Tuesday, 24 November 2020 00:00

"በውጪው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች ሳይሆን ተስፋፋች እላለሁ"                             --- መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ክፍል አንድ

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን በዛሬው የቤተ አብርሃም ዓምድ ዝግጅታችን ይዘንላችሁ የቀረብነው በሰሜን አሜሪካ የሴንት ሊውስ ደብረ ናዝሬት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የኦሃዮ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ የሆኑትን መልአከ ገነት በለጠ ይረፉን ነው፡፡  በመንፈሳዊ አገልግሎት ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ ፤ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ በብዙ አድባራት በተለያየ ኃላፊነት ተመድበው ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል፡፡ እኛም በ፳፻፲፫ ዓ.ም  ፴፱ኛው ዓለም አቀፍ  የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ሀገረ ስብከታቸውን ወክለው ኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ አግኝተናቸው ከልጅነት እስከ እውቀት ያላቸውን የሕይወት ተሞክሮ ( የሥራ ልምድ እንዲያካፍሉን የአብርሃም ቤት እንግዳ አድርገናቸዋል እነሆ፡- ስምዐ ጽድቅ ፦ በቅድሚያ ጥሪያችንን አክብረውና ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ሆነው ስለተገኙልን በልዑል እግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን ፡፡ መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦ እኔም አክብራችሁ ሐሳቤን እንድሰጥ የሕይወት ተሞክሮዬንም ለሌሎች እንዳካፍል ለቃለ ምልልስ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ የምሰጠውም ሐሳብ የሚጠቅም እንዲሆንልኝ እመኛለሁ፡፡

 

ስምዐ ጽድቅ ፦ በመጀመሪያ የት ተወለዱ? ወላጆችዎ ማን ይባላሉ? የትስ ተማሩ?  

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦   የተወለድኩት በ፲፱፻፷ ዓ.ም በኦሮምያ ክልል አሩሲ፤  ሥሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ነው፡፡ አባቴ ሊቀ አበው ይረፉ ደንባው ይባላሉ አሁን በሕይወተ ሥጋ የሉም፤ እናቴ እማሆይ በቀለች ለሽበሉ ይባላሉ በሕይወት አሉ፡፡ ወደ መንፈሳዊ ት/ቤት የገባሁት በሕፃንነት ዕድሜዬ ነው ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ታላላቅ ወንድሞቼ ሁሉ ካህናት እና ዲያቆናት ስለነበሩ የእነርሱን ፈለግ በመከተል ነው፡፡

የቃልና የንባብ ትምህርት እስከ ግብረ ዲቁና  ሥሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከቆሞስ አባ ሀረገ ወይን ( አቡነ ሰላማ ) ዘንድ ተምሬ በ፲፱፻፸፫ ዓመተ ምሕረት ከብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የዲቁና ክህነት በመቀበል በይመና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዲቁና አገልግያለሁ፡፡ 

ውዳሴ ማርያም ዜማ መስተጋብዕ ሠለስት አርያምን የተማርኩት ጀጁ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ልሳናት ነቅዓ ጥበብ ቸኮል ዘንድ ነው፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴን የተማርኩት ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ከየኔታ ሙሴ ዘንድ ነው፡፡ ሰዓታት የተማርኩት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ከታላቅ ወንድሜ ሊቀ መዘምራን ፀጋዬ ይረፉ ዘንድ ነው፡፡ በዓለማዊ ትምህርት ከአልፋ የርቀት ትምህርት ኮሌጅ በሒሳብ አያያዝና ማኔጅመት የትምህርት ዘርፍ ተምሬ ተመርቄአለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ የጀመሩትን መንፈሳዊ አገልግሎት በመደበኛነት ያገለገሉባቸውን ቦታዎች ቢገልጹልን ? 

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦  እውነት ነው ቅዱስ ጳውሎስ " ያጸናኝን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግነዋለሁ፤ለመልእክቱ ሾሞ ታማኝ አድርጎኛልና " ፩ኛ ጢሞ ፩፥፲፪ ብሎ ለጢሞቴዎስ እንደነገረው እግዚአብሔር ፈቅዶልኝ  መንፈሳዊ አገልግሎት የጀመርኩት እጅግ ሕፃን ሳለሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር አባቴ  ቤተ ክርስቲያን እናቴ አገልግሎቷም ጥማቴ ብዬ በሀገሬ በኢትዮጵያ ፤ከሀገር ውጪ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ አውሮፓንና ካናዳን ጨምሮ በአለችኝ ትንሽ እውቀትና በተሰጠኝ ፀጋ መጠን በቅዳሴ፣ በዝማሬ ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በፀሐፊነትና በአስተዳዳሪነት አገልግያለሁ፡፡ 

በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ደጅ እየጠናሁ የቅዳሴ ትምህርት ከተማርሁ በኋላ የኮተቤ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤተ ክርስቲያን ሲቋቋም የቃል ኪዳኑ ታቦታ ከቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ሄዶ ፫ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቅዳሴ ቤቱን ሲያከብሩ የመጀመሪያው ዲያቆን ሆኜ ገባሁ፡፡ በዚያው ቀርቼም በዲቁና ፣ በሰባኬ ወንጌልነት በዋና ጸሐፊነት አገልግያለሁ፡፡

ከመካነ ሰላም ኢያቄም ወሐና ቤተ ክርስቲያን ወደ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን በዋና ፀሐፊነት ተዛውሬ በወቅቱ ሰባኬ ወንጌል የነበሩት አባት ቆሞስ አባ መልአኩ ጌታነህ (የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል) ም/አስተዳዳሪ ሆነው ሲሾሙ እኔ በምትካቸው የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሆኜ ተመድቤ አገልግያለሁ፡፡  ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ወደ እንጦጦ መንበረ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተዘዋውሬ በጊዜው የደብሩ ሰባኬ ወንጌል የነበሩት አባ አፈወርቅ ወደ ውጪ ሀገር ሲሄዱ በእሳቸው ቦታ በሰባኬ ወንጌልነት ለአንድ ወር እንደሰራሁ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ዝውውሩን በመቃወም ይመለሱልን ብለው ቤተ ክህነቱን ስለጠየቁ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ተመልሼ በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ያገለገልኩ ሲሆን ቅዱስ ጋብቻዬንም የፈጸምኩት በዚሁ ደብር በዚያን ጊዜ ነው፡፡

ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጥንታዊውና ታሪካዊው የየካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተዛውሬ በዋና ጸሓፊነት አገልግያለሁ፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው የካራ ቅዱስ ፋኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሲቋቋም የመጀመሪያ አስተዳዳሪ ሆኜ የቃል ኪዳኑን ታቦት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ተቀብዬ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ፤አዲስ ቦታ፤አዲስ አለቃ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ 

በመቀጠል ወደ ሳሪስ አዲስ አምባ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ተዘዋወርኩ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ በካህናቱ አንድነት በሕዝቡም አስተዋይነት በደብሩ ላይ ውጤታማ ሥራ የሠራሁበት፤  ብዙ በረከት ያገኘሁበት ቦታ ነው፡፡ በስብከተ ወንጌልና በመልካም አስተዳደር ከአዲስ አበባ አድባራት የተሻለ ውጤት በማምጣት ተሸላሚ ለመሆን የበቃሁበት ደብር ነው እግዚአብሔር ቢፈቅድ መካነ ዕረፍቴ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ከሳሪስ አዲስ አምባ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ወደ ገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ተመድቤ ነበር፤ ነገር ግን የኪዳነ ምሕረት ካህናትና ምእመናን ቅያሬውን በመቃወም ለቅዱስ ፓትርያሪኩ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ  ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አምባ ደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት አገልግያለሁ፡፡ 

ሳሪስ አዲስ አምባ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እያለሁ በተከታታይ የሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ሲያትል ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ፣ የስዊድን እስቶክሆልም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ተመድቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዞው ሳይሳካ ቀረ፡፡ በሦስተኛው ግን በጣሊያን ሚላኖ የፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆኜ ተመደብኩ ነገሩ ተሳካና ወደ ጣሊያን ሄጄ ለሁለት አመታት ያህል በአስተዳዳሪነት አገልግያለሁ፡፡   

ስምዐ ጽድቅ ፦ የውጪ ሀገር ጉዞ ለሁለት ጊዜ ተጀምሮ ከቀረ በኋላ በሦስተኛው ተሳክቶ ወደ ጣሊያን እንደሄዱ ነግረውናል በዚያ ያለውን አገልግሎት እንዴት አገኙት ? 

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦ እንግዲህ አስቀድሞ የተመደብኩበት የውጪ ሀገር ጉዞ ያልተሳካው ለበጎ መሆኑን ሁሉንም ከአየሁት በኋላ በሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ሰሜን አሜሪካ ተመድበሃል ተብዬ ደብዳቤ ደርሶኝ ከምወደው ደብሬና ሕዝቤ መካከል ተነስቼ ቦታውን አስረክቤ ብዙ ተወርቶ ሲቀር አዝኜ ነበር፤ የተሰጠኝም ምክንያት አላሳመነኝም ፤ሰውም ደህና ነገር አልነገረኝም፤ ነገር ግን "ያለ እርሱ ፈቃድ የሚበላ ወይም የሚጠጣ ማነው?" መክ ፪፥፳፭  እንዲል እግዚአብሔር ለእኔ ከእኔ በላይ ስለሚያስብ ነው በማለት ተቀብዬዋለሁ፡፡ በእርግጥ ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ወደ ጣሊያን ሚላኖ ፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተመድበሃል የሚል ደብዳቤ ሲደርሰኝ እንደ በፊቱ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈጽሞ እንድወጣ ተደረገ፡፡ 

በእውነት በቦታው ስደርስ  ዲያቆናቱ ፣ መዘምራኑና ምእመናኑ ነበሩ በፍቅር የተቀበሉኝ፡፡ የአባቶቼ አምላክ እግዚአብሔርም ስለተከተለኝ ሰበካ ጉባኤው፣ ዲያቆናቱ፣ መዘምራኑና ምዕመናኑ ሁሉ የምላቸውን የሚሰሙ ሆኑልኝ፣ እኔም እነርሱን በሚገባ እሰማለሁ በፍፁም መተባበር በእንድነትና በፍቅር ሆነን መንፈሳዊ አገልግሎቱን በማጠናከር፣ ወጣቱን በማስተባበር ፣ሕዝቡንም በማስተማር እና ስልጠና በመስጠት ለሁለት ዓመታት ውጤታማ ሥራ  ለመሥራት ችያለሁ፡፡ 

ምንም እንኳ የተመደብኩት ሚላኖ ፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቢሆንም በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩትንም ምእመናን ለማገልገል እንፋጠን ነበር፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቦታዎች በዚያን ጊዜ በጽዋ ማኅበር ስም ያሰባሰብናቸው ናቸው፡፡ በወቅቱ በጣሊያን ሀገር ሁለት  አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ነበሩ  የሚላኖ ፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤልና የሮም ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ይመስገን በርካታ ሆነዋል፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩት ንቡረ እድ ኃይለ ልዑል ወልደ ገሪማም ብዙ ሠርተዋል፡፡

በውጪ ሀገር አንድ ካህን ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ነው በውስጥ ገብቶ ይቀድሳል ፣ በዓውደ ምህረት ቆሞ ያስተምራል ፣በቅኔ ማኅሌቱ ያገለግላል ፣ ያፀዳል : ያነጥፋል ፣ንስሐ አባት ነው ይጠብቃል ፣አማካሪ ነው አስታራቂ ሽማግሌም ነው፡፡ በእውነት ጨው መሆኑ የሚታይበት አገልጋይነቱ በትክክል የሚረጋገጥበት ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ ወደ አሜሪካን ሀገር እንዴት ሄዱ? በዚያ ያለ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዴት ጀመሩ?

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦  ለሥራ ተመድቤ ወደ ጣሊያን ሚላኖ ስሄድ የቃል ኪዳን ባለቤቴንና ሕፃናት ልጆቼን ሀገር ቤት ጥያቸው ነበር የሄድኩት፡፡ ነገር ግን ጊዜው እየገፋ ሲሄድ የቤተሰቤ ናፍቆት እንዲሁም በውጭ ሀገር ያለው የብቸኝነት ኑሮ እየከበደኝ ሄደ፡፡ ከኔ ጋር መጥተው አብረን እንድንኖር ይደረግልኝ ዘንድ በተደጋጋሚ ብጠይቅም ዛሬ ነገ በሚል ብዙ ጊዜ ወሰደ፤ እኔም " ከሙክት መካከል ከሚውል ቀበሮ ከልጆቹ ጋር የሚጭር ዶሮ ይበልጣል " እንዲሉ ከእግዚአብሔር የተሰጡኝ አደራዎቼ ናቸውና ስለ እነርሱ ስል ወደ አሜሪካን ጉዞ አደረኩ፡፡ አሜሪካን የገባሁት በእነርሱ ምክንያት ነው፡፡ 

አሁን የማገለግልበት የሴንት ሊውስ ደብረ ናዝሬት ቅደስት ማርያምና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታቸው በፀና ምግባራቸው በቀና በጥቂት ምእመናን የተቋቋመ ነው፡፡ እኔም አገልግሎት የጀመርኩት በዚያ ነው፡፡ ከአንድ ዲያቆን ጋር በመሆን በኪራይ ቤተ መቅደስ ብዙ ጊዜ ቀድሻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ዛሬ ተጨማሪ ካህናት እና  በርካታ ዲያቆናት አሉን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገዝተናል፤ ዕዳውንም ከፍለን ጨርሰናል ፤የሕዝቡም ቁጥር እጅግ በዝቷል፡፡ ሌላው በዚያው የተወለዱ እና ቋንቋችንን የማያውቁ ሕፃናት ግብረ ዲቁና ተምረው ክህነት ተቀብለው ያገለግላሉ፤ ዜማውን በግእዝ ንባቡን ደግሞ በእንግሊዘኛ ይጠቀማሉ ይልቁንም በሀገራችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል የኖሩ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሆኑ ዲያቆናት በሥራና በትምህርት ስለመጡ የቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት ከፍ አድርገውታል፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ ፦ በአጠቃላይ በሰሜን አሜሪካ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን ይመስላል ? እንደ ኦሃዮ ሀገረ ስብከትስ?

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦  አስቀድሜ እንዳልኩት በውጪ ሀገር ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት በሀገር ውስጥ ከአለው አገልግሎት የሚለየው በአገልግሎቱ፣ በእምነቱና በሥርዓቱ ሳይሆን በካህናቱና በምእመናኑ ቁጥር ብዛትና ማነስ እንዲሁም በጊዜውና በቦታው ነው፡፡ በሀገራችን በብዙ ካህናት የተለመደው አገልግሎት በዚያ አይገኝም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች በዛ ያሉ ካህናት ቢኖሩም በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ቁጥሩ አንድም ሁለትም ሊሆን ይችላል፡፡ የምእመናኑም ቁጥር እንደዚያው ነው በኑሮ በሥራ የተወጠረ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን ሀገሩን ቤተ ክርስቲያኑን ለመርዳት የሚሮጥ ጊዜ የሌለው ይሆናል፡፡ ቢሆንም ግን በትንቢተ ኤርሚያስ "በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጒርጒርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?" ት.ኤር ፲፫፥፳፫ እንደተባለው ተዋህዶ ሃይማኖቱን ቤተ ክርስቲያን እናቱን ይወዳል፡፡ ምእመናኑ በአንዳንድ ቦታዎች ቁጥራቸው ትንሽ ሆኖ ነገር ግን ከፍተኛ ሥራ ሠርተው ይታያሉ፡፡ በሰሜን አሜሪካ በትልልቁ ግዛቶችና ከተሞች ትልልቅ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ብዙ ካህናት፣ዲያቆናትና መምህራንም አሉ፡፡

 እኔ በአለሁበት ኦሃዮና አካባቢው ሀገረ ስብከት አስራ ስምንት አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ሁሉም ራሱን የቻለ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን አላቸው፡፡ በሀገራችን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በምእመናን አስተዋጽኦ ይሠራል በውጭ ሀገር ግን እንደዚህ አይደለም መጀመሪያ በኪራይ ወይም ደግሞ ሕንፃው ተገዝቶ ነው አገልግሎቱ የሚሰጠው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች መሬቱን ገዝተው ሕንፃውን የሠሩ አሉ፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ አብያተ ክርስቲያናት ከኪራይ ሕንፃ ወጥተው በራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማገልገላቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ በኪራይ ሕንፃ ማገልገሉ የሚያስከትለውን ችግር ይግለፁልን?

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦ የኪራይ ቤት እንኳን ለቤተ ክርስቲያን ለመኖሪያነትም ቢሆን ከባድ ነው ይልቁንም አከራይ የእምነቱ ተከታይ ከአልሆነ፤ እምነቱንና ሥርዓቱን ከአላወቀ  አሊያም የሌላ እምነት ተከታይም ከሆነ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡

ለምሳሌ ሕንፃውን ግማሽ ቀን አከራይተው ግማሽ ቀን ደግሞ ራሳቸው የሚገለገሉበት ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ በምንገለገልበት ጊዜ መንበሩን በቋሚነት ዘርግተን ፤የቃል ኪዳኑን ታቦት በቋሚነት ትተን፤ መጋረጃውን ዘርግተን፤ ነዋየ ቅድሳቱን አሟልተን እና በፈለግንበት ሰዓት ከፍተንና ዘግተን ለመገልገል እንቸገራለን፡፡  ሰዓት አሳጥሩ ፣ዕጣን አትጠኑ ፣ከበሮ አትምቱ . . . ወዘተ የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ ፡፡ ኪራዩን አቋርጠው ልቀቁ የሚሉበት ጊዜም ይኖራል፡፡ በእውነት ኪራይ ሲሆን ችግሩ ብዙ አይነት ነው፡፡

የራስ የሆነ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን እንዚህ ችግሮች ሁሉ አይኖሩም፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ በዕለተ ሰንበትም ሆነ በዘወትር በወርኃዊና ዓመታዊ በዓላት መስጠት ይቻላል፡፡ ምእመናንም ተረጋግተው ይገለገላሉ፤ ከታቦቱ እስከ ነዋየ ቅድሳቱ በክብር ይቀመጣሉ፡፡ 

አሁን በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የገዙና የሠሩ ናቸው ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ገንዘቡን ከፍለው የጨረሱ በመክፈልም ላይ የሚገኙ አሉ ከገዙትና ከፍለው ከጨረሱት መካከል አንዱ እኔ ያለሁበት ደብር ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን እንደ ነጋዴ ነግዳ አታተርፍም፤ እንደ ገበሬም አርሳ አታመርትም ትርፎቿና ምርቶቿ ካህናትና ምእመናን ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትስፋፋው በካህናትና ምእመናን ትብብርና ጥረት ፍቅርና አንድነት ነው፡፡ ሃይማኖታቸውን የሚወዱ ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ በገንዘባቸው በእውቀታቸው በጉልበታቸው ይታዘዛሉ፡፡ 

በተለይ ምሳሌ የሚሆናቸው ፣የሚያስተምራቸው መልካም አባት ወይም ካህንና መሪ ከአገኙ ለመልካም ነገር ይሽቀዳደማሉ፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ከካህናት የሚጠበቀው ብዙ ነገር ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይጠበቃልና፡፡ ይህ ማለት ግን ከምእመናን የሚጠበቅ ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ ፦ የቤተ ክርስቲያን (የክርስትና) ጉዞ በውጭው ዓለም በተለይም እርስዎ በሚገኙበት ሀገረ ስብከት ምን ይመስላል? አመሠራረቷን ጭምር ቢነግሩን፡፡

መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦ በመጀመሪያ እኔ ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ተስፋፋች እንጂ ተመሠረተች የሚል ሐሳብ የለኝም፡፡ መሠረቷ ያለው ገዳማቱ አድባራቱ ሊቃውንቱ ካህናቱና ምእመናኑ በአሉበት በኢትዮጵያ ስለሆነ ነው፡፡ በውጪ ሀገር በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአውስትራልያ፣ በእስያና በካራቪያን ደሴቶች በሌሎችም ቦታዎች ተስፋፍታለች፡፡  ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ከሁሉ በፊት ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የእግዚአብሔር መንገድና ጥበብ ለሰው የተገለጠ አይደለም ቤተ ክርስቲያን በተለያየ ምክንያት ብትቋቋምም አሁን በደረስንበት ላይ ሆነን ስናስበው እግዚአብሔር የወደደውና የፈቀደው ነገር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት መስፋፋት የመከፋፈል ውጤት ናቸው እላለሁ፡፡ በእርግጥ  ምክንያቱ ሊለያይ ይችላል፡፡ የአስተዳደር ፣ የሥርዓት፤ ሰዎች በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ሲለያዩ፣ በመንደር፣ በጎሳ ፣ በሥልጣንና በጥቅም በሲኖዶስም የተነሳ ሲጋጩ ወጥተው ቤተ ክርስቲያን ያቋቁማሉ፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን አንዲት እና የሁሉም ለሁሉም እንደሆነች ቢታወቅም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በውጪው ሀገር ልዩ ልዩ ስም ወጥቶላት  የእነ እከሌ ናት የእነ እከሌ አይደለችም የዚህ ዘር ናት የዚህ አይደለችም የውስጥ ናት የውጪ ናት በሚል ለባህርይዋ በማይስማማ ስም ስትጠራ ኖራለች፡፡ ይኽን ለዝከረ ነገር አነሳሁት እንጂ አሁን ሁሉም አልፏል፤ እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም ወደ አንድነት መጥቷል ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ሲሆን ያ ሁሉ መለያየት ጠፍቷል፡፡

እኔ በአለሁበት የኦሃዮና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከላይ እንደገልጥኩት ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ እና በውጪው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ ፡፡ አሁን ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ሆኖ እርቅ ከተፈፀመ በኋላ እግዚአብሔር ይመስገን በአንድ ሀገረ ስብከት ሥር ሆነናል፡፡ 

 

Read 243 times