Saturday, 26 December 2020 00:00

የአዲስ አበባ ማእከል ለካህናትና መምህራነ ወንጌል ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ለካህናት፣ መምህራነ ወንጌልና ለስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ከታኅሣሥ ፲፫ ቀን !)፲፫ ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሥልጠና መስጠቱን የማእከሉ ትምህርተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ አማረ ምትኩ አስታወቁ፡፡  በሥልጠናው እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው ፪፻፵ ሠልጣኞች መካከል ፪፻፮ ያህሉ በሥልጠናው የተሳተፉ መሆናቸውን ያስታወቁት አቶ አማረ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች፣ መምህራነ ወንጌል፣ ካህናትና ክህነት የሌላቸው ነገር ግን በወንጌል አገልግሎት የተሠማሩ አገልጋዮች ተሳታፊ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡  እንደ ኃላፊው ገለጣ ሥልጠናው ከማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማእከል ስልታዊ ዕቅድ የተቀዳ ሲሆን ሦስት ሚሊየን አዳዲስ አማንያንንና ሦስት ሚሊየን ደግሞ ወደ ሌላ እምነት የሄዱትን መመለስ የሥልታዊ ዕቅዱ አንድ አካል በመሆኑ ስልታዊ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ  ወቅቱን የጠበቀ የመምህራነ ወንጌል ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብራት አስፈላጊ ናቸው፡፡  ሠልጣኞቹ በሥነ ምግባር የታነፁና ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን እንዲያፈሩ ለማገዝና ክብረ ክህነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ሥልጠና እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ማእከል ከ!)፲ ዓ.ም ጀምሮ ካህናትን በተለያዩ ደረጃዎች ሲያሠለጥን መቆየቱን አያይዘው ያነሡት ኃላፊው የዛሬው ሥልጠና ደረጃ ሁለት እንደሚባልም ተናግረዋል፡፡  ትምህርተ አበው፣ ኦርቶዶክሳዊነት እንዲሁም የተሰባክያንን ሥነ ልቡና መረዳት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለደረጃ ሁለት ሠልጣኞች ካህናት የተሰጠው ሥልጠና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ክብረ ክህነትን ጠብቆና አስጠብቆ ለማቆየት እንደሚያግዛቸው ኃላፊው አስረድተዋል፡፡  ሥልጠናው የአኀት አብያተ ክርስቲያናት የአገልግሎት ተሞክሮ ጭምር የዳሰሰና የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥን ያካተተ እንደሆነ ኃላፊው ገልጠው፤ የሥልጠናው ተሳታፊዎችም የሀገረ ስብከታቸውን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ተረድተው ወንጌልን እንዲሰብኩ፣ አዳዲስ አማንያንን አጥምቀው እንዲያጸኑ፣ ጉባኤ እንዲዘረጉ እንዲሁም የሊስተሮዎች፣ የወጣቶች፣ የወዛደሮች፣ የወታደሮችና የሴተኛ አዳሪዎችን ጉባኤያት እንዴት መምራት እንደሚችሉ ግንዛቤ ያስጨበጠ  ሥልጠና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  ከዚህ ቀደም ለካህናት አገልጋዮች በተሰጡ ሥልጠናዎችና አሁን በተሰጠው ሥልጠና የቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ወቅታዊ ሁኔታ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ኃላፊው አስረዳተዋል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት አክራሪዎች እየፈጸሙት ያለው ግፍ በዝርዝር ለተሳታፊዎች ቀርቦ የመፍትሔ ሀሳብ እንደቀርበ የስገነዘቡት ኃላፊው በሌላ በኩል ደግሞ ዓለማዊነት ምእመናንን እየወሰደ ያለው በምግባር ታንፀው ባለመያዛቸው መሆኑን አሰልጣኞቹ ለሥልጠናው ተሳታፊዎች እንዳብራሩላቸው ገልጸዋል፡፡ የደረጃ አንድ ሥልጠናዎች በቀጣይ ተጠናክረው በአጥቢያ ደርጃ እንደሚቀጥሉ ያስገነዘቡት ኃላፊው በቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልንም በብዛትና በጥራት ለማፍራት ዕቅድ መያዙን አብራርተዋል፡፡ ሥልጠናው በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያንን የሚያካትት ሲሆን ከሥልጠናው በኋላም የተለያዩ ሴሚናሮችን በማዘጋጀት የልምድ ልውውጦች እንደሚካሄዱ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡    ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በቦሌ ገርጅ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን መምህር የሆኑት መጋቤ ሐዲስ አክሊሉ አያሌው አኀት አብያተ ክርስቲያናት ያሉባቸውን ውስብስብ ችግሮች ተቋቁመው በጥንካሬ እንዴት እንደተጓዙና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም የገጠሟትን ሁለንተናዊ ችግሮች በምን መንገድ መሻገር እንዳለባት ግንዛቤ ያገኙበት ሥልጠና መሆኑን ተናግረው በቀጣይም ከሌሎች አገልጋዮች ጋር በመሆንም ለቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ይጠቅማል ያሉትን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡  በቃሊቲ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤልና ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን የጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ኪዳነ ማርያም ምንብየለት በበኩላቸው ምእመናን በክብር ተጠብቀው፣በሃይማኖታቸው ጸንተው፣በምግባራቸው ቀንተውና ይህንን ዓለም ንቀው ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ ከማድርግ ጋር ተያይዞ ለሚሠሩ ሥራዎች ሥልጠናው አጋዥ እንደሚሆናቸው የተናገሩ ሲሆን አያይዘውም ምእመናንን በያሉበት ቦታ ቤት ለቤት ተዘዋውሮ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለማስተማር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡   
Read 674 times