Wednesday, 16 December 2020 00:00

ታስረው የነበሩ የመሎ ኮዛ አገልጋዮችና ምእመናን ከእስር ሊፈቱ ነው

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት የለሃ ደብር ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና አገልጋዮች ከእስር በዋስ ሊፈቱ እንደሆነ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ገለጡ፡፡  የለሃ ደብር ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ ዓመታት በበዓላት ማክበሪያ ይዞታነት ሲጠቀምበት የነበረውን መሬት የመሎ ኮዛ ወረዳ የመንግሥት አካላት “መሬቱ ይፈለጋል” በማለት መንጠቃቸውን ተከትሎ ምእመናን ‹‹የቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ ይከበር›› በማለታቸው ብቻ ለእስርና ገንዘብ መቀጮ እንደተዳረጉ ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡  በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር የቅዱስ ሲኖዶስ  ውሳኔን ይዘው ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ቢሮ ድረስ መሄዳቸውን የገለጡት ብፁዕ ነታቸው ከውይይታቸው በኋላ የታሠሩ ምእመናንና አገልጋዮች በዋስ እንዲፈቱና የተወሰደው የቤተ ክርስቲያን ይዞታም እንዲመለስ ርዕሰ መስተዳድሩ መወሰናቸውን አስረድተዋል፡፡  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሚያስፈጽሙ እንደነገሯቸው ያስረዱት ብፁዕነታቸው የታሰሩ ምእመናንና አገልጋዮች ሆnu የበዓላት ማክበሪያ ቦታው በቅርቡ መፍትሔ ያገኛሉ ቢባልም መቼ ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ እንዳላኙ ተናግረዋል፡፡  ከዚህ በኋላም ሀገረ ስብከቱ ተፈጻሚነቱን በቅርበት እንደሚከታተል የጠቆሙት ብፁዕነታቸው “ከዚህ ቀደም ጉዳዩ ጥቅምት !6 ቀን !)0፫ ዓ.ም መፍትሔ እንደሚያገኝ የተነገረን ቢሆንም የወረዳ ቤተ ክህነቱ የፍርድ ሂደቱን ለሀገረ ስብከቱ ባለማሳወቁ  ሂደቱ ተጓቷል” ብለዋል፡፡  በየሀገረ ስብከቱ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ብፁዕነታቸው ያነሱ ሲሆን “እኔ የምመራውን ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመመራት የሚፈጠሩ ችግሮችንና ስጋቶችን ከየአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በጋራ ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡   
Read 777 times