Friday, 11 December 2020 00:00

''የመንታ እናት ተንጋላ ትሞት’’

Written by  ዲ/ን አሻግሬ አምጤ
ቤተ ክርስቲያን የሰላም በር ብትሆንም በየጊዜው በልዩ ልዩ ምክንያት በተከሠተ ጦርነት ስትለበለብ ኖራለች። ጦርነት አውዳሚ መሆኑን ተረድታ ክፉዎች በጥፋት ቀጥለው ዘለዓለማዊ ቤታቸውን እንዳያጡ ትጸልያለች። ጸሎቷም በዓለም ላይ አማናዊው ሰላም ይሰፍን ዘንድ ነው። ጦርነት በተከሠተ ጊዜ ግን ተዋጊዎች በአንድ በኩል ከለላ ለማግኘት በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ብለው ለማስጠቃት ቤተ ክርስቲያንን ይጠጓታል።  ከውጭ ወራሪ ጋር የሚደረግ ጦርነት ከሆነ ቤተ ክርስቲያን እንደ አገር  ለትውልድ ሥነ ልቡና መገንቢያ ተደርጋ ስለምትታሰብ በጦርነት ስትለበለብ ኖራለች። በመጀመሪያው ወረራው ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሽንፈትን ተከናንቦ የፈረጠጠው ፋሽስት ኢጣሊያ ለሁለተኛው ጊዜ አገራችንን ለመውረር ሲያስብ ለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ምክንያቱን አጥንቶ ቤተክርስቲያን መሆኗን ደረሰበት። ከጥናቱ በመነሣትም ቤተክርስቲያንን አንዷ የጥቃት ዒላማ እንድትሆን አድርጐ ክርስቲያኖችንና አብያተ ክርስቲያንን አወደመ። የአንድ እናት ልጆች በአንድ በኩል አገርን ለመታደግ በሌላ በኩል ደግሞ ለማፍረስ ከመጣው ፋሽስት ጋር በመወገን ኢትዮጵያን አወደሙ። የጦርነት ፍጻሜው እንዲህ ነው።   

 

በዚህ ምክንያትም ፋሽስት ኢጣሊያ ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ብቻ ከ፳፻ እስከ ፴፻፫፻ የሚደርሱ መነኰሳትን እንደፈጁ፣ ወደ ሞቋዲሾ እንዳጋዙና ታስረው እንዲሠቃዩ እንዳደረገ ኢያን ካምቤል የተባለ ጸሐፊ “The Masackre of Debre Libanose” በተሰኘው መጽሐፉ ገልጧል። በየዘመናቱ የተነሡ ወራሪዎችና ለጦርነት የተሰለፉ አካላት ቤተክርስቲያንን ለሁለት ነገር ሲጠቀሙባት ኖረዋል። የመጀመሪያው ክርስቲያን መስለው ሕዝበ ክርስቲያኑን ሰብስበው ለጦርነት ለመማገድ ሲሆን ሁለተኛው በጦርነት የሚሸነፉ ከሆነ ጠላት ደፍሮ ስለማይገባ ጊዜ መግዣ እናደርገዋለን፣ ጨክኖ ተኩስ ከከፈተም ከጦርነት ቀጠና ነፃ መሆን ባለባቸው ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት ፈጸመ ብለን ለዓለም ኅብረተሰብ ለማሳጣት ይመቸናል ብለው የሚፈጽሙት እኩይ ድርጊት ነው።

በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው ጦርነትም የአንድ አገር ልጆች በመሆኑ በሁለቱም ወገን ለጦርነት የተሰለፉ አካላት አብያተ ክርስቲያናትን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ሕፃናትንና ሴቶችን ዒላማ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚኖርባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት እየገለጡ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ተገን አድርገው ሌላውን ለማጥቃት የሚፈልጉ አካላትም ሆኑ ጠላት የሚሉት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ መስፈሩን እያወቀ ጦርነት የከፈተ በዓለማዊ ሕግም፣ በሞራልም የሚያስጠይቅ ነው። 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም “ችግር ሁልጊዜ አንዳንድ መልካም ነገሮችን ይዞ ይመጣል፤ የዘመኑ ወረርሺኝም በእኔ አስተያየት ሁለት ጥሩ ነገሮችን አስከትሏል፤ አንዱና ዋናው ከጃንሆይ በኋላ ተሽሮ የነበረው እግዚአብሔርን መልሶ በቦታው ማስቀመጡና በየመገኛዎች የእግዚአብሔርን ስም ማንሣት ተለመደ፤ ይህ ትልቅ ንቃት ነው፤ እግዚአብሔር ሁሌም በመንበሩ ላይ ነው፤ አይነቃነቅም፤ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተረስታ ወደጓዳ ተደብቃ ነበር፤ ዛሬ ጉልበትዋ በሙሉ ባይሆንም ታየ። 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዝናዋ አልተነገረም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለበትን ውለታ ገና በትክክልና በዝርዝር የተናገረው የለም፤ እንደተዳፈነ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተደግፈው የሚወጡ ሁሉ በሥልጣኑ ጣዕምና ሙቀት እዚያው ቀልጠው ይቀራሉ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለውነተኛ ተማሪዎች የሊቅነት ማዕርግ የሚያሰጣቸው ነው፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን  የትምህርት ሚኒስቴር ነበረች፤ የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ነበረች፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች፤ የባህልና የቅርስ ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች … በዛሬው ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተማሩ ሰዎች አላጣችም፤ እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያለው እንኳን ደፍሮ ጉልበተኞችን መጋፈጥ አልቻሉም” በማለት የገለጧት ቤተ ክርስቲያን አሁንም ለአደጋ ተጋልጣለች። ክርስቲያኖች እርስ በርስ እየተፋጀን መተላለቃችን አገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም። ለአደጋ የሚጋለጡት ክርስቲያኖች ናቸው። ክርስቲያኖች ተሰደው የሚሔዱትም በእምነት ወደ ማይመስሏቸው አካባቢዎች በመሆኑ ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል።

ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ኢሰመኮ በሰጠው መግለጫ መሠረት ትግራይ ክልል ማይካድራ በተባለች ከተማ በተፈጸመው የንጹሓን ዜጎች ጭፍጨፋ ብዙዎች ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት በጅምላ ተገለዋል። መግለጫው የተጎዱትን ማቋቋም እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጦ “በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው የማይካድራ ከተማ ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. በወቅቱ በሥልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የፀጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በንጹሓን ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን አስታውቋል።  መታወቅ የሚኖርበትም ለመግደል ከተሰማሩት ብዙዎቹ፣ ከሞቱትም ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸው ነው። ጦርነቱ በሕንፃ ቤተክርስቲያን፣ በቅርሶች፣ በአቅመ ደካሞች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ መጠንቀቅ ይገባል። እንደ ኮሚሽኑ መግለጫ ከኅዳር ፭ እስከ ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበት ግኝት ነው።   

ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችል ገልጧል።   የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፣ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ለወደፊቱም በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል።  የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፣ በዚህ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።  እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚያሳየን ኢትዮጵያውያን ጠበብ ካደረግነው ደግሞ ክርስቲያኖች እርስ በርስ እየተፋጀን መሆኑን ነው። ድርጊቱ ቤተ ክርስቲያንን የማይስማሙ ‹‹የመንታ  እናት ተንጋላ ትሞት›› የሚያስብል ነው።

 

Read 627 times