Monday, 11 January 2021 00:00

የማንቂያ ደወል የሆነው የኮሚሽኑ ሪፖርት

Written by  ዲ/ን አሻግሬ አምጤ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ባለ ፷፬ ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ከኮሚሽኑ ሪፖርት መረዳት የሚቻለው የተፈጸመው ጥቃት ኦርቶዶክሳውያን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ነው። ሕይወታቸውን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበቃ ቢተርፉ እንኳ የሚበሉት እንዳይኖራቸው ንብረታቸውን መዝረፍ፣ ማቃጠል፣ አፈናቅሎ በማሳደድ በችግር ሲሠቃዩ እንዲኖሩ ማድረግ መሆኑን መረዳት ይቻላል። የኮሚሽኑ ሪፖርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስታሳስበው የከረመችውን የሚያጠናክር በአንጻሩ መንግሥት ጥቃቱ አጋጣሚ የፈጠረው እንጂ በተጠና መልኩ የተፈጸመ አይደለም በማለት ሲያስተባብል የከረመውን የሚያጋልጥ ሪፖርት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የወጣ ጠንከር ያለ ሪፖርት መሆኑን አንብቦ መረዳት ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ሪፖርቶች እውነት ተዳፍና የምትቀር እነርሱም ከተጠያቂነት እንድናለን እየመሰላቸው በወንጀል ላይ ወልጀል፣ በኃጢአት ላይ ኃጢአት የሚደርቡ ወገኖች ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ አስበው እጃቸውን ከጥፋት እንዲሰበስቡ ያደርጋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም “የመንግሥት የበታች ባለሥልጣናት ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ከለላ እጃቸውን እንዲሰበስቡ”ያሳሰበችው በመዋቅር ክርስቲያኖች ሲገደሉ፣ ሲሳደዱ፣ ሀብት ንብረታቸው እየተዘረፈ ቀሪው ሲቃጠል ብዙዎቹ የክልሉ መንግሥት የጸጥታ አካላት ቆመው ያዩ ስለነበር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መከላከያ ሠራዊት እንዳይገባ ከመከልከል ጀምሮ የተሳሳተ መረጃ ይሰጡ እንደነበር የሚያሳየው ኮሚሽኑ መረጃ  ባንክ ለመጠበቅ ብቻ ለግዳጅ እንዲሰማሩ መደረጉ መንግሥት የራሱን መቅር መመርመር ያለበት መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።

 

አጠቃላይ ግኝቱ “ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው ፵ የኦሮሚያ አካባቢዎች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል ከተሰማበት ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ ሰዎች በሰልፍ መልክ እና በቡድን ወደ ጎዳና በመውጣት፣ ጎማ በማቃጠል እና ድንጋይ ደርድሮ መንገድ በመዝጋት እንቅስቃሴዎች ከጀመሩ በኋላ ሰዎችን ማጥቃት እና ንብረት ማውደም የጀመሩ ሲሆን በማግስቱ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. ሁኔታው ተባብሶ ቀጥሏል” በማለት ያብራራል። መንገድ የተዘጋውም አድኑን ብለው ለሚጮኹ ክርስቲያኖች የክልሉ ልዩ ኃይልም ሆነ የክልሉ ፖሊስ አይቶ እንዳላየ በማለፍም ሆነ በአንዳንድ አካባቢዎች የጥፋቱ ተባባሪ በመሆኑ መከላከያ ደርሶ እንዳያድናቸው ነው። የኮሚሽኑ ሪፖርት በመቀጠልም “ወደ አደባባይ/ጎዳና የወጡ ሰልፈኞች ከፍተኛ ሁከት እና ጥቃት  ባስነሱባቸው አካባቢዎች በሰላም የሚኖሩ ሲቪል ሰዎች ሁከት ባስነሱ ሰዎችና ቡድኖች በየቤታቸው እና በየጎዳናው በግፍና በጭካኔ በዱላ፣ በጩቤ፣ በመጥረቢያ፣ በስለት ብረት፣ በድንጋይ እና በኤሌክትሪክ ገመድ ተደብድበው ተገድለዋል ። የአካል እና የሥነ-ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፤  ቤት እና ንብረታቸው ሆነ ተብሎ በእሳት ተቃጥሎ ወድሟል፤ በከፊልም ተዘርፏል። በዚህም የተነሣ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በግል ድርጅቶች፣ በመንግሥት እና በፖለቲካ ፓርቲዎች ንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። የጥቃቱ ባሕሪ እና መጠን እንደየአካባቢው ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም በአመዛኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃቱ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን  የእስልምና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ደግሞ በኦሮቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ነበር”  ይላል።

የቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ኃላፊነት የሚሰማቸው አካላት ከዚህ የተለየ አልዘገቡም። ምንም እንኳ የጥቃቱ ዒላማዎች ክርስቲያኖች የነበሩ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት የነበረውንና አሁንም ያልቆመውን የምትዘግበውና ዓለም እንዲያውቀው የምታደርገው ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች በዚህ ምድር ያላቸው አገር ኢትዮጵያ በመሆኗ ሰላም እንዲሰፍን እንጂ የገደለንን እንግደለው በሚል አገሯን ሀገራቸውን አያፈርሱም። እንዲህ ዓይነት ተልእኮ ያላቸው አካላት ቢኖሩም ቤተ ክርስቲያን ግን የሰላም ሐዋርያ እንጂ የጥፋት መልእክተኛ ባለመሆኗ የተፈጸመባትን የምትገልጠው እንኳ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም መረጋገጥ መፍትሔ እንዲሰጡ ብቻ ነው። ዓላማዋ አይደለም እንጂ እንደተፈጸመባት ጥቃት አጸፋውን ብትመልስ ሀገር እንደሀገር አትቀጥልም። ተልእኮዋ ሰማያዊ መሆኑ ቀርቶ ለኃላፊው ዓለም ይሆናል ማለት ነው።

አስቀድመን እንደገለጥነው ኮሚሽኑ ሙስሊሞች በበዙባቸው አካባቢዎች ክርስቲያኖች ዓላማ ሆነዋል። የደረሰውንም “የእስልምና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ደግሞ በኦሮቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ነበር” በማለት በማያሻማ መንገድ ገልጦታል። ይህ የኮሚሽኑ ሪፖርት ወቅት እየጠበቀና ምክንያት እየተፈጠረ ክርስቲያኖችን የመጨፍጨፍ ተልእኮው መፍትሔ እንዲበጅለት የጥሪ ደወል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን መንግሥት በራሱ መዋቅር ተሰግስገው ገዝግዘው ለመጣል የሚሠሩ አባላት እንዳሉት ተገንዝቦ ጥፋተኞችን እየለየ ለሕግ ማቅረብ እንደሚኖርበትም የሚጠቁም ነው።

“በወንጀል ድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩት ሰዎች ተግባራቸው ስልታዊ እና የተቀናጀ ወይም የሰፊ ጥቃት አካል መሆኑን በማወቅ የተሳተፉበት እንደነበር ያሳያል። በአጠቃላይ በዚህ ሪፖርት በዝርዝር እንደ ተመለከተው በጥቃቱ በተሳተፉት ሰዎች በቡድን በመሆን የተፈጸሙት ጥቃቶች እንደ ተራ ወንጀል ብቻ የሚቆጠር ሳይሆን ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ (crime against humanity) የግፍና ጭካኔ ወንጀል (atrocity crime) ስለመሆኑ የሚያሳዩ ናቸው” የሚለውን የኮሚሽኑን ሪፖርት ከጥቂት ወራት በፊት ከቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ ጋር ካደረግነው ቃለ መጠይቅ ጋር ማገናዘብ ይቻላል። “በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን አክራሪ እስልምና እያጠቃቸው እንደሆነ ከመንግሥት አካላት ጋር መተማመን አልተቻለም ነበር። አሁን ግን ሁሉም የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በሚገባ ተረድተውታል። ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በተደራጀና ተቋማዊ መልክ ባለው ሁኔታ እየተጠቁ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለመንግሥት እናመለክት ነበር።

ነገር ግን የመንግሥት ምላሽ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቃው በድንገት እንጂ በተደራጀ ኃይል አይደለም የሚል ነበር። እና የተደራጀ ኃይል ቤተ ክርስቲያንን እያጠቃ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች ነበሩን። ከማሳያዎች አንዱ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን የሚጠቁት አብዛኛውን ጊዜ ሕዝበ ሙስሊሙ በሚበዛባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች መሆኑ ነው። ሌላው ማርጋገጫ ደግሞ በቅርቡ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሽፋን በማድረግ እስልምና በሚበዛባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ  አካባቢዎች በምእመናን ሕይወትና ንብረት ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ጥቃት ነው።

ጥቃቱ  በተደጋጋሚ የሚፈጸመው በባሌ፣ በአርሲ፣ በጅማ፣ በሐረርጌና በከሚሴ ነው። ይህ የሚያሳየው ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው በአክራሪ ሙስሊሞች መሆኑን ነው። … በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚኖሩ በርካታ የሸዋ ኦሮሞዎች ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ከሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር በአሰቃቂ ሁኔታ ተገለዋል፤ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል እንዲሁም ተቃጥሏል” የሚለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጥኚ ግብረ ኃይል መድቦ ለበርካታ ወራት አስጠንቶ ከደረሰበት ማጠቃለያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ጉዳይ የሚያመለክተው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድታ ከመንግሥት ጋር ተባብራ በመሥራት ጥቃቱ እንዲቆም የምትችለውን ሁሉ ማድረግ የሚገባ መሆኑን ነው።

እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት እኛም ስንዘግበው እንደ ከረምነው ጥቃቱን አሰቃቂ ያደረገው “መንግሥት የሌለ እስከሚመስል ድረስ …የጸጥታ አካላት በበላይ አካል አልታዘዝንም፣ የግለሰብ ንብረት ጠብቁ አልተባልንም፣ የምንጠብቀው የመንግሥት የልማት ተቋማትን፣ ባንኮችን እና የሃይማኖት ተቋማትን ነው” ብለው መልስ እየሰጡ ሀገር ሲጠፋ እጃቸውን አጣጥፈው ማየታቸው ነው። ከዚህ የኮሚሽኑ ሪፖርት በመነሣት ጥቃቱ ዳግም እንዳይከሠት መሥራት ከመንግሥትም፣ ከእያንዳንዳችን ከፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ከሃይማኖት ተቋማትም የሚጠበቅ ተግባር ነው።

ለአንባብያን ተጨማሪ ግንዛቤ ለመፍጠር ከኮሚሽኑ ሪፖርት በመጥቀስ አሳባችንን እናጠቃል። “በሰዎች እና በንብረት ላይ ጥቃት ከመድረሱ አስቀድሞ ለመከላከል እና ጥቃቱን ለማስቆም የጸጥታ አካላት የነበራቸው ሚና ከቦታ ቦታ የተለያየ ሲሆን  በተወሰኑ አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሉ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ጉዳቱን ለመከላከል፣ ለማስቆም ወይም ለመቀነስ ተችሏል ። ጥቃቱ ያነጣጠረው በከፊል በብሔር እና ሃይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሰዎችን ከየቤታቸው ለይቶ በማሳደድና በማጥቃት በከፊል ደግሞ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ወይም ሲቪል ሰዎችን ሆነ ብሎ በማጥቃት ነበር፤ ጥቃቱ የተፈጸመው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እንደመሆኑ መጠንና በወቅቱ በማኅበራዊ ሚዲያና በተወሰኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይተላለፉ ከነበሩት መልእክቶች እንዲሁም በወንጀል ድርጊቱ ይሳተፉ የነበሩ ሰዎችና ቡድኖች ያሰሟቸው ከነበሩ መፈክሮች አንጻር፤ ጥቃቱን በመፈጸም ይሳተፉ የነበሩት ሰዎች  ተግባራቸው ስልታዊና የተቀናጀ ወይም የሰፊ ጥቃት አካል መሆኑን በማወቅ የተሳተፉበት እንደነበር ከነገሩ ሁኔታ ለመረዳት ይቻላል” ይላል። ኮሚሽኑ የተወሰነ አካልን መርጦ ለማጥፋት ታስቦበት የተፈጸመ መሆኑን ያረጋገጠውም ይህን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

 

Read 562 times