Friday, 11 December 2020 00:00

“በውጪው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች ሳይሆን ተስፋፋች እላለሁ” -መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ክፍል ሁለት

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል።  ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።       ስምዐ ጽድቅ፦ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት መምጣቱ መልካም ነገር ሆኖ ሳለ ምናልባት በውጪው ሀገር ለክርስትናው መስፋፋት መከፋፈሉን እንደ በጎ ልናየው እንችል ይሆን?  መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ፦  በምንም አይነት መለያየትን እንደ መልካም ነገር ልናየው አንችልም።  በተለይ የቤተ ክርስቲያን ሲሆን ደግሞ መለያየት ክፉ ነው ብዙ ጠባሳ ጥሎ ንፁሐንንም አቁስሎ ያልፋል።  በነበረው መከፋፈል የተነሳ በዓለም ላይ መሥራት የሚገባንን መንፈሳዊ ሥራ ሳንሠራ ቀርተናል፤ አገልግሎቱንም ጎድተናል፤ ሕዝቡን ለመናፍቃን ገብረናል፤ ብዙ ነገር አበላሽተናል።  የወላጆች መከፋፈል ለልጆች፤ የመሪዎችም መከፋፈል ለተመሪዎች ምን ያህል ችግር መሆኑ ይታወቃል።   እንግዲህ ይህንን ስናስብ መለያየትን ልንጠየፈው ያስፈልጋል።  ይኽ ደግሞ አጋጥሞን አልፏል፤ በታሪክ አጋጣሚ ይህንን አስተናግደናል፤ የምንወደውን ትተን የምንጠላውን ሆነናል፤ በወቅቱ በፓለቲካም ይሁን በቅዱስ ሲኖዶስ በዘርም ይሁን በሥልጣን ተበታትነን ሳለን ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ስላገኘን ይህንን ነገር እግዚአብሔር ለበጎ አድርጎት ይሆን? ብለን እንጠይቃለን ሰዎች ነንና እንዲህም እናስባለን ደግሞ እንመለስና እንዴት በእግዚአብሔር ፊት መለያየትን ለበጎ እንላለን? የሚል ሐሳብም ይመጣል።   በሀገራችን ጥንት ቤተ ክርስቲያን ይቋቋም የነበረው ያለው ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን ሲርቃቸው፣ ወንዝ እየሞላ ሲያስቸግራቸው፣ ሕፃን ታቅፈው ለማስጠመቅ፣ ሰው ሞቶባቸው ለቀብር ሲርቃቸው፣ በአካባቢያቸው ደብር እንዲኖራቸው በሚል ቅን ሐሳብ በስምምነት ነው እንጂ ተጣልቶና ተኳርፎ ተለያይቶ የሚሆን አይደለም በውጪ ሀገር ግን ሁሉም ባይሆኑም አንዳንድ ቦታ ያሉት የመለያየት ውጤቶች ናቸው።   አሁን የጥንቱ አንድነት ተመልሷል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ሆኗል፣ ቀደም ሲልም ልዩነቱ የጀመረው ከላይ ነበር አሁንም ከላይ ተስተካክሏል በተፈጠረው ልዩነት ስናዝን የነበርነው ካህናትና ምእመናንንም አሁን አንድ በመሆናችን ደስተኞች ነን።  

 

ስምዐ ጽድቅ፦ ቤተ ክርስቲያን በውጪው ዓለም ይበልጥ እንድትስፋፋ አሁን ምን እየተደረገ ነው ያለው? 

መልአከ ገነት በለጠ፦ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማጠናከር በየደረጃው ብዙ ጥረት ይደረጋል።  በተለይ በአንዳንድ አድባራት ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስ ወጣቶችንም ለማደራጀት እየተሠራ ነው።  በውጪ ሀገር ተወልደው ያደጉ ልጆች ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲማሩ ይደረጋል።  ብዙ አድባራት ለሕፃናት፣ ለማዕከላውያንና ለወጣቶች ለአዋቂዎች ጭምር ሥርዓተ ትምህርት  ቀርፀው ያስተምራሉ ለምሳሌ የእኔን ደብር ብጠቅስ በየሳምንቱ ቅዳሜና እሑድ ለሕፃናት፣ ለወጣቶችና ለአዋቂዎች በየደረጃቸው የሃይማኖት ትምህርት፣ የመዝሙር ጥናት እንዲሁም የቋንቋ ትምህርት ይሰጣል።   ብዙዎችም በዚህ ተጠቅመዋል በማስተማርም የሚያገለግሉ አሉ በርካታ ዲያቆናትም ያፈራነው ከዚያው ነው።  በዚህ አጋጣሚ በርካታ ዲያቆናትን በማስተማር ከፍተኛውን ሥራ የሠሩትን የደብራችን ካህን መጋቤ ሃይማኖት ዘለዓለም ጽጌን፤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ተተኪ የሆኑትን ወጣቶችንና ሕፃናትንም ጭምር በማስተማር የሚደክሙትን ወንድሞችና እህቶች ላመሰግን እወዳለሁ ከእኔ ይልቅ እነርሱ ይበረታሉ።  ቤተ ክርስቲያንም አለች እየሠራች ነው ማለት የሚቻለው ሕፃናትን ማዕከላውያንና ወጣቶችን ይዛ ለነገ ተረካቢ እንዲሆኑ ከአስተማረች ነው። 

ስምዐ ጽድቅ፦ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው አብሮ የመሥራት፣ ግንኙነቱና መተጋገዙ ምን ይመስላል?

መልአከ ገነት በለጠ፦ በውጪ ዓለም እንደ ሀገር ውስጥ አብያተ ክርስቲያናቱ በቅርብ ርቀት የሚገኙ አይደሉም።  ብዙዎቹ የሚገኙት በግዛት ደረጃ ነው ለምሳሌ እንደ ኮሎምቦስ፣ ቺጋጎ ባሉ ግዛቶች ውስጥ በርካታ አድባራት ይገኛሉ።  በሌላው ግዛት ደግሞ አንድ ደብር ብቻ ይሆናል።  ለምሳሌ በዚሁ ሀገረ ስብከት ሥር ያሉ ሌሎች ግዛቶች አንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ነው ያላቸው።  እና በጋራ ለማገልገል ሁልጊዜ የመገናኘቱ ነገር ከባድ ቢሆንም በበዓላት፣ በንግሥ ጊዜ የአንዱ ደብር ካህናትና ምእመናን ወደ ሌላው ደብር ጉዞ በማድረግ ከዋዜማው እስከ ክብረ በዓሉ ድረስ ማኅሌቱን፣ ቅዳሴውን ጠቅላላ አገልግሎቱን በጋራ ይሰጣሉ። 

አንዱ ያለ አንዱ ለብቻው አያከብርም ለዚህም ሲባል ብዙውን ጊዜ በዓላት የሚከበሩበት ቀዳሚት ሰንበት ነው።  እንዲህ የሚደረገው በዕለተ እሑድ በየደብራቸው አገልግሎት ስለአለ ሲሆን ከሰኞ እስከ ዓርብ ደግሞ ሕዝቡ በሥራ ላይ ስለሆነ ነው።  በሕብረት በአንድነት ማገልገሉ እያደገ መጥቷል በተለይ መለያየቱ ቀርቶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ከሆነችበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ይመስገን መቀራረቡ አለ።  በእርግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ በኩል ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል እርቅና አንድነት በሲኖዶስ ደረጃ ተፈፅሞ መቅረት የለበትም ወደ ታች ወደ ካህናቱ ብሎም ወደ ሕዝቡ ሊወርድ ይገባል።  ቀደም ሲል ካህናትና ምእመናን በነበረው መከፋፈል ለየብቻ ቆይተዋል እርቁ ሲመጣ ግን አባቶች በአንድነት ሲሆኑ ያንን መልሰው ወደ ሕዝቡ ማምጣት ነበረባቸው።  ይህንን ሐሳብ ያኔ በእርቁ ሰነድ ላይ አስቀምጠውታል ተናግረውታልም እኛም እንጠብቅ ነበረ።  በእርግጥ ያንንም ሳንጠብቅ እኛ ካህናቱ እርስ በርስ መነጋገር አንድነቱን፣ ሕብረቱን፣ መቀራረቡን እየፈጠርን ስለሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንዲት ሆናለችና እግዚአብሔር ይመስገን።  

ስምዐ ጽድቅ፦ በጋብቻ ሕግ ተወስነው የሚኖሩ ካህን ነዎትና እስኪ ስለ ቤተሰብዎ ይንገሩን?

መልአከ ገነት በለጠ፦ እውነት ነው በቅዱስ ጋብቻ ተወስኜ በትዳር የምኖር ካህን ነኝ።  ከባለቤቴ ጋር ያፈራናቸው አራት ልጆች አሉን።  ስማቸውም ዲያቆን ተዋሕዶ በለጠ፣ ሜላተ ወርቅ በለጠ፣ ወንጌል በለጠ እና ኖላዊ በለጠ ይባላሉ።   ባለቤቴ እጅግ የተባረከችና የተወደደች ሚስት ናት።  ስሟ  አብነት ነጋሽ ይባላል።  ለመንፈሳዊ አገልግሎቴ መሳካት ትልቅ ኃይልና ብርታት የምትሰጠኝ ልዩ ስጦታዬ በረከቴ ናት።   “ደግ ሚስትን ያገኘ ሞገስን አገኘ ፥ ከእግዚአብሔርም ደስታን ተቀበለ።” ምሳ ፲፰፥፳፪  እንዲል እግዚአብሔር በጎደለኝ በኩል ሊሞላልኝ እርሷን መርጦ እንደሰጠኝ አምናለሁ።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በአለኝ ሞያና በተሰጠኝ ፀጋ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ተዘዋውሬ እንዳገለግል፣ አርአያ ክህነቴን እንድጠብቅ በማድረግ በኩል የእርስዋ ድርሻ ትልቅ ነው። 

ጋብቻ ከመሠረትን ቆየን ሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ አክብረናል፤ አሁን ሃያ ሰባተኛ ዓመት ሊሆነን ነው።  ባለቤቴ በሕፃንነቷ የጀመረችው አገልግሎት ዛሬም 

 እናት ሆና በሰንበት ት/ቤት ልጆቻችንን ይዛ እያገለገለች ትገኛለች።  ሁሉም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አይለዩም በየደረጃቸው ያገለግላሉ። 

ስምዐ ጽድቅ፦  በአገልግሎት ዘመንዎ ውስጥ ገጠመኝ የሚሉት መልካምና መጥፎ ገጠመኝ ካለ ቢነግሩን

መልአከ ገነት በለጠ፦ እውነት ነው ማግኘትና ማጣት፣ ማዘንና መደሰት፣ መሾምና መሻር እነዚህ ሁለቱ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ሲፈራረቁ የሚኖሩ ናቸው።  

የሰው እድሜው መንፈቁ ለክብር መንፈቁ ለኃሣር ግማሽ ዕድሜው ለክብር ግማሹ ደግሞ ለመከራ ነው ሁልጊዜ አይደሰትም ሁልጊዜ ደግሞ እያዘነ አይኖርም።  

ከላይ እንደገለጥኩት እኔ በብዙ አድባራት በኃላፊነት ለብዙ ዓመታት አገልግያለሁ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱሳን ጸሎት እየረዳኝ በሰላም በፍቅር በምስጋና በሽልማት ነው የኖርኩት።  በዝውውር ተነስቼ ወደ ሌላ ደብር ስሔድ እንኳ “ይመለስልን” እየተባለ ነው የኖርኩት “መልካም ሀብት ሁሉ፥ ፍጹም ዕድልም ሁሉ ከላይ ነው፤. . .” ያዕ ፩፥፲፯ እንዲል መጽሐፉ ይህ ከእኔ የተነሳ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተደረገ ነው።  

መንፈሳዊ አገልግሎት በፍቅር ከአልሆነ ምንም ዋጋ እንደሌለው አምናለሁ፤ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር እወዳለሁ፤ እኔ ዝቅ ብዬ ሌላው ከፍ ቢል ደስ ይለኛል።  ተበድዬም እንኳን ስለፍቅር ይቅርታ እጠይቃለሁ ቅዱስ ጳውሎስ ፩ኛ ቆሮ ፰ ፥ ፲፫ “ነገር ግን በመብል ምክንያት ወንድሜ የሚሰናከል ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክል ለዘለዓለም ሥጋን አልበላም።” እንዳለው ሰውን አስቀይሜ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አልችልምና የእኔ ጥቅምና መብት መሆኑን እንኳ እያወኩ በዝምታ አልፈዋለሁ።  ባለማወቅ አይደለም ፤በሞኝነትም አይደለም እግዚአብሔር ለእኔ ያለውን እንደሚያደርግልኝ ስለማምን ነው።  ስለዚህ ብዙ ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም። 

ምንም ነገር ፈተናና ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም ማለት ግን አይደለም በእኔ ላይ የደረሰውን ያጋጠመውን (ያሳዘነኝን) ሳይሆን ለእኔ የደረሰውንና የሆነውን የእግዚአብሔርን አስገራሚ የሆነውን ድንቅ ነገር ሳስብ መልካሙ ነገር ሚዛን ይደፋልና እንዲሁ ስለአደረገልኝ ነገር ተመስገን እላለሁ። 

ስምዐ ጽድቅ፦ እንደሚያውቁት በሀገር ቤት ያለችው ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ዛሬ አይነቱ ብዙ የሆነ ጥቃት እየተፈፀመባት ነውና እርስዎ ስለዚህ ምን ይላሉ ? 

መልአከ ገነት በለጠ፦ በቅድሚያ በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰባቸው በሚገኘው ጥቃት ሞትና ስደት ከፍተኛ ኃዘን ይሰማኛል በክርስትናቸው የተነሳ ለሞቱት ወገኖቼ ነፍሳቸውን ይማር እላለሁ።  

በሰው ሀገር በባእድ ምድር የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ክብሯና መብቷ ተጠብቆ  በነፃነት ትኖራለች፤ አገልግሎቷንም በሚገባ እየሰጠች ትገኛለች በተቃራኒው ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በገዛ ሀገርዋ ላይ ስደተኛ እየሆነች ነው።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ባለውለታ ናት።  ታሪክ ሠርታና አቆይታ ያስረከበች፤ እውቀትን፣ ፍቅር አንድነትን ያስተማረች፤ ጠላት ወራሪን የመከተች ለሀገሪቱ ዳር ድንበር የዘመተች ብዙ ውለታ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት።  መጽሐፍ ቅዱስ” በግብፅ ዮሴፍን ያላወቀ ሌላ ንጉሥ ተነሣ “ዘፀ ፩ ፥፰   እንዲል በሀገራችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ውለታ የማያውቁ ሰዎች ተነስተዋል።  አንዳንዶች ያለ ስሟ ስም ያለ ግብሯ ግብር ሲሰጧት ይሰማሉ፣ ይታያሉ ።  ምዕመናንን የሚያሳድዱ፣ በጭካኔ የሚያርዱ፣ እሳት የሚያነዱ አሉ።  የምትጠፋ መስሏቸው ብዙ እየጣሩ ነው ፤ የጥምቀትና የደመራን በዓል ማክበሪያ ቦታዎቿን ሳይቀር እየነጠቋት ነው በርግጥ ሊያጠፏት የሚጥሩት ይጠፋሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ከቶም አትጠፋም የትላንት ታሪክ የሚነግረን ይኽን ሀቅ ነውና። 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይኽ ሁሉ ግፍ የሚደርስባት በደል ተገኝቶባት አይደለም ምናልባት በውስጥዋ የምኖረው እኔ ተሳስቼ  አጠፋ  ይሆናል  እንጂ  እርስዋ  የምትሳሳት  አይደለችም።  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ከኢትዮጵያ ለይቶ ማየት አይቻልም  የማይነጣጠሉ ናቸውና።  የሌሎች እምነት ተከታዮች ወደ ሀገራችን ሲመጡ “ግቡ ቤት የእንግዳ ነው” ብላ እጇን ዘርግታ የተቀበለችና ሀገር ያለማመደች ዛሬም ቢሆን  “ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ “ እያለች ለሀገር ለወገን ሰላምን ፍቅር አንድነትን ስጥልን ብላ የምትጸልይ ናት። 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተከብራ የኖረች ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ሆና ማየት እጅግ ያሳዝናል።  በብዙ ቦታ ካህናት ምእመናን ስማቸው እየታየ አድራሻቸውም እየተመዘገበ ተገደሉ፣ ተፈናቀሉ፣ አድባራቱም ተቃጠሉ፣ ሀብት ንብረታቸው እንዲወድም ተደረገ ሲባል ኃዘን ይሰማኛል፤ ልቤ ይሰበራል።  ይህ ችግር ወደፊት እንዳይቀጥል ከላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ  በሳልና ጠንካራ የሆነ ውሳኔና አመራር ይጠበቃል።  ቤተ ክርስቲያን የሰውና የታሪክ የሀብትም ድሀ አደለችም በመንፈሳዊም ሆነ በዘመናዊ እውቀት የበሰሉ ብዙዎች አሉአት እነርሱን ወደ ኃላፊነት ማቅረብ ካህናቱንና ምእመናኑም በሕብረት በአንድነት መምራት ያስፈልጋል።  ከእኛም ከካህናትና ከምእመናንም የሚጠበቅ ነገር አለ ከመለያየት ከመከፋፈል ርቀን ለአንዲት ቤተ ክርስቲያናችን በአንድነት መቆም ይገባናል።  

ስምዐ ጽድቅ ፦ በሰሜን አሜሪካ የኦሃዮና አካባቢው አህጉረ ስብከትን ወክለው የ፴፱ኛውን ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ለመካፈል ነው የመጡት ከዚህ ጉባኤ ምን አገኙ? 

መልአከ ገነት በለጠ፦ እውነት ነው ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ሀገረ ስብከቴን ወክዬ በ፴፱ኛው ዙር ዓለም አቀፍ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ነው።  በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣የሁሉም አህጉረ ስብከቶች ሥራ አስኪያጆችና የሥራ አመራሮች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች ተገኝተውበታል።  ሁሉም የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምቶና አክብሮ በመገኘቱ ደስ ብሎኛል ቤተ ክርስቲያን ስትጣራ መስማትና አቤት ብሎ መገኘት ጥሩ ነገር ነው እኔም የዚህ ታላቅ ጉባኤ ተካፋይ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ። 

በሌላ በኩል ዘመኑ ዘመነ ኮረና (COVID-፲፱ ) ስለሆነ ለሁሉም ነገር በተለይ ለመሰብሰብ ተቀራርቦም ለመነጋገር አስቸጋሪ ስለሆነ ያስፈራል የስጨንቃል ይህንን አውቃለሁ፤

ቢሆንም ወደ ስብሰባው ስመጣ ብዙ ነገር ተስፋ አድርጌ ነው የመጣሁት።  የምጠብቀው ብዙ ነገር ነበር ከሞላ ጎደል መልካም ነበር ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያንን ችግር፣ የክርስቲያኖችን ነገር በሚመለከት ሰፊ ጊዜ የሚሰጠውና ውይይት የሚደረግበት ሰፊ ክፍለ ጊዜ ይኖራል፤ ከስብሰባው ተካፋዮችም ልዩ ልዩ ሐሳቦች ይቀርባሉ እኔም የማውቀውን የሰማሁትንና ያየሁትን ችግርና የመፍትሔ ሐሳብ ጨምሬ እናገራለሁ ብዬ ነበር።  ነገር ግን የውይይት ጊዜ አልነበረም በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ከመላው ዓለም የሚመለከታቸው ተወካዮች ተገኝተዋል፤ የጉባኤው መሪና አስተባባሪ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለጉባኤው መዘጋጀት ብዙ ደክሟል፤  እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ብዙ የገንዘብ ወጪ አድርጓል፤ ተሰብሳቢዎች ሥራቸውን በመተው ተገኝተዋል፤ ምእመናንም ከዚህ ጉባኤ ብዙ ይጠብቃሉ። 

በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን በውስጥና በውጪ ለገጠማት ችግር የመፍትሔ አቅጣጫ ይነገርበታል፣ ይወሰንበታል ለቅዱስ ሲኖዶስም ትልቅ ግብአት ይሆናል ብዬ ነበር።  ለሁለት ቀናት የሁሉንም አህጉረ ስብከት ሪፓርት ሰማን ከውጪ ሀገርም እንዲሁ አደመጥን እግዚአብሔር ይመስገን እኔም ተራ ደርሶኝ የሀገረ ስብከቴን ሪፖርት በንባብ ለጉባኤው አቀረብኩ።  በእርግጥ የውይይይት ጊዜ ሳይሰጥና ሐሳባችንን ሳናካፍል ስብሰባው ቢፈጸምም ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት በጉባኤው ማጠቃለያ የቀረበው የአቋም መግለጫ የሁሉንም ሐሳብ የያዘና ችግሮችን አንስቶ የመፍትሔ ሐሳብ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያመላከተ ስለሆነ አሁንም የመጨረሻው አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የዚህን ታላቅ ጉባኤ ውሳኔ ተመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። 

ስምዐ ጽድቅ፦ በመጨረሻም የሚጨምሩትና ቀረ የሚሉት ነገር ከአለ? 

መልአከ ገነት በለጠ፦ አምሰግናለሁ በእውነት ማህበረ ቅዱሳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል፤ ገዳማትንና የአብነት ት/ቤቶችን በመርዳት፤ ካህናትንና መምህራንን በማፍራት፤ እውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን በመስጠት የሚሠራው መልካም ሥራ ብዙ ነውና እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ይጠብቅልን እላለሁ።  አሁን በአደረግነው ውይይት ቀረ የምለው ነገር የለም ነገር ግን የሚናገር ሰው ይስታል ዳህፀ ልሳንም ይኖረዋል በጎደለው እግዚአብሔር ይሙላበት ይህንን የሚያነቡ ወገኖች ሁሉ የጎደለውን እየሞሉና እያቃኑ እንዲያነቡት በትህትና እጠይቃለሁ።  

በተረፈ እንግዳችሁ በማድረግ ሐሳቤን እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ በልዑል እግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ።  

Read 246 times