በ፴፱ ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተላለፈው “የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ራሳቸውን ለመከላከል ይደራጁ ”የሚለው አባታዊ መመሪያ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የተደራጀ መዋቅር አዲስ ባይሆንም ወቅቱን ያገናዘበ ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ እና በተከታይ ምእመናንዋ ላይ እያለፈ ያለውን ሰቆቃና መከራ ማዕከል ያደረገ፤ የጠበቀ እና የተቀናጀ አሰላለፍ እንዲኖር የተላለፈ መመሪያ በመሆኑ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጅ ትኩረት ሰጥቶ በተግባር ላይ ሊያውለው ይገባል፡፡
ወቅቱ እያንዳንዱ ለብቻው የሚሮጥበት ሳይሆን ያለውን እና የነበረውን መዋቅራዊ አደረጃጀት ጠብቆ በኅብረት የሚጓዝበት፤ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት አጥብቆ የሚሠራበት፤ የቤተ ክርስቲያንን የቀደመ ክብር ለመጠበቅ የሚተጋበት መሆን አለበት፡፡ ከዘልማዳዊ አሠራር ወጥቶ በሕግ እና በሥርዓት በመሄድ ከዚህ በፊት ለተፈጠረው እና ወደፊት ሊፈጠሩ ለሚችሉ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ተኮተር ጥቃቶች የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመዋቅር ባዕድ ፤ ለአደረጃጀት አዲስ አይደለችም ሲባል ከምእመኑ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን የአገልግሎት መርሕ ማለት ነው፡፡ ይኽን የተለመደ አሠራር ትኩረት ሰጥቶ መከወን መደበኛ አድርጎ በዕለት ከዕለት ሕይወት መተርጎም፣ከእኔነት ወጥቶ በእኛነት መንፈስ መንቀሳቀስ ፤ የሁሉም ድርሻ አድርጎ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት፣አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት እና አድባራት፣ ማኅበራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እና ሰባክያነ ወንጌል መምህራን ከፍተኛውን ድርሻ ሊጫወቱ ይገባል፡፡
አደረጃጀቱን ለማጠንከር አስቀድሞ የነበረው መዋቅር ክፍተት ምን እንደሆነ መፈተሸ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም የትላንት ድክመት ነገ ለሚሠራው ሥራ ግብዓት ይሆናልና፡፡ ትላንት የታለፈበት መዋቅር የትላንቱን ችግር ለምን እንዳመጣው መፈተሸ ግድ ይላል፡፡ ዛሬ ላይ ቆሞ ወደ ኋላ ሄዶ ክፍተቱ የት ጋር እንደተፈጠረ መገምገም ቀዳዳውን ከመድፈን ባሻገር ነገ ለሚፈጠረው ጠንካራ አደረጃጀት መነሻ መሠረት ሊሆን ይችላልና ሊበረታበት የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡
የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ዘላቂ በሆነ ሉዐላዊነት ላይ ለማስቀመጥ እያንዳንዱ ራሱን መከላከል በሚችልበት አቅም ላይ እንዲደርስ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ወግና ባሕል መሠረት አንዱ ሌላውን በጥሞና ሊሠማው ይገባል፡፡ ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን አንዱ ለሌላው ክብር ሊሰጠው ይገባል ፣ስለ ልዕልናዋ ሲባል ከራስ ክበብ ወጥቶ በኅብረት ውስጥ መገኘት ይጠበቃል፡፡ ዳርና ዳር ጽንፍ መያዝ እና ለብቻ መቆም ቤተ ክርስቲያንን ዛሬ እየደረሰባት ካለው መከራ ፣ ነገ ሊገጥማት ከሚችለው ፈተና ሊታደጋት አይችልም፡፡ ይልቁንም “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ትጠፋለች፤ . . ” ማቴ ፲፪፥፳፭ እንዳለው ወንጌላዊው ከኅብረት የወጣ ግላዊነት ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ ነገር ከማጋለጥ የተለየ ፋይዳ የለውም፡፡ በመሆኑም እከሌ ከእከሌ ሳይባል በአንድነት መቆም ከማንኛው የቤተ ክርስቲያን ልጅ ይጠበቃል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆችዋ በኅብረት ሆነው ራሳቸውን መከላከል በሚችሉበት መልክ እንዲደራጁ መመሪያ ማስተላለፏ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ከአመፅ ጥሪ ጋር መቀላቀል የለበትም፡፡ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ የነበረ፣ያለና ወደፊትም የሚኖር መዋቅራዊ አሠራር ነው፡፡ በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኝ እና የሚከወን መሆኑን ጥርጣሬ ውስጥ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችም ሆኑ ከውጭ ሆነው በአመፅ መሣሪያነት የሚፈርጁ አካላት በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
በኅብረታዊ ሥራ እና አደረጃጀት ውስጥ ለኖረች ፤አሁንም እኖረች ላለችው ቅድስት ቤተ ክርስያናችን ወደ ተግባር የተለወጠ፣በጥበብ የታገዘ ግኙኝነትን በመፍጠር የራስንም ሆነ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና መጠበቅ ከባድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የነበረውን አስፍቶ እና አጠንክሮ ማስቀጠል እንጂ አዲስ ሥራ አይጠበቅምና ነው፡፡ አሁን ዐቢይ ጉዳይ የሚሆነው እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ከከተማ አስከ ገጠር ፤ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪው ዓለም “እንደ አንድ ልብ አሳቢ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ” ሆኖ መገኘት የግድ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ ፥ እነሆ መልካም ነው ፥ እነሆም ያማረ ነው፡፡” መዝ ፻፴፫፥፩ እንዳለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ኅብረት እጅግ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነውና ቸል ሊባል አይገባም፡፡
ዛሬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ ልጆች የአባቶቻቸውን ቃል ሊሰሙ ይገባል፡፡ አባቶች ለልጆች ጆሮአቸውን ሊሰጡ ይገባል፡፡ ወደ ጎንም ሆነ በተዋረዳዊው ሠንሠለት ውስጥ በመናበብ፣ በመታዘዝ እና በመቀባበል ለጠነከረ አደረጃጀት በቅድሚያ ወደ አንድነት መምጣት ከእያንዳንዱ የሚጠበቅ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ሁሉም ባለበት የዕድሜ፣ የዕውቀት ፣እና የሙያ ደረጃ ለእናት ቤተ ክርስቲያን በአንድነት መቆም ይጠበቅበታል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ዘር ቀለም፣ ዕድሜ እና ሙያ ሳይለይ በሚፈጠር ኅብረት ውስጥ ጎልታ ልትታይ የእያንዳንዱ ክርስቲያን የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ በየሙያ ዘርፉ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከቤተ ክርስቲያን ፣ ከአባቶች ጎን መቆም በኅብረት መሥራት ፣ ባሉበት ቦታ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር” እንዳለ የሀገሬ ሰው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነገ ሕልውና የቤተ ክርስቲያንን አደረጃጀት አስፋፍቶ እና አጥብቆ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡