ጥንታዊውንና ታሪካዊውን የሀግያ ሶፊያ ኦርቶዶክሳዊ ቤተ መቅደስን የቱርክ መንግሥት ወደ መስጅድነት የቀየረበትን ሂደት ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ዩኒስኮ ማስታወቁን የኦርቶዶክስ ታይመስ ድኅረ ገጽ አስነብቧል፡፡
የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት መቀየሩን በተመለከተ ከተለያዩ አካላት ይሰጥ የነበረውን አስተያየት ዩኒስኮ ከተመለከተ በኋላ ኃላፊነቱን ወስዶ በጉዳዩ ላይ ከሐምሌ ፳፻፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ምርመራ ሲያካሄድ እንደቆየ ዘገባው አስታውሷል፡፡
ዩኒስኮ በቤተ መቅደሱ ላይ ያለው አቋም የማይለዋወጥ መሆኑን ዘገባው ያነሳ ሲሆን ቅርሱ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም ቀደም ሲል የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎቹን ወደ ስፍራው እንደላከ ተገልጧል፡፡ ባለሙያዎቹም በቅርሱ ላይ የተደረገውን አካላዊ ለውጥና ወደ መስጅድነት መለወጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖረው ስለሚችል ተፅዕኖ ገምግመዋል ተብሏል፡፡
የምርመራ ውጤትና ሂደቱን ከሰኔ ወይም ከሐምሌ ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ ለዓለም አቀፍ የቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ እንደሚቀርብ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በቅርሱ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ባለመጠናቀቁ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳልተቻለ ዘገባው አመልክቶ ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ክብካቤ ሕግጋትን ጠብቆ ዩኒስኮ እየሠራም እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ሃያ አንድ አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴም እንዲሁ ቅርሱ ወደቀደመ ክብሩ የሚመለስበትን ሁኔታ እያመቻቸ እንደሆነ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡