Saturday, 26 December 2020 00:00

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከ፲፱፻፵፪ - ፳፻፲፫ ዓ.ም

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከልጅነት እስከ ዕለተ እረፍታቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነት አገልግለዋል።  ከአዲ አባት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የፊደል ትምህርት የሚጀምረው የልጅነት ሕይወታቸው መንፈሳዊውን የቤተ ክርስቲያን እውቀት ለመቅሰም ከተለያዩ ሊቃውንት ዘንድ ደርሰዋል፤ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረዋል።  ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪው ዓለም ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሰማራቻቸው ቦታዎች ሁሉ በመሄድ ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል።  ብዙ መጻሕፍትን በመጻፍ ለምእመናን እንዲደርሱ አድርገዋል፤ የሰንበት ት/ቤት፤ የስብከተ ወንጌል እና የአብነት ትምህርት ቤት አገልግሎት እንዲስፋፋ በሕይወት ዘመናቸው ብዙ ሰርተዋል።   ብፁዕነታቸው ከተወለዱበት ሚያዚያ ፭ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ.ም እስካረፉበት ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም መንፈሳዊ እድገታቸውንና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን፤ባጠቃላይ የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል መልካም ንባብ፦ የብፁዕነታቸው የልጅነት ሕይወት ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በቀድሞ በትግራይ ክፍለ ሀገር በሽሬ አውራጃ ፀለምት ወረዳ ውስጥ ልዩ ስሙ አዲ አባት ኪዳነ ምሕረት ደብር ከአባታቸው ከባላምባራስ አሳየኸኝ ነጋ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ሕይወት ረታ ሚያዚያ ፭ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ.ም ተወለዱ።  ፈሪሃ እግዚአብሔር ካደረባቸው፤ በጉልበታቸው እና በገንዘባቸው ቤተ ክርስቲያንን ያገለግሉ ከነበሩት ወላጆቻቸው በስዕለት የተገኙት ብፁዕነታቸው የያኔው አምኃ ሥላሴ ገና የአምስት ዓመት ሕፃን ሳሉ ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥተዋል።   ሕፃኑ አምኃ ሥላሴ በጣም የሚወዷቸውና ሲንከባከቧቸው የነበሩ ወላጅ አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ኀዘናቸው በጣም የመረረ እንደነበር ይነገራል።  ሆኖም  ለቤተ ክርቲያን የተሰጡ የስዕለት ልጅ ናቸውና በዚያ የጨቅላነት ዕድሜያቸው በሕልማቸውም ሆነ በእውናቸው የሚታሰባቸው የአበው መነኰሳት ሕይወት ነበረ፤ እንደነሱ ለመሆንም እጅግ ይመኙ ነበረ።   የብፁዕነታቸው የትምህርት ቤት ሕይወት ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ  የ፮ እና የ፯ ዓመት ልጅ እያሉ በዋልድባ አበረንታንት ገዳም ዙሪያ ከ፴‐፺ ኪሎ ሜትር እየተዘዋወሩ በርካታ መንፈሳዊ ትምህርት ተምረዋል።  በአቅራቢያቸው በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ከፊደል እስከ ንባብ ያለውን የልጅነት ትምህርት ከመምህር ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ተምረው አጠናቀዋል።    በ፲፱፻፶፱ ዓ.ም ጎንደር ድረስ በመሄድ ከብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የዲቁና ማዕረግ ተቀብለዋል።  ደብረ አባይ ገዳም በመግባትም የአብነት መምህር ከሆኑት ከየኔታ የኋላሸት ዘንድ ለአንድ ዓመት ተኩል መዝገበ ቅዳሴን ተምረው በ፲፱፻፷ ዓ.ም ከገዳሙ የእውቅና ሰርተፊኬት ተቀብለዋል።  ለዓመታት የዋልድባ የገዳም ቆይታቸው ሥርዓተ ምንኰስናውን እያጠኑ በረድዕነት ገዳሙንና ማህበሩን በከፍተኛ ደረጃ ሲረዱ ቆይተዋል።  ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም በተወለዱ በ፳፫ ዓመታቸው ከታወቁት ባለ አስኬማ ከባሕታዊ አባ ገብረ አረጋዊ ወልደ ገሪማ ማዕረገ ምንኩስናን ተቀብለዋል።  ኅዳር ፳፫ ቀን ፲፱፻፷፬ ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  እጅ በአክሱም ርእሰ አድባራት ወገዳማት የቅስና ማዕረግ ተቀብለዋል።   ቅስናን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ቀድሞ ገዳማቸው አበረንታንት በመመለስ በልዑክነት፣ በቄሰ ገበዝነት አበውንና ገዳሙን እያገለገሉ ከታላቁ መምህር የኔታ ገ/ኪዳን ወ/ሥላሴ ባህረ-ሐሳብ ተምረዋል።  ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እስከ ፲፱፻፸ ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የሥራ መስኮች እያገለገሉ ጎንደር ከምትገኘው ጥንታዊቷ ደብር ግምጃ ቤት ማርያም ከሚገኙት ከመምህር ወልደ ሰንበት መጽሐፈ መነኰሳትን ተምረዋል።  ከጎንደር ግምጃ ቤት ማርያም መጽሐፈ መነኰሳትን ከተከታተሉ በኋላ ወደ ገዳማቸው ዋልድባ ተመልሰው በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ገዳሙንና አበው መነኮሳትን አገልግለዋል።  ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም በመመለስም ከሊቀ ሊቃውንት መንክር ሐዲስ ኪዳንን ተምረዋል።  ሲመለሱም በአበው መነኰሳት ተመርጠው አዲስ አበባ ድረስ እየመጡ የገዳሙን ተግባር እያከናወኑ በአጠቃላይ በተማሪነት፣ በረድዕነት በመጋቢነት፣ በቄሰ ገበዝነትና በልዑክነት ለ፲፱ ዓመታት ዋልድባ አበረታንትን አገልግለዋል።   ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከገዳሙና ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያካበቱትን እውቀት ለማዳበር ወደ ኢሉባቡር በመሄድ በኢሉባቡር ሀገረ ስብከተ ከሚገኘው መቱ የካህናት ማሠልጠኛ ት/ቤት ገብተው የስብከት ዘዴ በዘመናዊ መልክ  ሲከታተሉ ቆይተው አብረዋቸው ሲማሩ ከነበሩት ፷ ካህናት መካከል አንደኛ በመውጣት በወቅቱ ከነበሩት ሊቀ ጳጳስ እጅ ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ተቀብለው  ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።  የብፁዕነታቸው የሥራና የአገልግሎት ሕይወት ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በዋልድባ አበረንታንት ገዳም  በረድዕነት በመጋቢነት፣ በቄሰ ገበዝነትና በልዑክነት ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተሰጠውን የአስተዳዳሪነት ፈተና ጥያቄ ከሰባት መነኰሳት መካከል ሁለተኛ በመውጣታቸው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በፈንታሌ ወረዳ በሚገኘው የመተሐራ አንቀጸ ሰላም መድኃኔ ዓለም ገዳም በአስተዳዳሪነት ተሹመው አገልግለዋል።       በመተሐራ አንቀጸ ሰላም መድኃኔ ዓለም ገዳም በሦስት ዓመት የአገልግሎት ዘመናቸው ባሳዩት የሥራ ፍቅር ከጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፹፭ ዓ.ም ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን/ገዳም/ አስተዳዳሪ በመሆን ተሹመው አገልገለዋል።  በመቀጠልም ወደ ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በመዛወር ከየካቲት ፲፱፻፹፭ እስከ የካቲት ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለ፩ ዓመት አገልግለዋል።  ከየካቲት ፲፱፻፹፮ ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተዛውረው የመንሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ሞግዚት ሆነው የገዳማዊ ዕውቀት ግብረ ገብነትና ትህትናን አስተምረዋል።    ከኅዳር ፳ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ.ም እስከ ሰኔ ፳ ፲፱፻፹፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ፣ በሊቀ ሥልጣናት ማዕረግ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ፣ከመጋቢት ፩ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም  እስከ  ኅዳር ፲ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም  ዋና አስተዳዳሪ ፣ ከኅዳር ፲ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲፩ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ፣ በሀገር ውስጥ ያለው ኀላፊነታቸው እንዳለ ሆኖ  ከሰኔ ፳ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲፱፻፺፩ ዓ.ም በጅቡቲ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በመሾም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት አገልግለዋል።  ከጅቡቲ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ከየካቲት ፩ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ጀምሮ ምዕረገ ጵጵስናን እስከተቀበሉበት ሐምሌ ወር ድረስ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። ማዕረገ ጵጵስና ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከረጅም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን የትጋት አገልግሎት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም በኤጲስ ቆጶስነት መርጧቸው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ አባ ኤጲፋንዮስ በሚል ስያሜ ማዕረገ ጵጵስናን ተቀብለዋል።   ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ማዕረገ ጵጵስናን ከተቀበሉ በኋላ በሀገር ውስጥ በሸካ ቤንች ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ እንዲሁም በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም በደቡብና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን አገልግለዋል።  ብፁዕነታቸው ከሀገር ውስጥ አገልግሎት በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን በውጪው ዓለም ካቋቋመቻቸው አህጉረ ስብከት ውስጥ በየመን ሰንአ፣ በሊባኖስ ቤይሩት፣ በጣልያን ሮም፣ በኢየሩሳሌም፣ በደቡብ አፍሪካና በግብፅ ካይሮ እየተላኩ ምእመናንን አጽናንተዋል፤ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል።  የብፁዕነታቸው የኅትመት ሥራዎች ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከታላቁ ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ከመግባታቸው በፊት በትውልድ ቀያቸው በምትገኘው አዲ አባት ኪዳነ ምሕረት የተለማመዱትን የመንፈሳዊ ሕይወት ወደ ደብረ አባይ ሄደው በርካታ መንፈሳዊ ትምህርት አካብተዋል።  ይህንኑ የተማሩትን ትምህርት ለሌላው ለማካፈልና ለማስተማር በነበራቸው ትጋትና ጥረት ጥቂት የማይባሉ መጻሕፍትን በመጻፍና በማሳተም ለቤተ ክርስቲያናችንና ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው አበርክተዋል።    ፍኖተ ሃይማኖትና ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤  ክህነትና አገልግሎቱ፤ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሃይማኖተ አበው አስተዋጽኦ፤ ፍሬ ጸሎት ወንስሐ መጽሐፈ መነኮሳት የተሰኙ መጻሕፍት ጥቂቶቹ ናቸው።  ብፁዕነታቸው በልማት ሥራዎች ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በነበሩበት የሕይወት ዘመን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም፣ ምእመናንን የሚያንጽ መንፈሳዊ አገልግሎትን የሚያሰፋ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን ማከናወናቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።  በተለይ የነበራቸው የጸሎት ሕይወት፣ የመንፈሳዊ አባትነትና ትሕትናቸው በብዙዎች ዘንድ የመወደድ ፀጋን አላብሷቸዋል።  ለሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት መሳካት ምሥጢሩም  ፍጹማዊ ሕይወታቸው አንዱ ሲሆን ሌላው የተለያዩ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎችን፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን እና በሀገር ቤት የሚገኙ ባለሀብቶች የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው የማስተባበር ፀጋ እንዳላቸው ይነገርላቸዋል።  ብፁዕነታቸው በተመደቡበት አህጉረ ስብከትና አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከፍተኛ የልማት ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።  በደቡብ ምዕራብ ሸዋና በምዕራብ ሸዋ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የካህናት ማሰልጠኛ አዳሪ ት/ቤቶች፣ የሕፃናት መርጃ (ዕጓለ-ማውታ)፣ ክሊኒክና ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማሳነጽ በዚህ አጭር ጊዜ መግለጽ የማይቻል የልማት ሥራ አከናውነዋል።  በተለይ  በሰሜን ምዕራብ ወረዳ በፀለምት የእምባ ድኩላ አቡነ አረጋዊ እና የአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቤተ ክርስቲያንን በግል ገንዘባቸው አሳንጸው ለምእመናን እና ምእመናት እንዲገለገሉበት በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ኀላፊነታቸውን የተወጡ ታላቅ አባት ነበሩ።    ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የሥራ ክቡርነትን የተረዱ፤ ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን ፍፁም ፍቅር የነበራቸው፤ ከምንም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ የጸሎት ሰው መሆናቸው፣ ግብረ-ገብነታቸው፣ ለሌላው ያላቸው የመልካም ምሳሌነት፣ ሰውን ሁሉ መውደድና ካላቸው ሁሉ ማካፈል የሚወዱ መሆናቸው፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ያላቸው ምሳሌነት ከቤተ ክርስቲያን እና ከምእመናን ልብ የማይጠፋ ሕያው ታሪክ ያላቸው አባት እንዳደረጋቸው ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ይቻላል።  ብፁዕነታቸው መንፈሳዊ ሕይወትን በተግባር የኖሩ፤ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን የበረከት ዕድሜ በሙሉ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ያዋሉ ጠንካራ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ነበሩ፤ ‹‹ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ሰው ማነው?›› መዝ ፹፰፥፵፰ እንዳለ ዳዊት በመዝሙሩ በነበራቸው የሕይወት ዘመን ቤተ ክርስቲያንን በብዙ መልኩ አገልግለው እና ከቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ልብ የማይጠፋ ታላቅ ሥራ ሠርተው ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በተወለዱ በ፸፪ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።  የብፁዕነታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍ ለቤተ ክርስቲያን እና ለምእመናን ጥልቅ ሐዘን ቢሆንም ያከናወኗቸው በጎ ተግባራት ህያው ናቸውና በዚህ እንጽናናለን።    በረከታቸው ይደርብን!  
Read 856 times