Tuesday, 24 November 2020 00:00

“ከትናንቱ በመማር ዛሬ ላይ ጠንክረን ልንሠራ ይገባል” - መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ደሳለኝ  (የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ) ክፍል አንድ

Written by  እህተ ሚካኤል
በሀገሪቱ ከመጣው ለውጥ ጋር ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በሰው እና በንብረት ላይ ብዙ ጉዳት ደርሷል፤ብዙዎች የተወለዱበትን፣ ያደጉበትን እና የኖሩበትን አካባቢ ለቀው ተሰደዋል፡፡ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ብዙ የነበራቸው ባንድ ጀንበር ንብረት አልባ ሁዋል፡፡ ለዚህ መሰሉ ጥቃት ከተጋለጡት ውስጥ ደግሞ አንደኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መንግሥት በተለዋወጠ እና ሀገሪቱ ላይ አንድ ነገር በተከሠተ ቊጥር ግንባር ቀደም የጥቃት ዒላማ የምትሆነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ኋላ ሄዶ የመንግሥት ለውጥ ታሪካችንን ማየቱ በቂ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራን አሳልፋለች፡፡ በእሳቱ ውስጥ ካለፉ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ደግሞ አንዱ የምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በወቅቱ የደረሰውን የቤተ ክርስቲያን ጥቃትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሚከተለው አነጋግረናል ይከታተሉን፡፡   ስምዐ ጽድቅ ፦  አባታችን ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ስለፈቀዱልን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡  በቅድሚያ ሙሉ ስምዎትን ከየት እንደመጡና የአገልግሎት ድርሻዎትን ይግለፁልን መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ደሳለኝ፦ እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝና እንድናገር ስለፈቀዳችሁልኝ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡ መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ደሳለኝ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሲሆን የአገልግሎት ድርሻዬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ 

 

ስምዐ ጽድቅ ፦ የክርስትና አገልግሎትና አጠቃላይ እንቅስቃሴው በሀገረ ስብከታችሁ ምን ይመስላል?

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ የክርስትና አገልግሎትን በተመለከተ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ሥር ርእሰ ከተማው ሁለት ክልሎች ናቸው ያሉት፡፡ በርእሰ ከተማው የሀረሪ ክልል ሕዝባዊ መስተዳድር አለ፡፡ ከዚያ ውጪ ከአርባ አምስት በላይ የሚሆኑት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት  በምሥራቅ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው፡፡ 

እንደሚታወቀው ምሥራቁ ክፍል በአብዛኛው ኢአማንያን ወይም ሙስሊሙ እና ፕሮቴስታንቶች የሚበዙ ስለሆነ ያን ሁሉ ተጽዕኖ ተቋቁመን በተቻለ መጠን እንደ አቅማችን በስብከተ ወንጌሉም በሰንበት ትምህርት ቤቱም በመደራጀት በርእሰ ከተማውም ሆነ በገጠሩ ቤተ ክርስቲያን እየተንቀሳቀስን መንፈሳዊ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ምእመኑ በክርስትናው እንዲጸና ፤በአብዛኛው በሙስሊሙ ኅብረተሰብ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖች እንዳይጠለፉ እና ወደ ሌላ እምነት እንዳይሄዱ ስብከተ ወንጌል እየሰጠን እንገኛለን፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦   የሀገረ ስብከቱን የቤተ ክርስቲያን እና የክርስትና ታሪክ ቢነገሩን?

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ የሀገረ ስብከቱ የክርስትና ታሪክ ሲነሣ በሐረር ከተማ ላይ ክርስትናው ጥንታዊ ነው፡፡ በቀደመው ዘመን አባቶቻችን እነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሲመሩት በነበረበት ጊዜ ከዋናው ከቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በመላው ሐረርጌ ተብሎ ነበር የሚጠራው፡፡ ሐረርጌ ብፁዕነታቸው ሲመሩት የነበረ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ እነ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ቀዳሚው፣ እነ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ቀዳማዊው የመሳሰሉ ብፁዓን አባቶች ጭምር በመላው ሐረርጌ እየተባለ ሲመሩት የነበረ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ 

ጥንታዊና አንጋፋ ሀገረ ስብከት ነበረ፡፡ በአሁን ሰዓት ግን እንደ አንጋፋነቱ፣ እንደ ትልቅነቱ እንደ ቀድሞው አይደለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ መላው ሐረርጌ ተብሎ ባንድ ይጠራ የነበረው ሶማሊያ ሀገረ ስብከት ፣ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት፣ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፣ ምራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ተብሎ መከፋፈሉና በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙት በገጠሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የገቢውም አቅም አነስተኛ እንዲሁም ምእመኑ በአብዛኛው በሙስሊሙ መካከል ያለ በመሆኑ ነው፡፡   

ስምዐ ጽድቅ ፦ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት በተጀመረው ዘመቻ የጥፋት ዒላማ ከሆኑት ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የእናንተ ሀገረ ስብከት አንዱ ነበር እስኪ ስለዚያ ይንገሩን 

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ በ፳፻፲፪ ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ከጥቅምት የጀመረ የቤተ ክርስቲያን ጥቃት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ  በአርቲስት ሀጫሉ ሞት ምክንያት በኛ ሀገረ ስብከት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶአል፡፡ ከ፬፻፴፫ በላይ የሚሆኑ አባወራዎች ተፈናቅለው፤ ቤታቸው ተቃጥሎ ከ፮ ምእመናንን በላይ በመግደል፣  አስከሬናቸውን በመቆራረጥ እና መሬት ለመሬት በመጎተት ኢትዮጵያውያን ይፈጽሙታል የማይባል አፀያፊ ድርጊት የተፈጸመበት ቦታ ነው፡፡

 በተለይ ቦረዳ የምትባል ቦታ ላይ አቶ ዳመና የሚባሉ አባወራ ቤተ ክርስቲያንን የሚረዱ፤ ጠንካራ ክርስቲያን እና የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ  ከነቤተ ሰቦቻቸው ነው ያለቁት፤ አሰቃቂ ግድያ ነው የተፈጸመባቸው፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ ፦ ከሞት የተረፉትን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናን ከማጽናናት አንፃር በሀገረ ስብከቱ ምን ምን ሥራ ተሠርቷል? 

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ እኔም ሆንኩ ሊቀ ጳጳሱ በዚያ ወቅት ነበር ለሀገረ ስብከቱ የተመደብነው፡፡ ሆኖም በጊዜው የነበረውን መከራ በመቋቋም በተቻለ መጠን ወደ ምእመናኑ በመሄድ በቃለ እግዚአብሔር ከማጽናናት እና ከማረጋጋት ባሻገር ከሀገረ ስብከቱ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመርዳት ሞክረናል፡፡ ከዚያም አልፎ ጊዜና ሰአት እያመቻቸን በመሄድ ብዙ አጽናንተናል፡፡ ነገር ግን የተወሰኑት ምእመናን ተደራርቦ የመጣውን መከራ በመሰቀቅ እና ተስፋ በመቁረጥ ትንሽ ገንዘብ ያለው ቤቱን መሠረቱን እየነቀለ እየሄደ ነው፡፡ የተወሰነው ደግሞ ለጊዜው በዚህ ሰዓት ተረጋግቶ ነው ያለው፤ እኛም ከጎናቸው አልተለየንም፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ አካባቢውን እየለቀቀ የሚሄደው ክርስቲያን በቊጥር ይታወቃል ? ምን ያኽል ይሆናል?

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ እንግዲህ  ይኼን ያህል ተፈናቅሎ ሄዶአል ለማለት ዳታው የለንም፤ ነገር ግን የተወሰኑ ምእመናን ወደ አዲስ አበባ፤ ወደ ናዝሬት እና ወደ ደብረ ዘይት እንደገቡ በተወሰነ ደረጃ ሰምተናል፡፡ በአብዘኛው ግን በዚህ በሐረር እና በዙሪያው ያሉ ምእመናን ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው፤ብዙም አቅም ያላቸው አይደሉም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያችኑ የፈራረሰች ቤት እየጠገኑ ለመኖር ተገደዋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ በአጠቃላይ እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የተጎጂዎች ቊጥር ምን ያህል ይሆናል? የተያዘ መረጃስ አለ ወይ? ሀገረ ስብከቱ ከሰጠው እርዳታ ውጪ በመንግሥት? በግለሰቦች? የተደረገ ነገር አለ? 

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ በአሁን ሰዓት የተጎዱት እና በዝርዝር የያዝነው ዳታ ፬፻፴፫ አባወራዎች ናቸው፡፡ የእያንዳንዱን የወደመበትን ንብረቱን ጨምሮ የተመዘገበ ነው፡፡ ከእርዳታ ጋር ተያይዞ በዚህ በአዲስ አበባ የተቋቋመ እርዳታ የሚሰጥ ዐቢይ ኮሚቴ አለ፡፡ ተጎጂዎችን በማቋቋም ሂደት ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣትና እስከመጨረሻው ለመደገፍ  ፫ ቢሊየን ብር ተመድቧል፡፡ በወቅቱ ግን የተሰበሰበው አርባ ሚሊየን ብር ለጠቅላላ ተጎጂዎች ማለትም በሌሎች ሀገረ ስብከቶችም ሲከፋፈል እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የተሰጠው ፬ ሚሊየን ብር ነው፡፡ ለምእመናኑ የተሰራው ገንዘብ መቀበያ ቡክም ለ፪፻፸፰  አባወራዎች ብቻ ነው የተሠራው፡፡ የቀረው ምእመን ግን አልተሰራለትም፡፡ በዚህ የተነሣ እኛ የተላከልንን ፪፻፸፰ ቡክ ለማከፋፈል ተቸግረናል፡፡ ስለዚህ የተጎዳው ሳያገኝ ያልተጎዳው መለስተኛ ጉዳት የደረሰበት ቡክ ሲሰጠው እኛ ላይ ነው ችግሮች የሚፈጠሩት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተሟልቶ አንዴ ቢሰጥ የሚል ሐሳብ አቅርበናል፡፡ በእርግጥ በመንግሥት ደረጃም የተወሰነ እርዳታ እየደተረገላቸው ነው ቆርቆሮውንም ሚስማሩንም እንጨቱንም  እየተሰጠ ወደየ ነበሩበት ለመመለስ ተችሎአል፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ ጉዳት የደረሰባቸው ምእመናን ቊጥር የሚታወቅ ከሆነ ለምን ለ፪፻፸፰ አባወራዎች የሚሆን ቡክ ብቻ ተዘጋጀ? በጉዳዩ ላይ ተገናኝታችሁ ለመነጋገር አልቻላችሁም? ዐቢይ ኮሚቴው የሚያነሣው ምክንያትስ ይኖር ይሆን?

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ፦ በእርግጥ ምክንያታቸው አሳማኝ ነው፡፡ ዐቢይ ኮሚቴው መጀመሪያ ላይ ገንዘቡን ሲያቀርቡ  ለተጎጂዎች ለዘመን መለወጫ በዓል እንዲደርስ ተብሎ በችኮላ ነበር የተሠራው ፤ ከኛ ጋርም ግኙኝነት አልነበረም፡፡ አርባ ሚሊየኑን በራሳቸው ወስነው ነው ለተጎጂዎች ለመከፋፈል የሞከሩት የምሥራቅ ሐረርጌንም በራሳቸው ያገኙትን ዳታ መሠረት አድርገው ነው ቡኩን የሠሩት፡፡ እኛ የሰበሰብነውን የ፬፻፴፫ አባወራዎች መረጃ ሪፖርት የምናቀርበው በዋናው መሥሪያ ቤት በኩል ነው፤ እነሱ ብሩን ሲያከፋፍሉ መረጃውን ከኛ መውሰድ ነበረባቸው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ተጠይቆ መረጃ የሰጠው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡

የ፴፱ኛውን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጨረስን በኋላ የዐቢይ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ ሰብስበውን ነበር፡፡ እኛም በሀገረ ስብከቱ ላይ የደረሰውን አስከፊ ችግር የሕዝቡን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም ባቀረብነው ልክ አንዱ ከአንዱ ሳይለይ ለሁሉም ተጎጂዎች እኩል ቢሰጣቸው የሚል ሐሳብ አቅርበናል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ዐቢይ ኮሚቴው አርባ ሚሊዮኑን ከአከፋፈሉ በኋላ መጠባበቂያ ብለው ያስቀመጡት ፭ ሚሊየን ብር ብቻ ነው፡፡ ለኛም ”የተሠራውን ወደ ፪፻፸፰ ቡክ  ውሰዱና ለተራቡት ድረሱላቸው ከዚያ በኋላ ደግሞ በቀጣይ ስብሰባ ስላለን እናይላችኋለን“ የሚል ምላሽ ነው የሰጡን፡፡ በኛ በኩል በቂ መረጃ አቅርበናል  አጋጣሚ ይህን ከተረዱ ቢያደርጉልን ደስታውን አልችልም፡፡ ሆኖም ፪፻፸፰ ቡክ እንድንረከብ ግፊት እያደረጉ ነው ያሉት ያው መረከባችን አይቀርም፡፡   

ስምዐ ጽድቅ ፦ አሁን በቊጥር ከተያዘው ፪፻፸፰ ውጪ ያሉትንና የከፋ ጉዳት ላይ ያሉ ምእመናንን ለመደገፍ  በሀገረ ስብከት ደረጃ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? 

መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ፦ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በሀገረ ስብከቱ የሰላም ኮሚቴ ተብሎ የተቋቋመ ኮሚቴ ስላለ ዳታውን  አስተካክለው ሠርተውታል፡፡ ይኽ ኮሚቴ ዳታውን የሰበሰበው በእሳት ውስጥ አልፎ ነው፡፡ እጅግ አስቸጋሪና ውስብስብ ነበረ፡፡ በእኛ በኩል ችግር ያለባቸውን ለይተን ስም ዝርዝር አውጥተናል፡፡ ይኽን ዝርዝር ስናዘጋጅ ለምሳሌ የስም ዝርዝር ችግሮች ገጥመውን ነበር፡፡ የሰላም ኮሚቴው የስም ልውውጥም አድርገዋል ለምሳሌ በሞተም ሰው የተመዘገበውን በአለው ቤተሰብ ስም እንዲሆን ተደርጎ ተስተካክሎአል፡፡ ያንን ግን ሄደን ለማስፈረም ቢያንስ ከሀገረ ስብከቱ ወደ አንዱ ችግር ወደ ደረሰበት ቦታ ለመሄድ ከ፻ ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ለዚያ የሚሆን እና ለተለያዩ ነገሮች ወጪ ጠይቄ ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገረ ስብከቱ እንዲሸፈን የሚል ሓሳብ ነው የቀረበው፡፡ በእርጥ ሀገረ ስብከቱ ብዙ ነገር እየሸፈነ ይገኛል፤ብዙ ሥራም እየሠራ ነው፤ይሸፍን ከተባለ እንሸፍናለን ፤ነገር ግን  ቢያንስ የቀሩት ምእመናን ዳታ ተሞልቶ ቡክ እንዲሠራላቸው የሚል ጥያቄ አንስተንላቸዋል፡፡ ዐቢይ ኮሚቴው ይኽን ጥያቄ አስመልክቶ የተጠየቀው ዳታ ወደፊት እንደሚሞላ ወይም ደግሞ ወደ CCRDA የተባለ ድርጅት(ወደ እዚያ ድርጅት የገባ ገንዘብ ስላለ) እንደሚያስተላልፉልን ነው የመለሱልን፡፡ 

 

Read 580 times