Tuesday, 24 November 2020 00:00

ማኅበረ ቅዱሳን ፲፬ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ አካሔደ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  ማኅበረ ቅዱሳን ፲፬ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በማኅበሩ ጽ/ቤት ሕንፃ አካሔደ፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ጸሎተ ወንጌል እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን የዕለቱ መርሐ ግብር በማኅበሩ ሰብሳቢ በአቶ ታምሩ ለጋ የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክት ተጀምሯል፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ የ፳፻፲ ዓ.ም እና የ፳፻፲፩ ዓ.ም የውጪ ኦዲት ዘገባን ጨምሮ የማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣የኤዲቶሪያል አገልግሎት ሪፖርት የማኅበሩ ኦዲት አገልግሎት ሪፖርት፣ የማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ የአጋማሽ ዘመን ግምገማ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚሉ አንኳር ርእሰ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡ በቀጣይ ቀንም ፮ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫና የኦርቶዶክሳውያን ተሳትፎ ፣ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች እይታ፤ በኦርቶዶክሳውያን አንድነትና ኅብረት የማኅበረ ቀዱሳን ድርሻ ፣ የማእከላት እና የዋናው ማእከል ግኑኝነት ከፋይናንስ አኳያ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት መመሪያ ማሻሻያ ምክረ ሓሳብ የሚሉ አጀንዳዎች ቀርበው በሁሉም ርእሰ ጉዳዮች ላይ  በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ጉባኤውን ሲከታተሉ በነበሩ አባላት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡  በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ-ጂንካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ኃላፊ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፤ ከየማእከላቱ የተወከሉ የማኅበሩ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው እሑድ ኅዳር ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በነበረው የመጨረሻ መርሐ ግብሩ ማኅበሩን ለቀጣይ ዓመታት የሚመሩትን የሥራ አመራር አባላት በማስመረጥ እንዲሁም  አገልግሎት ያጠናቀቁ የሥራ አመራር አባላትን በክብር በመሸኘት ጉባኤውን አጠናቋል፡፡  
Read 558 times