ለምሳሌ በዓሉ ከረጅም የጾም ወቅት በኋላ የሚከበር መሆኑ ቢታወቅም አሁን አሁን ከዚህ የጾም በረከት የሚካፈል ምእመናን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የምንታዘብባቸው ገጠመኞቻችን ብዙዎች ናቸው። ሰዎች ተገደው የማይጾሙባቸው ምክንያቶች ቢኖሩም በምናለበት የሚደረጉ እና በተለይም ‹‹የአባቶች ጾም ነው›› በሚል እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በሌለ አስተምህሮ የሚጓዘው ምእመን ቁጥር ቀላል አይደለም። የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲህ ዓይነቱን ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የወጣ ሥጋዊ አካሄድ ሲያዩ ቸል ሊሉ አይገባም።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የአጽዋማት ወራት ሲመጡ የሚዘጉ የአጽዋማት ወቅት ሲያልቅ ደግሞ የሚከፈቱ የሥጋ መሸጫ ቤቶች ዛሬ ዛሬ በጾም ወራት ውስጥ በብዛት ተከፍተው ማየት የተለመደ ሆኗል። የእነዚህ ሥጋ ቤቶች ባለቤቶችም አብዛኞቹም ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሆነው መገኘታቸው ለክርስትና ህይዎታቸው ያላቸውን ግዴለሽነት ማሳያ ነው። የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲህ ዓይነቶቹን በስም ክርስቲያን የሆኑ ምእመናንን ‹‹ለምን?›› በማለት ሊጠይቋቸው፣ ‹‹ልክ አይደለም›› በማለት ሊገስጹአቸው ትክክለኛውንም መንገድ ሊያሳዩቸው ይገባል።
በሌላ በኩል ድግሞ የጾም ወቅት በሚጀምርበትና በሚፈጸምበት ጊዜም የሚታየው አቀባበል ሌላው ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጠና ፍጹም ሥጋዊ ሆኖ ነው የሚታየው። ጾም ሲፈታ በሚጾመውም ሆነ በማይጾመው ክርስቲያን ዘንድ የሚታየው ግርግር ከጾም ዓላማ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነው። ጾሙ ፍጹም ለሥጋዊ ፈቃድ ያደላ፣ የበዓሉ ዋና ዓላማ የተዘነጋበት ጊዜ ሆኖ ነው የሚያልፈው። አባቶች እንዲህ ዓይነቱን ሥር የሰደደ እና የቤተ ክርስቲያንን በዓላት መልክ የቀየረ አካሄድ ከዐውደ ምሕረት ትምህርት ባሻገር ለንስሐ ልጆቻቸው በተናጠልም ቤት ለቤት ሊያስተምሩ ብሎም ሊገሥጹ ይገባል።
በጾም ወራት በተለይ በሚጀምርበት እና በሚፈጸምበት ጊዜ ለምግብ ለመጠጥ የሚወጣው ወጪ እና የሚከናወነው ዝግጅትም ሌላው ፍጹም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያፈነገጠ፤ የአብርሃምንም መንገድ ያልተከተለ ነው። ብዙ ችግረኞች ባሉባት ሀገራችን ተካፍሎ መብላት፣ ምንዱባንን ማሰብ ከክርስቲያኑ ልቡና ከተሰደደ ቆየ። ለራስ ብቻ የሚታሰብበት ከአቅም በላይ የሚበላበት አሁን አሁን በዓሉ ምግብ መጠጥ ብቻ የሚመስልበት ትዕይንት ማየት የተለመደ ነው። ተካፍሎ መብላት፣ ችግረኞችን ስለማሰብ በተማርንበት የቤተ ክርስቲያን መድረክ ሳይቀር መታየቱ እጅግ ያሳፍራል። መብል መጠጡ ምንም የሌላቸውን ያላሳተፈ መሆኑ የክርስትናችንን ልክና መጠን የሚያሳይ ነውና ከዚህ ዘልማዳዊ አዙሪት እንወጣ ዘንድ ሊታሰብበት ይገባል።
‹‹በመጠን ኑሩ›› ተብሎ በተጻፈው አምላካዊ ቃል መሠረት በመጠን መኖርና እንደ አባቶች አስተምህሮ መመላለስ ይገባል። በዓል ሲደርስ በቤት ውስጥ ብቻ ተወስኖ በምግብና በመጠጥ ብቻ ማሳለፉ የክርስቲያን ወግ አይደለም። ብዙዎች በዓል ሲመጣ ለበዓሉ ያስፈልጋል የሚሉትን ከማዘጋጀት ውጪ በቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ሲሳተፉ አይታዩም። ለምሳሌ ከጾም በኋላ ስለሚበላው ምግብ እንጂ ካላቸው ላይ ለድሆች ስለማካፈል አያስቡም፣ በጾም ውስጥ ስለሚዘጋጀው ምግብ እንጂ ስለጸሎት፣ ንስሐ ስለመግባት ግድ የላቸውም፤ ጾመው ስለመዋል እንጂ ስለሌሎች የትሩፋት ሥራዎችም የሚመለከታቸው አይመስልም፤ ሰዓት ጠብቆ ስለመብላት እንጂ ጊዜ ቢኖራቸውም እንኳ ማስቀደስ ትውስ አይላቸውም።
ጾም ሲፈታም እንደዚያው ነው በዓሉን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፣ ከማኅሌቱ ከቅዳሴው በረከት ስለመካፈል የሚያስበው ምእመን ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ይህ ሥር የሰደደ በሽታችን ነውና በቃለ እግዚአብሔር ሊፈወስ ይገባዋል። የአብዛኛው ምእመን መልክ ይህን ይመስላልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብዙዎች ከዚህ ሥጋዊ ልምድ እንዲወጡ በትጋት ልትሠራ ይገባታል። የቤተ ክርስቲያን አጽዋማትንም ሆነ በዓላትን እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ልናሳልፍ ይገባል የሚለው የዛሬው መልእክታችን ነው።