ጆርጂያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለጥንታዊው የጆርጂያ ጀቫሪ ገዳም ጥገና የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
በምሥራቃዊ ጆርጂያ የሚገኘው ይህ ጀቫሪ የተሰኘው ኦርቶዶክሳዊ ገዳም በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተገደመ ሲሆን የአሜሪካ ኤምባሲ ለጥገናው ወጭ ያደረገው ገንዘብ ቅርሱ ይዘቱን እንደጠበቀ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ይህ ታሪካዊና ጥንታዊ የጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም በዩኒስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ ስለሆነም የአሜሪካ ኤምባሲ ለገዳሙ ጥገና የሚውል ከአምስት መቶ ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በጆርጂያ የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደር የሆኑት ኬሊ ዲኛን መንግሥታቸው በጆርጂያ ኦርቶዶክስ ገዳም ላይ ለሚደረገው መሠረታዊ ጥገና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ በእጅጉ ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
የጆርጂያ ገዳማት ለጆርጂያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት የላቀ ሚና እንዳላቸው የተጠቆመ ሲሆን የረጅም ጊዜና ዘመን ተሻጋሪ ሆነው መገኘታቸው ለመካከለኛው ዘመን የጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ህያው ምስክሮች ሆነዋል ተብሏል፡፡