Saturday, 26 December 2020 00:00

ለቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ዘላቂ መፍትሔ ያሻል

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

የቤተ ክርስቲያናችን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ በተለያየ ምክንያት እና በተለያዩ አካላት መወሰድ ከጀመረ ሰንብቷል።  መወሰዱ ብቻም ሳይሆን ከነበረው መንፈሳዊ አገልግሎት በተቃራኒ ለተለያዩ አገልግሎቶች መዋል ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል።   ይህ የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን በየጊዜው የመንጠቅ ተግባርም ሥር እየሰደደ ሲሄድ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብት እያሳጣት በራሷ መብት ሌሎችን እየለመነች እንድትኖር አስገድዷታል።  ነገሩን እያረሳሳ  በሥውር  የሚካሄደው ይህ የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ይዞታን የመንጠቅ እኩይ ተግባር ሞቅ በረድ እያለ ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ ችግር ሲዳርጋት ኖሯል።  ይዞታው በተነጠቀበት ወቅት ብዙዎች ተነሥተው የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለማስመለስ ጥረት ቢያደርጉም የአንድ ሰሞን ብቻ ጩኸት ይሆንና ነገሩ ካለፈ በኋላ በመረሳት ተዳፍኖ ይቀራል።  በተለያየ ጊዜ እና በተለያዩ አካላት ለተለያየ ምክንያት ለተወሰዱ የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች የጃንሜዳው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ አንዱ ማሳያ ነው።  እንደሚታወቀው የጃንሜዳው በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በነበረው ጥረት ውስጥ የጥምቀት በዓልን የአከባበር ሥርዓት መንፈሳዊ ክዋኔ አስመልክቶ ናሙና የተወሰደበት ቦታም ጭምር ነበረ።  ብዙ ዓለም ዓቀፍ ጎብኚዎች የሚጎርፉበት የጥምቀት በዓል  የተቀመጠውን መሥፈርት አልፎ በዩኒስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ ቢመዘገብም ጃንሜዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ግን ለሌላ አካላት ተላልፈው ከመሰጠት አልዳኑም።   የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎቹ በስም የቤተ ክርስቲያን ቦታ መሆናቸው ከመነገር ውጪ ቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ቦታዎች ላይ የሰነድ ማስረጃ ስለሌላት ጉዳዩን እንዲከፋ አድርጎታል።  ከዚህም ባሻገር አንዱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሲወሰድ ጉዳዩን የአንድ ሰሞን ጩኸት ብቻ ማድረጉ ሌሎች ቦታዎች በተመሳሳይ እንዲወሰዱ እና የቤተ ክርስቲያን መብት ወደ ጎን እንዲገፋ ምክንያት ሆኗል።    በ፳፻፲፪ ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሠተው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ከፒያሳ የተነሡ የአትክልት ነጋዴዎች ወደ ጃንሜዳ ተዘዋውረው እንዲሠሩ በከተማው መስተዳድር መሰጠቱ ይታወቃል።  በጊዜው ቦታውን በምክንያት ለሌሎች መጠቀሚያነት ይሰጥ እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ በዓልዋን ስለምታከብርበት ሁኔታ እንዲሁም ስለቦታው አጠቃቀም የታሰበበት አልነበረም።  ይህንንም ለማለት የሚያስደፍረው አሁን ላይ ቦታው ሲለቀቅ የታየው ዘርፈ ብዙ ችግር ነው።  እስከ ችግሩም ቢሆን ቦታውን በእጅ ለማስገባት እና ዳግም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ ምእመኑ ድረስ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በግልም በማኅበርም በብዙ ታግለዋል።  የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም ይህንን ጥያቄ በቅንነት በመቀበል ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል።  ቦታውን ከማስለቀቅ ጀምሮ በማጽዳት ሥራ ተሳታፊ ሲሆኑም ታይተዋል።  ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።  ጉዳዩ ግን ቦታን በመመለስ ብቻ ሊቆም አይገባውም ባይ ነን።   የጃንሜዳው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታ በተመሳሳይ ለተወሰዱ የቤተ ክርስቲያን ቦታዎች አንዱ ማሳያ ነው።  የቀሩ እና ያልተመለሱ ቦታዎችን በመመለስ ብሎም ለነዚህ ቦታዎች ሕጋዊ ሰነድ ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ከመንግሥት ይጠበቃል።  ምክንያቱም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች በተለያየ ምክንያት ተወስደው ሳይመለሱ በመቅረታቸው በየአካባቢው ያሉ ምእመናን በየአጥቢያቸው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታ በማጣት ዛሬም እየተቸገሩ ነውና።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንዱ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ሲመለስላት በሌላ ቦታ ሌላውን እየተቀማች እስከ አሁን ድረስ  እያነከሰች ትገኛለች።   ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለ ሙሉ መብት የሆነችበትን እና ከጥንት ጀምሮ ስትጠቀምበት የነበረውን የራሷን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ይዞዎች ከሌሎች ልትጠይቅ አይገባትም።  በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁትንና በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ የተመዘገቡ እነዚህ የዐደባባይ በዓላት (መስቀልና ጥምቀት)ማክበሪያ ቦታዎች በመንግሥት ደረጃ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።  እነዚህ የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለሀገሪቱ ታላላቅ  የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በመሆናቸው የሚያስገኙት ገቢም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እጅግ ታላቅ ነው።  ስለሆነም መንግሥት እነዚህ በዓላት በሚከበሩባቸው ቦታዎች  ላይ የቤተ ክርስቲያንን ባለቤትነት ሊያረጋግጥላት ይገባል።   በተለይም የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን በዓላት  ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው እና ሀገርን  በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ በዓላት  እንደመሆናቸው መጠን ለበዓላቱ ተገቢውን ክብር በመስጠት ቤተ ክርስቲያን የምትጠይቃቸውን የባለቤትነት ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ሊያስመልስላትና መብቷን ሊያስከብርላት ይገባል።  በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ወቅት በቀል አካላት አንጡራ ሀብቷን መንጠቅ፤ የማክበሪያ ቦታ ማሳጣት ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መሆኑ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል።  በሀገሪቱ አንዳንድ ክልሎች እና አካባቢዎች የተጀመረው የቤተ ክርስቲያንን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች የማስመለስ ጅምር ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው።  ሆኖም ከዚህ መልካም ጅምር ጎን ለጎን መንግሥት ቦታዎቹን ሕጋዊ የማድረግ ሂደቱን በማፋጠን ቤተ ክርስቲያን ለይዞታዎቿ የሰነድ ማስረጃ የምታገኝበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራም ይጠበቅበታል።   ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ስትጠቀምባቸው በነበሩ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ  ተደርበው የተሰጡ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተነሥተው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ሊደረግ ይገባል።  ቀደም ብላ ቦታውን በማስከበር ስትጠቀምበት የነበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናትና።  ይዞታዋን ለሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ደርቦ መስጠቱ ውሎ ሲያድር ቤተ ክርስቲያንን ተጎጂ እያደረጋት መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው።  በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ መንግሥትም ሆነ ቤተ ክህነቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል።  ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊና  ባህላዊ ዕሴቶች የሚንጸባረቁባቸው፣ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌት የሆኑት የመስቀል እና የጥምቀት በዓላት የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆኑ የሀገርም ሀብት ጭምር በመሆናቸው በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።   ከላይ ለመጥቀስ ከተሞከረው በተጨማሪ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር መሥሪያ ቤትም ለሚታዩት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔን ከማሰጠት አንፃር ድርሻው የጎላ መሆን አለበት።  በየጊዜው በተለያየ ስም ከቤተ ክርስቲያን ላይ የሚወሰዱ እና የሚመለሱ ቦታዎች (ተነጥቀው የቀሩት ሳይረሱ) ሕጋዊ መሥመር የሚይዙበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ቤተ ክርስቲያን የይዞታው ባለቤት እንድትሆን ማስቻል ከሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ብዙ ይጠበቃል።  በተለያየ መንገድ የተደራጁ እና የቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ መብት ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ አካላት (ከግለሰብ እስከ ማኅበራት) የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎች ሕጋዊ እንዲሆኑ የጀመሩትን ጥረቶች ከዳር ሊያደርሱት ይገባል።  ቤተ ክርስቲያን ነገ እንደማንኛውም ባለይዞታ የምትታይበትን፣ ‹‹ይሄ እኮ የሷ ይዞታ ነው›› ተብላ የምትከበርበትን እንዲሁም በቦታዋ ላይ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንድትችል የባለቤትነት ካርታ የምታገኝበት መንገድ እስከመጨረሻው ድረስ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል።   ከዚያም ባሻገር በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ከአጥቢያ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በሙሉ ለዚህ የባለቤትነት ጥያቄ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን ሊቆሙ ይገባል።  በዓሉን ለማክበር ከውጭ ከሚገቡ ጎብኚዎች ባሻገር በበዓላቱ ወቅት ወደ ዐደባባይ የሚወጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ላሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ያላትን ቦታ ልትነጠቅ ሌሎች ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታዎችም ልታገኝ ይገባል።  ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስና በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት እያስገቡ በትጋት ሊሠሩ ይገባል።  
Read 548 times