Friday, 11 December 2020 00:00

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ዐረፉ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ከአባታቸው ከመምህር ቀሲስ ገብረ ሕይወት ወልደ ሐዋርያት እና ከእናታቸው ወይዘሮ ብርነሽ ቸኮል በቀድሞ የወሎ ክፍለ ሀገር ዋግ ሕምራ አውራጃ ተወለዱ። ብፁዕነታቸው በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ተዘዋውረው የቤተክርስቲያንን ትምህርት ጠንቅቀው ተምረዋል። ወደ ተለያዩ ውጭ ሀገራት በመሄድም የተለያዩ ትምህርቶችን ተምረው ያተጠናቀቁ ሲሆን በሩሲያ ሞስኮብ የቀድሞው ፒተርስበርግ በኋላ ሌኒንግራድ ዩኒቨርስቲ በሃይማኖተ አበው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። የማስተርስ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በነገረ ክርስቶስ ትምህርት ያገኙ ሲሆን  ዶክተሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በነገረ ሥጋዌ አግኝተዋል።  ቀጥሎም ወደ ሰሜን አሜሪካ በመሔድ በፕሪስተን ዩኒቨርስቲ በማስተር ኦፍ ቲዎሎጂ ዲግሪ ተቀብለዋል። ብፁዕነታቸው በምንኵስና የቅድስና ሕይወት ጉዞ የጀመሩትና ለታላቁ ማዕረግ እንዲደርሱ የእግዚአብሔር ጥሪ የደረሳቸው በ፲፱፻፷፩ ዓ.ም ሲሆን በዚህ ዓመት ወደ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም በመሔድ መንኰሰዋል። በመቀጠልም መስከረም ፮ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው  የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ዘመነ ፕትርክና ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅስና እና ቁምስናን ተቀብለዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራዶኦ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቀጥሎም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያና መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ ጥር ፬ ቀን ፲፱፻፸፪ ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ዶር አባ ኢያሱ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አባ ገብርኤል ተብለው የመንፈሳዊ ኮሌጅ ኤጲስ ቆጶስ (ዲን)፤ የድሬዳዋ እና አካባቢው ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሾሙ። በድሬዳዋ ሀገረ ሰብከትም ለአንድ ዓመት ያህል ከአገለገሉ በኋላ በ ፲፱፻፸፫ ዓ/ም የኤርትራ ክፍለ ሀገር ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለተከታታይ ሦስት ዓመታት አገልግለዋል።  ብፁዕነታቸው በአጠቃላይ ቤተክርስቲያንን በተለያዩ የአገልገሎት ዘርፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በትጋት ያገለግሉ ሲሆን። ከ፳፻፫ ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሲዳማ፣ ጌድኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞን ሀገረ ስብከት ተልከው እስከ ጥቅምት ፳፻፲፫ ዓ.ም ከላይ በተጠቀሱት። አህጉረ ሰብክት ተዛውረው በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ይገኙ ነበር።   ብፁዕነታቸው በጸበልና በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ከቀኑ ፭ ሰዓት በተወለዱ  በ፹ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም ቅዱስ ፓትርያሪኩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊዎች እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ኅዳር ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ከጠዋቱ በ፬ በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።   
Read 1082 times