባለ፡፡ በኋላ ላይ እሱም ቀረና በዕጣ ይለዩ ተብሎ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ባሉበት ዕጣ ሲወጣ ለኔ ወጣና በ፯፻ ብር ደሞዝ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል አገልጋይ ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በጊዜው የደብረ ሲና ሕዝብ እንድቀርላቸው ጠይቀው ነበር እኔ ግን ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡    ስምዐ ጽድቅ ፦  ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ያለዎት ያገልግሎት ጊዜ እንዴት ነው?  መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ  ፦    ደብረ ጽጌ ጥሩ የአገልግሎት ጊዜ ነው ያለኝ፡፡ አሁን ድረስ እዚያው ነኝ፡፡ በርግጥ ብዙ ተማሪ ባይገኝም የአብነት ትምህርቱ አለ፡፡ እንደ ክረምት ወንዝ ክረምት ክረምት ይበዛል በጋ በጋ ደግሞ ይቀንሳል አንዳንዴም ይቋረጣል ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዱ የዘመናዊው ትምህርት ይወስደዋል አብዛኛው እየሠራ ነው የሚማረው ደሞዝ የለውም፡፡ ከሰኔ ጀምሮ ግን ዘመናዊው ሲዘጋ ብዙ ሰው ይማራል ዘንድሮ ግን በኮሮናው ምክንያት ትምህርቱ ጭራሽ ተቋርጧል፡፡ ደብረ ጽጌ ጥሩ ጥሩ ካህናት ነበሩ ፤ የማታ ስብከተ ወንጌልም ይሰጣል፡፡ እያንዳንዱ ካህን በየተራ እየገባ ወንጌልን እንዲያስተምር ተወያይተን ፈቃደኛ ሆነው በመገኘታቸው ማታ ላይ  የሚሰብከውን ቀን ቀን ሲያጠና ውሎ ርእስ ጠብቆ ያስተምራል፡፡ በዓለ እግዚእ፣ በዓለ ማርያም ሲሆን ዋዜማ የሚመጡ ጉባኤተኛም ያስተምራሉ፡፡ እያንዳንዱ ካህን የራሱን ስብከት አጥንቶ መጥቶ ይሰብካል ፣ አስተያየት ይሰጠዋል በዚህም በደብሩ ላይ ያለው ካህን ሁሉ ሰባኪ ሆነ፡፡ በዚያ መነሻ ብዙዎቹ ካህናት የንስሓ ልጆቻቸውን  እየሰበሰቡ በየወሩ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ብዙዎች ወንጌልን የተማሩበት ትልቅ ቦታ ነው፡፡ አስተምረን ግን ለማስመረቅ ማኅተም አልነበረንምና ብዙ ተማሪዎች ማኅተም ካለበት ወደ ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም እየሄዱ እየተማሩ የምስክር ወረቀት መያዝ ጀመሩ፡፡ ስብከተ ወንጌሉ እዚያ ተመድቤ ከሄድኩበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ አለ እኔም አስተምራለሁ፡፡     ስምዐ ጽድቅ ፦  በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከጀመሩ ስንት ዓመት ሆንዎት?  መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ብቻ ፲፩ ዓመት አገልግዬአለሁ ከ፲፱፻፹፮ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፺፯ ድረስ ማለት ነው፡፡ ከ፲፱፻፺፯ ጀምሮ እስከ ዛሬ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን እያገለገልኩ ነው ያለሁት፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  በአብነት ትምህርት ቤት ምን ያህል ጊዜ ቆዩ ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦  በትምህርት ቤት ያሳለፍኩት ረጅም ዘመን ነው አንድ ፴ ዓመት ይሆነኛል፡፡ ቅኔ ቤት ከአምስት መምህራን ተምሬአለሁ፣ትርጓሜ መጻሕፍት ደግሞ ከሁለት የመጽሐፍ መምህራን ፣ እንዲሁም አቋቋም ከሁለት መምህራን ዘንድ ተምሬአለሁ፡፡ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ጠንቅቆ ማወቅ አይችልምና እኔም የተወሰነውን እና የምፈልገውን ያህል ተምሬአለሁ፡፡ ከኢሉባቦር እስከምመለስ ድረስ ለትምህርት ከሀገሬ ከወጣሁ ጀምሮ በ፴ ዓመቴ ነው ወደ ሀገር ቤት የተመለስኩት፡፡   ስምዐ ጽድቅ ፦  በአብነት ትምህርት ቤት መምህርነትዎ ከተማሪ ጋር የነበረዎት ግንኙነት እንዴት ነበር? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦   ከተማሪ ጋር ባለኝ ግንኙነት በተለይ ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ብዙም ደስተኛ አይደለሁም የዚህ ምክንያት ደግሞ ከማስተማሩ ጋር ብዙ ነገር ስላልተመቻቸልኝ ነው፡፡ ለማስተማር እፈልግ ነበር ግን ቦታው ተመቻችቶ ተማሪ በብዛት የሚገኝበት ሲሆን ነው መንፈስም የሚነቃቃው፣ ደስም የሚለው፡፡ ዛሬ አንድ ተማሪ ነገ ደግሞ አንድ ተማሪ እየተንጠባጠበ መጥቶ ሊማር ቢል ለአንድ እና ለሁለት ተማሪ ቁጭ ብሎ መዋል ብዙም አያረካም በዚህ ምክንያት ነው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል የማታውን ትምህርት የጀመርኩት፡፡ አብነት ትምህርቱ ላይ ሰው ሲጠፋ ነው ካህናትን ሰብስቦ ኮርስ የመስጠት ጅማሮ የነበረው፡፡ ከምእመናን እና ከሕፃናት እንዳልለይ ሐሙስ ሐሙስ አስተምር ነበር ተማሪ አልባ ዝም ብዬ እንዳልኖር በሚል ነው፡፡ ተማሪዎችን በሰፊው ለማስተማር ሐሳብ ነበረኝ ግን ተማሪ ስለሌለ አልተቻለም፡፡ ደብሩ አስፈላጊውን ነገር ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራን አሟልቶ ቢሆን ሁሉም ሥራ እስከሆነ ድረስ  ማገልገል ይቻል ነበር፡፡ እኔ ግን አሁን በብዛት አገልግሎቴ ማሕሌት መቆምና ፍትሐት መፍታት ነው፡፡ በደብረ ጽጌ እሑድን ሳይጨምር ዘጠኝ ወርኀ በዓል አለ፡፡ እሑድ አራት ጊዜ ይቆማል ከዚያ ውጪ ዘጠኙን ወርኃ በዓል በየቀኑ እየገባሁ ስቡሕ ወዉዱስ እያልኩ አገለግላለሁ፡፡ አሁን በኮሮና ምክንያት ቀረ እንጂ ፍትሐትም መንደር ለመንደር እየሄድኩ ስፈታ እውላለሁ፡፡ በአጠቃላይ ተማሪ ስለሌለ ዛሬ ላይ የኔ አገልግሎት ፍትሐትና ማሕሌት መቆም ነው፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  ምናልባት ከተማ መሆኑ ተጽእኖ አድርጎ ይሆን? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦  ከተማ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው ትልቁ ምክንያት ግን የተማሪዎች የኑሮ ሁኔታ ነው፡፡ ተማሪዎች የሚበሉት ስለሌላቸው የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ወደ ሥራ እንጂ ወደ ትምህርት አይመጡም፡፡ ጥቂት እንኳ ቢኖሩም ሙዳየ ምጽዋት እስኪያገኙ ድረስ ነው እሷም ስለማትበቃቸው ወጥተው ተጨማሪ የቀን ሥራ ይሰራሉ፡፡ ስለዚህ ከሥራ ውለው ማታ ላይ ለመማር ይደክማቸዋል ይተኛሉ፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  በአብነት ትምህርት ቤት መምህርነት ምን ያህል ተማሪዎች አፍርተዋል የእርስዎንስ ፈለግ የተከተሉ እንዲሁም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያንቱ መዋቅር ውስጥ የሚያገለግሉ አሉ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ የተቀኙ ብዙዎች ናቸው በቁጥር እንዲህ ነው ልል አልችልም፡፡ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ሳለሁ ቀደም እንዳልኩት የጎጃምና የጎንደር በር ስለሆነ ብዙ ተማሪዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው እየተቀኙ ሄደዋል፡፡ ከዚህ ደብረ ጽጌ ከመጣሁ ግን የማስታውሳቸው ዘጠኝ የተቀኙ አሉ፡፡ ከዚያው ሙዳየ ምጽዋት እያገኙ የተቀኙ ወደ ዐሥር አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጋውን አቋርጠው ክረምቱን የሚጀምሩ አሉ እንደዚያ እየሆነ ቁጥራቸው ከዚያ በላይ አልሄደም ፤ መዘምርነት  እንጂ ለመምህርነት ብዙ ደርሷል እንኳ ለማለት አልደፍርም፡፡ የኔን ፈለግ የተከተለ እና እንደ እኔ መምህር የሆነ እገሌ የምለው የለም፡፡ የሚማር ተማሪ እስከሌለ ድረስ የኔን ፈለግ የተከተለ ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት አንድ ደኅና ዘራፊ አለ ተምሮ የሄደ ተስፋ የማደርገው ነገር ግን  ገጠር ነው ያለው ምናልባት እርሱ እኔን ይተካ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦ ቤተ ክርስቲያን እንደ እርስዎ ያሉ መምህራን እንዲበዙ ምን ማድረግ አለባት ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦  መምህራን እንዲበዙ ከተፈለገ ቤተ ክርስቲያን ማድረግ ያለባት በጣም አጭር ዘዴ ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ የመምህራንን እና የተማሪን ፍልሰት ማቆም አለበት  ቀድሞ በጥንቱ እንዲህ የከፋ ፍልሰት አልነበረም ጎንጅ በጎንጅ፤ ዋሸራው በዋሸራ ፤ የዋድላውም በዋድላ አስመስክረው ከዚያው ቦታ ጎንጅ እና ዋሸራ ይቀመጡ ነበር፡፡ አሁን የሚፈልሱበት ምክንያት ይታወቃል፡፡ ዛሬም ለመምህራን በቂ ደሞዝ ሰጥቶ ባሉበት እንዲቀመጡ ቢደረግ መምህራን እንደሚበዙ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የሚፈልሱትን መምህራን እና ደቀ መዛሙርት የሚፈልጉትን አሟልቶ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ላይ ብዙ እየሠራ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በበአታ፣ በጎንደር፣ በቤተ ልሔም፣ በዙር አምባ፣ በደቡብ ሌሎችም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበሩ ብዙ ደቀመዛሙርት እያፈራ እንደሆነ እናያለን እንሰማለን ይህ እጅግ ደስ የሚል ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባ መልካም ተግባር ነው፡፡ ይህ በጎ ተግባር መቀጠል መስፋት አለበት አዲስ አበባ ላይ ያሉ መምህራን ደቀ መዛሙርትን እንዲያስተምሩ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ጉባኤ ከሌለ ምን ይጠቅማል? ጉባኤያት በምንጭ ይመሰላሉ ፤ ምንጭ ከከርሠ ምድር ካልወጣ ይቆማል ምንጩ እየበዛ ሲሄድ ደግሞ ፈሳሽ ይሆናል፤ ፈሳሹ እየበዛ ሲሄድ ወራጅ ይሆናል ፡፡ ምንጩ ደጋውን፣ ወራጁ ወይና ደጋውን፣ ፈሳሹ ቆላ ደጋውን አጠጣ ማለት ነው ነገሩ የተያያዘ ነው፡፡ እንደዚህ ጉባኤያት ምንጭ ከሆኑ ከምንጭ የሚወጣው ፈሳሽ ምንድነው መምህራን ናቸው ማለት ነው፡፡ ከጉባኤ የሚወጡ መምህራን ናቸው፡፡ ወራጁ ቆላውን የሚያጠጡ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ከመምህራን የሚወጡ መጻሕፍት ማለት ነው ተያያዥ ነው፡፡ ያ ምንጭ እስካለ ድረስ መምህራንም አሉ መጻሕፍትም አሉ፡፡ ምንጩ ከደረቀ ግን ስቡሕ ወዉዱስ ብሎ የሚቆም ወይም አሐዱ ብሎ የሚቀድስ ይቅርና  ተንሥኡ ጸልዩ የሚል ደቀ መዝሙር አናገኝም ይህ የታወቀ ነው፡፡  ዛሬ የምናገኛቸው አባቶቻችን ጳጳሳት በቅዳሴው በቅኔው፣በአቋቋም፣ በመጻሕፍት ትርጓሜና በሌሎቹ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ አልፈው እዚህ የደረሱ  ፤ ስለ እመ ብርሃን ብለው ከጉባኤ የወጡ ሊቃውንት እንጂ ቤተ ክርስቲያን ዝም ብላ ያመጣቻቸው አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምንጮች፣ ፈሳሾች ፣ ወራጆች እንዳይደርቁ ጉባኤያትን ማጠናከር ነው፡፡ አባቶች ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርና ምንጭ ናቸውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የዕውቀት ምንጮች በደንብ ይዛ የሚገባቸውን እየሰጠች እንዲያስተምሩ የምታደርግ ከሆነ ከሥር እየተተካ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ አሁን እንደምናየው ብዙ ዕድሜውን በአብነት ትምህርት ቤት ቆይቶ ሲወጣ ቤተ ክርስቲያን ደሞዝ ከፍላ በሚገባው ቦታ ተቀምጦ እንዲያገለግል ማድረግ አለባት፡፡ ይህ ካልሆነ ከ፳ እና ፴ ዓመት በኋላ ሊሆን የሚችለው ነገር ካሁኑ ያሰጋኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች ምንጫቸው ከደረቀ ፣ መምህራን ከሌሉ ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያ ማንነት ያሰጋኛል፡፡ ሀገራቸው እንደፈረሰ እንደ የመን እንደሌሎች ሀገሮች እንዳትሆን እሰጋለሁ፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አደጋ ተጋርጦ ነው ያለው፡፡ ይህን መቋቋም ካልቻልን ትምህርት ቤቱን አባዝተን ተማሪዎች እንዲበዙ ካልተደረገ እና ካልተጠናከሩ  ”ሁሩ ወመሀሩ‘ የሚለው አምላካዊ ትእዛዝ ካልተላለፈ በስተቀር ሁላችንም ደሞዝ ብቻ እያገኘን ያለማስተማር የምንቀመጥ ከሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያስፈራል፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  መጻሕፍት እንዳሳተሙ ይታወቃል ምን ያህል ናቸው ? ይዘታቸውስ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦  መጻሕፍቱ እንዲህ ዝም ብሎ ከመቀመጥ የተጻፉ ናቸው፡፡ ልብም ኅሊናም ስለማያርፍ ነው እንጂ ተሰጥኦ ኖሮኝ ወይም አዋቂ ሆኜ አይደለም የጻፍኩት፡፡ ግስ ወርዶ ሲያልቅ  ቅኔ ተዘርፎ  ሲያልቅ የሚመጡትን ሐሳቦች ችሎታ ያላቸውን ልጆች ኑ ጻፉ እላለሁ  ይጽፋሉ ያቺ ትቀመጣለች ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሌላ ሐሳብ ሲመጣ እንዲሁ ይደረጋል ያቺን አጠራቅሜ ነው መጽሐፍ ያደረግሁት፡፡ ለኅትመት የበቁት አምስት ያህል መጻሕፍት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፍ መጽሐፈ ታሪክ ወግስ የሚል ነው፡፡ በቆሎ ትምህርት ቤት የተማሪውን ችግር ለማቅለል የጻፍኩት ነው፡፡ የቆሎ ትምህርት ቤት ግስ በእጅ ተጽፎ ነው የሚጠናው ፤ መጻፍ የማይችል ሰው ከፍሎ ለማጻፍ ገንዘብ ይቸገራል በዚያ ላይ ግሱ ላይ ታሪክም ስላለ የተማሪን ችግር ለመፍታት ነው የዕለቱን ታሪክ እና ግሱን ለማጥናት እንዲመቻቸው አድርጌ የጻፍኩት፡፡ በዚህ መነሻ ነው በመጀመሪያ ግሱን ወደ አማርኛ በመተርጎም ፣ ሊቃውንት ጥንት በእጅ ጽፈውት የነበረውን ግእዙን እንዲሁ ክብረ በዓል ደግሞ ከልደታ እስከ ፴ ቀን ያሉተን በአጠቃላይ  አርስተ ግስ የቅኔ ዜማ ልክ፡ የአእመረን እርባታ እነዚህ ተሰብስበው ነው መጽሐፈ ታሪክ ወግስ መጽሐፍ የተጻፈችው፡፡ ሁለተኛዋ ትምህርተ አበው ወውሉድ የምትል አነስተኛ መጽሐፍ ስትሆን የአባቶች ትምህርት ለልጆች የምትል  ሰባቱን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፣ አምስቱን አእማደ ምሥጢር ፣ ለሕፃናት የሚሆኑ ልዩ ልዩ ታሪኮችን እንዲሁም የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የያዘች መጽሐፍ ናት፡፡ ሦስተኛዋ መዝሙረ ማሕሌት ወቅዳሴ የምትል መጽሐፍ ስትሆን የሰባቱን ዕለታት እና የዐሥራ ሁለቱን ወራት አጠቃላይ ታሪክ የያዘች መጽሐፍ ናት፡፡ ምስባኩ፣ የወንጌሉ እና መልእክታቱ ፣ የዘመኑ ታሪክም ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ መስቀል፣ ዘመነ ፍሬ እና ዘመነ ዮሐንስ በሚል ተከፋፍለው የተጻፉባት መጽሐፍ ናት፡፡ አራተኛዋ መጽሐፍ ቤተሰብና እንስሳት የምትል መጽሐፍ ናት፡፡ቤተሰብ እና እንስሳት ለየት ያለ ታሪክ ያላት ሲሆን የሰውን ከልደት እስከ እርግና ያለውን ታሪክ በዕድሜ ደረጃ በመከፋፈል ፤እንዲሁም ስለ እንስሳት የሚበሉና የማይበሉትን እንስሳት በመዘርዘር ዘሌዋውያን ፲፩  ላይ ካለው ጋር በማጣቀስ የጻፍኩት መጽሐፍ ነው፡፡ አምስተኛው መጽሐፍ ሐረገ ትውልድ ዘክርስቶስ የሚል ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ያለውን ትውልድ ነው የሚተርከው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘመነ ሐዋርያት ፣ ዘመነ ሐዋርያን አበው  ፣ ዘመነ ሰማዕታት፣ ዘመነ ሊቃውንት  . . . ወዘተ  አካቶ የያዘ  መጽሐፍ ነው፡፡ ከላይ ከጠቀስኳቸው መጻሕፍት በተጨማሪም እግዚአብሔር ቢፈቅድ ለኅትመት የተዘጋጁ ሁለት መጻሕፍትም አሉኝ፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦  በሕይወትዎ ፣ በአገልግሎት ዘመንዎ የገጠምዎን ጥሩም ሆነ መጥፎ የሚሉትን እና  የሚያስታውሱት ቢነገሩን? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦   ጥሩና መጥፎ የምንለው ያው የተፈራረቀብን ደስታና ኃዘን ማለት ይመስለኛል፡፡ በጣም የተደሰትኩበትን ጊዜ አላስታውስም ሐዘን ግን ከልቤ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ በተለይ የዚህን ዓለም ከንቱነት ሳስብ ፣ ”ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው‘ የሚለው ከኅሊናዬ ሲመላለስ ሐዘን ካልሆነ በስተቀር ደስታ ወደ ሐሳቤ መጥቶ አያውቅም፡፡ ሆኖም መጀመሪያ ያዘንኩበት ቀን ልጅ ሆኜ ፍየል ስጠብቅ ቦምብ የመታኝ ቀን ነው፡፡ የምንጠብቃቸው ፍየሎች ጠፍተውብን ከጓደኞቼ ጋር ባድማ ውስጥ ስንፈልግ በጨርቅ የተጠቀለለ ነገር አግኝተን ከኛ ከፍ የሚል ልጅ ነበር ምንነቱን ለማወቅ በድንጋይ ሲቀጠቅጥ ፈነዳ እኔ ከእርሱ ጀርባ ነበርኩና ፊቴ ላይና እጄ ላይ ጉዳት ደረሰብኝ ያ ጠባሳ ትቶ አልፎአል ሐዘኑ ግን ከልቤ አይጠፋም፡፡ እንዲሁም ዳሃና ዓምደ ወርቅ ልዩ ቦታው ጉራምባ ጊዮርጊስ የኔታ ታምራት ከሚባሉ ሊቅ ዘንድ  እየተማርኩ ሳለ ደግሞ  ወረርሺኝ ገብቶ ነበር ፡፡ በዚያ አካባቢ የወረርሺኙን ስም ”ሽዋ‘ ይሉታል በመጀመሪያ በዚያ ወረርሽኝ ምክንያት ጓደኛዬ ሞተ። እኔም የወረርሽኙ ዕጣ ፋንታ ደርሶኝ ከሞት ተርፌአለሁ፡፡ ተማሪዎች ተራራ ላይ እንደ ጎጆ ተክለው ”ቀሳ‘ይባላል በዚያ የተወሰነ ጊዜ ቆይቼ  ጓደኞቼ አስታማሚ ሆነው  እየረዱኝ ድኜ ወጥቻለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የአብነት ትምህርት ቤት እያለን አባት እናት ስለሌለ ተማሪው ነው እርስ በርሱ የሚረዳዳው። ያንን ችግር በአብነት ትምህርት ቤት ጓደኞቼ እርዳታ አልፌዋሁ፡፡ ሌላው የኢህአዴግ ሠራዊት ሰቆጣን ሲቆጣጠር እኔ ከአባ ዓለሙ ጋር ነበርሁ እየተማርኩ ምሽቱን ከደርግ ጋር ሲዋጋ አደረና ንጋት ላይ ከተማዋን ተቆጣጠረ፡፡ ጥዋቱን በየመንደሩ ሲዞር እኔ ያለሁበትን ቤት መጥቶ በሩን በመደብደብ አስከፈተኝ የኔታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ነበርና እኔን ይዘው ሊሄዱ ይጎትቱኝ ጀመር ሰዎች ልጅ ነው ተማሪ ነው ብለው ሊያስጥሉኝ ቢሞክሩም የደርግ ወታደር ነው ይኸው ጠባሳ አለው እጁ ሁሉ ተመትቷል ብለው እምቢ ብለው ሰውን ሁሉ ያስጨነቁበት ጊዜ መቼም አልረሳውም፡፡   ስምዐ ጽድቅ ፦  ቀረ የሚሉትና የሚጨምሩት ወይም የሚያስተላልፉት ነገር ካለ? መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦  የምጨምረው የለም ጠርታችሁ ስለጠየቃችሁኝ ከሕይወት ልምዴ እንዳካፍል ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ዛሬ ዛሬ ዙሪያው በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ተግታ ልትሠራ ይገባታል፡፡ ሁላችንም ከቤተ ክርስቲያን የተወለድን፣ መግቢያችን ፣ መጠጊያችን እርስዋ ናት ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋ እና እንድትበዛ ተግተን ልንሠራ ይገባል፡፡ የቤተ ክህነቱም ሆነ የማኅበሩ የቴሌቭዥን ጣቢያ በዚህ ረገድ ጥሩ እየሠራ ይገኛል፡፡ አሁንም አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሕይወታቸው አስተማሪ የሆኑትን ሊቃውንትን ብታቀርቡ ጥሩ ነው፡፡ ብዙ የተበላሹ ነገሮች ሊስተካከሉ ይችላሉና፡፡ በቅኔው ፣በግእዙ በኩል የሐዲሳቱ ሊቃውንት ቢቀርቡ ብዙ ያስተምራሉ የጠመመውን ያቃናሉ፡፡ በተለይ ግእዝ ሞቷል፣ተቀብሯል የሚሉቱ ብዙ ናቸው እኔ ግን ይበልጥ እየጠፋ ያለው ቅኔ ነው እላለሁ፡፡ የሚያስተካክል የሚያርም አባት ቁጥር እየመነመነ ነውና፡ ለምሳሌ አቋቋም ቢበላሽ ተው እንዲህ አይደለም የሚል ብዙ ነው ሊቃውንቱ ማሕሌቱ ላይ ፤ ዜማም  ሲሰበር እንደዚሁ  የሚያቀናው ብዙ ነው፡፡ ቅኔ ግን ሞያው ይቅርና ዜማው ሲሰበር ተው የሚል የለም፡፡ የዚህ አገልግሎት አነስተኛ እንደሆነ እናውቃለን ፡፡ በተለይ የግእዝ መምህራንን አቅርባችሁ የግእዝ  የት መጣ ገለጻ እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል፡፡ ጥንታዊ የመጀመሪያው በመሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሐዲሳትም ፣ የብሉያትም ፣ የሊቃውንቱም ፣ የመጽሐፈ መነኮሳቱም ምንጩ ስለሆነ  የቅኔው እና የግእዙ ሊቃውንት እንዲበዙ ብታደርጉ በእውነቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደፊት ትንሣኤዋን ታገኛለች ብዬ አስባለሁ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እናንተንም ይጠብቃችሁ ማኅበሩን ያስፋ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ ኢትዮጵያን ያስፋ እግዚአብሔር ይስጥልን  አመሰግናለሁ፡፡    
Read 264 times