Saturday, 26 December 2020 00:00

“ጦርነቱ ምእመናንን በሞት፣ በአካል ጉዳትና በስደት እየነጠቀን ይገኛል”

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በዚህ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ  ጦርነት መቀስቀሱን ሰምተናል፤ በሚዲያም አይተናል።  በጦርነቱም በሁለቱ ወገን  የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ሀብት ንብረት ወድሟል።  ይህ ድንገተኛ ጦርነት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ የጎላ ጉዳት እንደሚያመጣ ይታወቃል።  ጦርነቱ በቤተ ክርስቲያንና  በምእመናን  ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ም/ኃላፊ  ከሆኑት ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ ጋር አጭር  አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።  መልካም ንባብ።   ስምዐ ጽድቅ፡- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ምን ዓይነት ተፅእኖ ይኖረዋል ይላሉ? ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡-  የትም ቢሆን ጦርነት አስከፊ እንጂ መልካም ገጽታ የለውም።  ሁሉም ሰው እንደመረዳት አቅሙ የጦርነትን አውዳሚ ገጽታ ይረደዋል።  ሰሞኑን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በጣም አሳሳቢ ነው።  ጦርነት ሰዎች በራሳቸው ፍላጎት የሚያመጡት ሰው ሰራሽና ሰው ጨራሽ ድርጊት ነው።   ጦርነት የሰውን ልጅና ዓለምን ያወድማሉ ከሚባሉ ክፉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።  አስከፊና አሳዛኝም ክስተት ነው።  ጦርነት ሞትን ብቻ የሚጠራ ሳይሆን ሳንሞትም እንደሞትን እንድናስብ አድርጎ የሚያኖረን አውዳሚ ተግባር ነው።  ትልቅ ጠባሳን ጥሎም የሚያልፍ ነው።   ጦርነት በሥጋ ብቻ ሳይሆን በነፍስም ይጎዳል፤ ምክንያቱ በጦርነት ጊዜ አንዱ አንዱን ይገድላልና።  ሀገራችን ኢትዮጵያ የእርቅና የሽምግልና ጥሩ እሴት ባለቤት ሀገር ብትሆንም በየጊዜው እሴቶቻችንን ወደጎን በማለት ሀገሪቱ በጦርነት እንድትታመስ እየተደረገ ይገኛል።  ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ ከሽምግልናና ከእርቅ የዘለሉ አልነበሩም።  አሁን በዚህ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክልል እየካሄደ ያለው ጦርነትም ነገሩ በሽምግልና ማለቅ የነበረበት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ሄዶ ወደ ለየለት ጦርነት ተለውጧል።  ይህ ጦርነት ከመንጋው መካከል ያሉ ምእመናንን በሞት፣ በአካል ጉዳትና በስደት እየነጠቀን ይገኛል።  ጦርነቱ መንጋውን ከመንጠቁ በተጨማሪ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባቸው እንዲሁም የምእመናን ተስፋ የሆኑ አብያተ ክርስቲያት ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል፤ አንዳንድ ሀገራዊና ታሪካዊ ቅርሶች ደግሞ በሥጋት ውስጥ ይገኛሉ።  ይህ የጦርነት ክፉ ገጽታው ነው።  በጦርነት ጊዜ ምእመናን መሞታቸው አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ መቃጠላቸው አይቀሬ ነው።   በሁለቱም ክፍል በጦርነቱ እየተሳተፉ ካሉት አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናቸው።  ገዳዮችም ሟቾችም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።  ከሚጠፋው ሕይወት በተጨማሪ የሕዝበ ክርስቲያኑ ሀብትና ንብረት በአንድ ጀንበር እየወደመ ነው።  ይህ ጦርነት ነገ የማንተካቸው በአባቶቻችን የረቀቀ ጥበብ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናትን ጭምር ያጠፋል።  በጦርነቱ መሀል የጦርነቱ አካል የሆኑ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኗን መደበቂያ ሊያደርጓት ይችላሉ።  በዚህን ወቅት የመንግሥት ኃይል የተደበቁ ዓመፅያንን ለማጥፋት ሲሞክር ቤተ ክርስቲያንም ትጎዳለች።  በሌላ ሁኔታም ቤተ ክርስቲያን የወንበዴና የአጥፊዎች መሸሸጊያ ሆናለች የሚል ወቅቱን ያላገናዘበ ስያሜ ሊያሰጣት ይችላል።  የጦር መሣሪያ መከማቻ ሆናለች ልትባልም ትችላለች።  ነገር ግን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የገባ ኃይል መሣሪያውን አስረክቦ ከነፍሰ ገዳይነት ርቆ መጀመሪያ እጁን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ንስሐ ቢገባ ምልካም ነው።  ቤተ ክርስቲያንም የሽፍቶች፣ የነፍሰ ገዳዮች፣ የአማፅያንና የአረመኔዎች መደበቂያ መሆን የለባትም፤ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያናቸውን መጠበቅ አለባቸው።   ስምዐ ጽድቅ፡- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናን ለመርዳትና ለማጽናናት ምን ታስቧል? ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- የተፈናቀሉና ጉዳት የደሰባቸውን ምእመናን ማቋቋምና ማጽናናት ቤተ ክርስቲያኗ ቅድሚያ ሰጥታ የምትሠራው ሥራ ይሆናል።  ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ማድርጓ ይታወቃል።  ይህ ድንገተኛ ጦርነት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲፈጸምባት የነበረው በደል አድጎ ነው ወደለየለት ጦርነት የተቀየረው።  ምንጊዜም ጦርነት በመጣ ቍጥር በዋናነት ቤተ ክርስቲያንና ልጆቿን ነው የሚጎዳው።  በዚህ ጦርነትም በርካታ ምእመናን ተገድለዋል፤ ታርደዋልም።  ይህ ጦርነት እንዳይመጣ ቤተ ክርስቲያን አስቀድማ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ስታውጅና ስትጸልይ ቆይታለች፤ ወድፊትም ትጸልያለች።  የማስታረቅ ሥራም ለመሥራት ሞክራ ነበር።  ነገር ግን በሁለቱም ወገን ወደ ዕርቅ ለመምጣት ፈቃደኞች አልሆኑም።  ፈቃደኞች ባለመሆናቸውም ምክንያት ጦርነቱ ተከሰተ።  በዚህም ምእመናን ተፈናቀሉ፤ ሞቱም።  ምእመናን በሃይማኖትና በቋንቋ ወደ ማይመስሏቸው ሀገራት በመሰደድ በእንግልት የታጀበን ኑሮ መምራት ጀምረዋል።  የተሰደዱ ምእመናን መመለስና ማቋቋም የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው።  ምእመናንን በመመለሱና በማቋቋሙ ሂደት ላይ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት አካላት ጋር በጋራ ትሠራለች።   ስመዐ ጽድቅ፡- አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነት አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ቤተ ክርስቲያን ምን እየሠራች ነው?  ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- ሁሉም ሃይማኖታዊ ቅርሶች የቤተ ክርስቲያናችን ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥትና የሀገር ሀብቶች ናቸው።  ቅርሶችን ጠብቆ ማቆየትና ከጉዳት መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው።  ዓማፅያን ቤተ ክርስቲያንን መደበቂያ ሊያደርጓት ይችላሉ።  በዚህን ወቅት መንግሥት ተፈላጊ የሆኑ አማፅያንን ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሶች ጉዳት በማይደርስባቸው ሂደት ሊሆን ይገባል።   መንግሥትም አስቦ ወይም በቸልተኝነት በቅርሶች ላይ ጉዳት እንዲደርሰባቸው ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም።  ነገር ግን ቅርሶች በድንገት ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችልም ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው።  የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።  ስለዚህ ሀገር ከቅርሶቹ የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ መንግሥት የቻለውን ያህል ቅድመ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።  ምእመናንም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን በቅርሶች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።  መንግሥት በበኩሉ የሕግ ማስከበር ሂደቱን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እያከናወነ እንደሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሲሰጥ ተስተውሏል።  እስካሁን ድረስም በግልጽ የታወቀ በቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት ያለመኖሩን ተረድተናል።   ጥንታዊ ገዳማትና አድባራትን ከመጠበቅ በተጨማሪ ንጹሐን ዜጎች የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ጭምር መንግሥትን የማሳሰብ ሥራ እየተሠራ ነው።  መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት ሸሽተው ወደ አጎራባች ሀገራት የሄዱ ኢትዮጵያውያንም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ወደአካባቢያቸው ተመልስው የቀደመ ኑሯቸውን እንዲመሩ እንዲያደርግ መልእክቶች ተላልፈዋል።   እስኪመለሱ ድረስም በያሉበት አካባቢ አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተጠይቋል። መንግሥትም የተጠየቀውን ተቀብሎ ወደተግባር በመለወጥ ዜጎቹ ዘላቂ ሰላም እንዲያገኙ እየሠራ እንደሆነ ገልጧል። ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ሂደቱን የሚከታተል ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግሥት ጋር በጋራ የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች።   ስመዐ ጽድቅ፡- ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት በመንግሥት ቀጥተኛ ትእዛዝ እንዲዘጉ እየተደረገ ነው።  ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?  ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- አብያተ ክርስቲያናቱና ገዳማቱ እንዲዘጉ የተደረገው መንግሥት የፀጥታ ሥጋት አለ በማለቱ ነው።  ቤተ ክርስቲያን በዚህ ደረጃ የፀጥታ ሥጋት ምንጭ ትሆናለች ተብሎ አይታሰብም።  ነገር ግን አንዳንድ ሰርጎ ገቦች ወቅቱን ምክንያት አድርገው የቤተ ክርስቲያን ክብር እንዲነካ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ።  የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የፀጥታ ሥጋት መፍጠር ሳይሆን ዓለም የፀጥታና የሰላም ምንጭ እንድትሆን ማድረግ ነው።  ከዚህ ውጭ የሆነ ዓላማ ሁሉ ሰይጣናዊ እሳቤ ያላቸው ግለሰቦች እንጂ ሰማያዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አይደለም።   ሰዎች ከቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ ውጭ የሆነ ተግባርን በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።  ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ዓለማዊ እንዳልሆነችና ከዕኩይ ተግባር የራቀች መሆኗን ለመንግሥትም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስረዳት አለበት።  ጉዳዩ የተከሰተው በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ባሉ አጥቢያዎች በመሆኑ ሀገረ ስብከት ጉዳዩን እየተከታተለ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ሊሠራ ይገባል።  የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውም ክትትል በማድረጉ ሂደት የራሱን ድርሻ የሚወጣ ይሆናል።   ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ? ሊቀ ኅሩያን ሠርፀ አበበ፡- ሀገራዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን በፍቅርና በሰላም መሥራት አለብን።  ጦርነት አውዳሚ እንጂ ጠቃሚ አይደለም።  በሀገራችን ፍቅር እንዲኖር ካስቀየምነው ፈጣሪ ጋር እርቅ መፈጸም አለብን።  ክርስቲያን ተስፋ አይቈርጥምና ዛሬ የጨለመውን ነገ እንደሚነጋ አስበን መኖር አለብን።  መንግሥት የዜጎቹንና የቅርሶቹን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ምእመኑም በጸሎት እየተጋ ይህ አስከፊ ጦርነት እንዲቆም እግዚያአብሔርን መለመን አለበት።  ቤተ ክርስቲያን በሀገር ላይ ሰላም እንዲመጣ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም።  ይህንንም ለዘመናት ስታከናውነው ነበረች፤ለወደፊትም የአስታራቂነት ድርሻዋን ትወጣለች።  መንግሥትም የአባቶችን ምክርና ተግሣፅ መስማትና መተግበር ይጠበቅበታል።  እግዚአብሔር በኢትዮጵያና በልጆቿ የሚጨክን አምላክ ባለመሆኑ በሀገራችንና በሕዝባችን መካከል ሰላምና ፍቅርን ያመጣልን ዘንድ እንማጸናለን።   እግዚአብሔር ሀገራችንን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቅልን።     
Read 630 times