Saturday, 26 December 2020 00:00

የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሕንፃ እድሳት ተጠናቆ ተመረቀ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር
የአጤ ምኒሊክ መታሰቢያ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እድሳት ከተጠናቀቀ በኋላ በቅዱስነታቸው ተባርኮ ታቦተ ሕጉ ቅዳሜ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም   ወደ መንበረ ክብሩ ተመለሰ፡፡ በዕለቱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች ፣ የአድባራት እና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ካህናት እና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡   የገዳሙ ሕንፃ እድሳት ፵ ሚሊዮን ብር ያህል መፍጀቱን የሕንፃው አሠሪ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ በሀገር ውስጥ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውጪ በሰሜን አሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ከሚገኙ የቀድሞ የገዳሟ ካህናት አገልጋዮች እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ያካተተ ንዑሳን ኮሚቴን በማዋቀር በርካታ የገቢ ማባሰብ ሥራዎች መሥራት መቻሉ  ተጠቅሷል፡፡  በአንድ ዓመት ተኩል ሊጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የገዳሙ ሕንፃ እድሳት የኮቪድ-፲፱ ወረርሺኝ ባስከተለው ተፅዕኖ ምክንያት ሁለት ዓመታት ያህል መፍጀቱን ከሕንፃው አሠሪ ኮሚቴ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙና እንዲጎበኙ ከተመረጡ ዐሥር ቦታዎች ውስጥ አንዷ የሆነቸው የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ለዳግማዊ አጤ ምኒልክ መታሰቢያነት በልጃቸው በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ነው የተሠራቸው፡፡ በገዳሟ ሙዚየም ውስጥ አባቶቻችን አድዋ ይዘውት የዘመቱት መስቀል፣ ከውጪ ነገሥታት ለአጤ ምኒሊክ የተበረከቱ ስጦታዎች እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከ፻ ዓመት በኋላ እድሳት የተደረገላት የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የአጤ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱ፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲሁም የመጀመሪያው ግብፃዊ ጳጳስ የአቡነ ማቴዎስ አፅም እንደሚገኝባት ይታወቃል፡፡ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም በ፲፱፻፲ ዓ.ም ቦታውን የመጥረግ ሥራ በመጀመር የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ የግንባታው ሥራ ዐሥር ዓመታት የፈጀ ሲሆን በ፲፱፻፳ ዓ.ም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠናቆ ጽላቷን ከጎንደር በማስመጣት ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፳ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ መከበሩን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ 
Read 670 times