ያሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት በተለይ በ፳፻፲፪ ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። ለዘመናት የመንግሥት ለውጥ በተደረገ ቁጥር የጥቃት ዒላማ ሆና የኖረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም በተመሳሳይ ሰቆቃን አሳልፋለች። ካለፉት ተደጋጋሚ ድርጊቶች በመነሣት ጠላቶቿ የመንግሥትን ለውጥ አለዚያም ትንሽ ግርግርን ተገን አድርገው ሊያጠቋት ሠይፍ ይዘው እንደሚነሡ ታዝበናል። ዛሬም እያስተናገደች ያለችው ይህንኑ ነው። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ምእመናንና ምእመናት፣ ሕጻናትና ወጣቶ፣ አዛውንቱና አረጋውያኑ፣ ካህናትም ሳይቀሩ ብዙዎቹ የወቅቱ የጥቃት ሰለባ ሆነው አልፈዋል። የሰውን ልብ የሚሰብር ግፍ የተፈጸመባቸው፣ ከቤት ከንብረታቸው የተፈናቀሉ፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ብዙዎች ናቸው። አብያተ ክርስቲያናቱ ተቃጥለው፣ ካህናቱ ተሰደው ተንገላተው ባቆሟት ሀገር ባይተዋር ሆነው አሳልፈዋል።
በዚያው መጠን በደረሰው ጉዳት እና ጥፋት ልክ ቤተ ክርስቲያን እና ልጆችዋን ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቁጥር ቀላል አይደለም። በየቦታው የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጥፋት በመከታተልና በማጋለጥ፤ ሊደርስ የሚችለውን የጥፋት ዕቅድም አስቀድሞ መረጃ በመስጠት ብዙ ሥራ ሠርተዋል። ለተጎዱት በመድረስ ጉዳታቸውን፣ኀዘናቸውን በመካፈል አለኝታ ሆነዋቸዋል። በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን መከራ ጮኸው ለዓለም አሳውቀዋል። በጊዜው ድምጽ ላልነበራቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ድምጽ ሆነዋል። ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ በግልም በቡድንም የተደረገው ርብርብ የነገን ተሰፋ የሚያጭር ለቤተ ክርስቲያን ኩራት፤ ለምእመናንም አርአያ የሆነ፣ ይበል የሚያስብል ሥራ ነውና ሊመሰገኑ ይገባል።
ስለ ክርስትናቸው ከቤተ ክርስቲያን ጥፋት በፊት ራሳቸውን አስቀድመው ሰማዕትነትን ስለተቀበሉት ምእመናን ‹‹ክርስትና ማለት ይህ ነው›› ብለው ለቀረነው ክርስቲያኖች ጽናት እንዲሆነን መስክረውልናል። በሕይወት ለቀሩት ነገር ግን በጥቃቱ በአንድ ጀንበር ንብረታቸው ለወደመባቸው ፣ ከነበሩበት ከፍተኛ የኑሮ ማማ ላይ ወርደው የሰው እጅ ተመልካች ለሆኑት ምእመናን ቀድሞ በመድረስ፤ የምግብ፣ የልብስ እና የገንዘብ ዕርዳታን በማድረግ የፈረሰ ቤታቸውን የሠሩ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ዋጋቸው በምን ይተመናል? የተቃጠለውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ከበፊቱ በተሻለ በመሥራት በፈረሰው በኩል የቆሙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእምነት እንዴት መቆም እንዳለብን አሳይተውናልና ሊመሰገኑ ይገባል።
የእምነት አርበኛ በሆኑት የቤተ ክርስቲያን ልጆች፤ በኅብረት እና በግል የተደረጉ እርዳታዎች፣ ለመልካም ነገር የተዘረጉ እጆች ባጠቃላይ ሰጪዎችን ብቻ ሳይሆን የተሰጣቸውን ተጎጂዎች በእምነታቸው እንዲጠነክሩ ነገን ተስፋ እንዲያደርጉ ያስቻለ በተግባር የተገለጠ ክርስትናን አሳይተውናል። ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፣ ስለተጎጂዎቹ ልጆችዋ የመንግሥትን ቸልተኝነት ፊት ለፊት ያጋለጡ፣ ጊዜ የሰጠውን አጥፊ ሳይፈሩ በክፉ ቀን ከቤተ ክርስቲያን ጎን የቆሙ ፣ ሳይሳቀቁ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን የጮኹ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች አርዓያዎቻችን ናቸው። በተለይም ነገን እንዴት መኖር እንዳለብን አሳይተውናልና የመንፈስ ጥንካሬያቸውን፣ መንፈሳዊ የዓላማ ጽናታቸውን አርአያ ልናደርገው ይገባል።
የጠላትን ዛቻና ጥፋት ሳይሳቀቁ ያጋለጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ከምእመኑ እስከ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከፊት ቆመው ጮኸዋል። በቃል ብቻ ሳይሆን ጥፋት በደረሰባቸው ቦታዎች ተገኝተው የምእመኑን ኀዘን ተካፍለዋል፣ ያላቸውንም በመስጠት ብርታት እና ጉልበት ሆነዋቸዋል። ስለቤተ ክርስቲያን መሥዋዕትነትን የከፈሉ ምእመናንን፤ ቤተ ክርስቲያን ለዘላለም ታስባቸው ዘንድ ‹‹የቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት ቀን›› ብለው ሰይመውላቸዋል። ዛሬ መልካም ዛፍን ተክለው የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ፍሬዋ እንዲበዛ አድርገዋል። በየቦታው ሲመቱት የሚጠብቅ ክርስቲያንን አንጸዋል፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዴት መኖር እንዳለብን ክርስትናን በተግባር አሳይተውናልና በክብር ሊዘከሩ ይገባል።
ቦታና ጊዜ ሳይገድባቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጆሮአቸውን የሰጡ፣ እጃቸውን የዘረጉ ከውስጥና ከውጭ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች የነበራቸውን ተሳትፎ በቀላሉ ማየት አይቻልም፤ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ነገር ማለት ነውና። በመከራ ውስጥ ያለፈችውን ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንዋን ለመታደግ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ከሕመሟ እንድትፈወስ፣ ከድካሟ እንድትበረታ፣ በጽናቷ እንድትቀጥል በማድረግ ለቀረው ምእመን የቤት ሥራ ሰጥተዋል።
ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጠውን መከራ ፊት ለፊት በመናገር ፣ በማስጠንቀቅ እንዲሁም ምእመናኑን በማጽናናት አባቶቻችን ያሳዩት ቁርጠኝነት ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ብርታት ሆኗታል። በቦታው ላይ በመገኘት ለምእመናን ያሳዩት አባታዊ ፍቅር እና ምክር የመልካም እረኝነትን ተግባር የገለጠ ነውና ሳይታሰብ መታለፍ የለበትም። ታላላቅ ጉባኤያትን በማዘጋጀትና በቦታው ላይ በመገኘት ለምእመናኑ አባታዊ ምክር በመስጠት ፣ በመባረክ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ የተወጡ አባቶቻችን፣ በቃለ ወንጌሉ ፣ በዝማሬ ሲያጽናኑ የነበሩ ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ለቤተ ክርስቲያን ባሳዩት ፍቅር ልክ ሊታሰቡ ይገባል።
በፈረሰው በኩል በመቆም ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ እንዳይቋረጥ ባጠቃላይ ምእመንዋ እንዳይበተንና፣ እንዳይጠፋ ባለበት ጸንቶ እንዲቆም የታገሉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። በተለይም የጥቃቱ ሰለባ የነበሩቱ ስአንዲትዋ ቤተ ክርስቲያን ተላልፎ መሰጠት እየሞቱ መኖር እየጠፉ መብዛትን አስተምረውናል። በሁሉም መንገድ ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ጋር አብረው መከራውን የተቀበሉ፣ የቁርጥ ቀን ልጆች ታላቅ መልእክት አስተላልፈውልናል።