አባ ወልደ ጊዮርጊስ ፦ በመጀመሪያ እስከ ፲፫ ዓመቴ ዘመናዊውን ትምህርት ነበር ስማር የቆየሁት። በኋላ ግን በጊዜው በነበረው የኢህአፓ ግርግር ዘመናዊውን ትምህርት ትቼ ወደ ሠይፍ አጥራ ማርያም በመሄድ አብነት ትምህርት ቤት ገባሁ። በዚያም ከመምህር ዳንኤል ዘንድ ዳዊትን፣ውዳሴ ማርያምን እና ዜማ ተማርኩ። ለግ ማርያም ከየኔታ መንክር ዘንድ ቅኔን ተቀኝቻለሁ፤ለሁለተኛ ጊዜ ከመምህር ጽጌ ዋረብ አርባዕቱ እንስሳ እና ቅኔን ተቀኝቻለሁ። ቅኔውን በደምብ ከተማርኩ በኋላ ወደ ጎንጅ ተመልሼ አራት ዓይና ከነበሩት ከየኔታ ብርሃነ መስቀል እርባ ቅምሩን፣ ንባብና ዜማውን እንዲሁም አቡሻኽሩን አጠናቀቅሁ። ቅዳሴ ከመምህር ገብረ አምላክ፣ ብሉያትን፣ ሐዲሳትን እና ፍትሐ ነገሥትን ደብረ ሊባኖስ ገዳም ከመምህር ገብረ ሕይወት ተምሬአለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ወደ ምንኲስና ሕይወት እንዴት ገቡ?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ ጎንድ ለተክለ ሃይማኖት በዓል በሄድኩ ጊዜ የገዳሙን አኗኗር፣ የአንድነት ሕይወታቸውን እንዲሁም የአባቶችን ትሕትና ስመለከት “እንዲህ ዓይነትም ሕይወት አለ” ብዬ ወደዚያ ህይወት ተሳብኩ። ከዚያ በፊት ገዳም አላውቅም ነበር ለጊዜው በዓሉን አክብሬ ተመለስኩና ከአራት ወር በኋላ ተመልሼ ወደዚያ ገዳም ገባሁ። ወደ ገዳሙ ከገባሁ በኋላ ቅዳሴ እየተማርኩ፣ እያገለገልኩ፣ እየተላላክሁ ብዙ ጊዜ ቆየሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ ከዚያስ ወዴት ሄዱ?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ በገዳሙ እያገለገልኩ በነበርኩበት ወቅት ቅዳሴውን ተምሬ ጨረስሁ ከዚያም በኋላ ቅዳሴውን አስመስክር አሉኝ ቅዳሴውን ላስመሰክር ደብረ ዓባይ ሄድኩኝ። ከደብረ ዓባይ ስመለስ ወዲያውኑ ዝዋይ ትፈለጋለህ ተብዬ ወደ ዝዋይ ገዳም ሄድኩና ለሦስት ዓመት ያህል ቅዳሴ አስተማርኩ።
ነገር ግን እጅግ የበዛ የገዳም ፍቅር ስለነበረኝ ‹‹በአሁኑ ሰዓት ወንበር ላይ የምቀመጥበትና ሳንቲም የምቆጥርበት ዘመን አይደለም ዓይኔ ሳይፈዝ ደብረ ሊባኖስ ሄጄ መጋገር አለብኝ አለብኝ›› ብዬ ከዚያ ወጥቼ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄድኩ። ደብረ ሊባኖስ እንደደረስኩ ተቀበሉኝ በትርፍ ሰዓት ሰዓታት እየቆምኩ እያገለገልኩ ጋገራ ጀመርኩና እዚያ ለአንድ ወር ያህል ቆየሁ። ከወር በኋላ በጊዜው ያረፍኩባቸውና አሁን አቡነ ድሜጥሮስ የሚባሉት የያኔው ጓደኛዬ ‹‹የት እየዋልክ ነው?›› አሉኝ
‹‹ቤተ እግዚአብሔር እየጋገርኩ አልኳቸው።
‹‹ገዳም አይደል እንዴ ያደከው እንዴት ለሁለተኛ ጌዜ ትሄዳለህ?›› አሉኝ
‹‹እኔ ትንሽ በረከት ማግኘት አለብኝ ጎንድም ትንሽ ሳልጋግር ነው የመጣሁት›› አልኳቸው። እሳቸውም ‹‹የኔ ድርጎ ይበቃናል ሴት ደብር ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ቀድሞ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ይባላሉ እሳቸው ሰው ስለሌላቸው እሳቸው ጋር እሑድ እሑድ እየቀደስክ መማር ነው ያለብህ ›› ብለው ወደ መጽሐፍ ቤት ይዘውኝ ሄዱ።
ስምዐ ጽድቅ፦ ደብረ ሊባኖስ ምን ያህል ጊዜ ቆዩ ከዚያስ?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ ደብረ ሊባኖስ መጽሐፍ ቤት በጀት ሳይሠጠኝ ለሁለት ዓመት እየቀደስኩ ተማርኩና ኋላ በጀት ተሰጠኝ አዲሳቱንም ዘልኩ። መምህሬ እንዳይቆጡኝ ደግሞ ተደብቄ ብሉያት እማር ጀመር እንደጨረስኩ በዚህ የሚያውቁኝ ሰዎች በጊዜው መምህር ብርሃነ ሥላሴ አሁን አቡነ ዲዮስቆሮስ ለምስካዬ ኅዙናን ገዳም ሚሆነው እሱ ነው እናምጣው ብለው ነገሯቸው። እኔ ከተማ ነው አልገባም ብዬ እምቢ ብዬ ነበር መምህር ብርሃነ ሥላሴ /አሁን አቡነ ዲዮስቆሮስ / አባብለው ይዘውኝ ወደ ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም በመምህርት መጣሁ።
ለጊዜው የተማሪ ቤት እስከሚሠራ ድረስ በዚህ ተቀመጥ ብለው መሪጌታ ረታ የሚባሉ ገዳማዊ ሰው ቢሮ አስለቀቁልኝ እዚያ ሆኜ አምስት ተማሪዎችንም እንዳስተምር ሰጡኝ። እሺ ብዬ ተቀበልኩና ተመልሼ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄድኩ። ወደ አዲስ አበባም ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኔ ወደ አብረንታንት ዋልድባ ሄድኩኝ። ዋልድባ አንድ ወር ቆይቼ ስመለስ ደግሞ ‹‹መጣ›› ሲባል መኪና ይዘው መጥተው በግድ በልመና ወሰዱኝ ምስካዬ ኅዙናን በአምስት ተማሪ የጀመርኩት ሰባት ከዚያ አስራ አራት እያለ አሁን ካለንበት ደርሰናል ማለት ነው።
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን በአብነት ትምህርት ቤት ህይወትዎ አብነት ሆነውኛል የሚሏቸው መምህራን ወይም ሊቃውንት ካሉ ቢነግሩን
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ ከተማርኩባቸው መምህራን የወሰድኩት ጥሩም ደካማ ጎንም አለ። የነበርሁባቸው መምህራን በማስተማር በኩል ሁሉም ጥሩ ሊቃውንት ናቸው። የመጀመያው መምህሬ ጎንጅ ተክለ ሃይማኖት ምሥራቅ በለሳ የነበሩት የድጓ፣ የአቋቋም መምህር ናቸው። እጅግ ሲበዛ ቁም ነገረኛ እና ትጉህ መምህር ናቸው ነገር ግን በትንሽ ነገር ይበሳጫሉ። አንድ ተማሪ ሲያጠፋ ይናገራሉ፣ ይቆጣሉ። እኔ ወደ መምህርነት ከገባሁ በኋላ በተማሪ ላይ መበሳጨት ከንቱ መሆኑን ነው የተረዳሁት። ሁለተኛው መምህሬ ጎንጅ ተክለ ሃይማኖት የተማርሁባቸው የቅዳሴ መምህር ናቸው ድጓ አዋቂ፣ የአቋቋም መምህርም ናቸው። ከብቃት ደረጃም የደረሱ፣ ትግሃ ሌሊት ያላቸው ብርቱ መምህር ናቸው። እኚህ መምህር እኔ ሳውቃቸው አንድ ቀን ሲተኙ አይቻቸው አላውቅም። ሁል ጊዜ ማታ ድንገት ልጠራቸው ስሄድ ራሳቸውን ጉልበታቸው ላይ ደፍተው የተቀመጡበት ላይ ሆነው ነው የሚያንጎላጁት። የቤተ ክርስቲያን ደውል ሲደወል ወደ ጸሎት የሚሄዱ፤ ሕይወታቸው ሲደወል ከቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ወደ ወንበር ነው። ሕይወታቸው እንዲህ ነው፤ ነገር ግን ቁጡ ናቸው። ያሁሉ ትግሃ ሌሊት፤ መንኖ ጥሪት እጅግ የሚያስደንቅ ነው። የቸገረው ሰው ሲያገኙ ያላቸውን ከመስጠት አልፎ ተርፎ ልብሳቸውን አውልቀው እስከ መስጠት የደረሱ አባት ናቸው። ስመ እግዚአብሔር፣ የእመቤታችን ስም ከተጠራ ልብሳቸውን ወርውረው ጥለውት ይሄዳሉ እየተባለ ቤታቸው ጸበልተኛ፣ ተማሪ እንዳያስቸግራቸው እንዳይለምን ዘበኛ ያቆሙላቸው ነበረ። ያ ሁሉ ጉባኤ እያለ ግን ይበሳጫሉ።
ከእርሳቸው በኋላም የተተኩት መምህር ስራቸውን የሚያከብሩ፣ የሚወደዱ ሊቅ ናቸው፤ይሁን እንጂ ብስጩ ናቸው። የነገዋን ቤተ ክርስቲያን የሚረከብ ደቀ መዛሙርት የሚያፈሩ መምህራን ከተበሳጩ ተማሪ ደንጋጣ ስለሚሆን ዋጋ ቢስ ድካማቸው ከንቱ ነው ማለት ነው። እንደ አሁኑ ሰዓት ቢሆን ተማሪ አይከተላቸውም ነበር።
ሌላው ሁለቱ የቅኔ መምህራን ናቸው። አንደኛው የቅኔ ቤት መምህሬ የኔታ መንክር የሚባሉ የጎጃም ደግ ነበሩ፤ ዓይነ ስውር ናቸው ፤መልካም ስብእና ያላቸው፣ የማይበሳጩ፤ ሰው የማይንቁ ናቸው። ሁለተኛው በለሳ የተማርኩባቸው መምህር ጽጌ ዋረብ የሚባሉ ደግ መምህር ነበሩ፤ በጣም ሲበዛ ሰው አክባሪ ናቸው ሰውን ትክ ብለው አይተው ‹‹ይሄ ልጅ ለወደፊቱ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቀዋል›› ብለው የሚገምቱ ሰው ነበሩ። የቅኔ መምህራኑ ሁለቱም በጣም ደጋግ ነበሩ አብነት የምላቸው እነሱን ነው።
ከዚያ ቀጥሎ ጎንጅ ላይ የነበሩት ኔታ ብርሃነ መስቀል የሚባሉ የድጓው፣ የአቡሻኸሩ መምህር ናቸው። ያን ጊዜ ልጅነት ስለነበረ ማታ ማታ ነው አገባብ እርባ ቅምር የምማረው ዜማ ደግሞ በዐል በዐል አያየሁ ነው የምማረው። እሳቸው ደግሞ ተግተው ከማስተማር ውጪ ተማሪ ለምን ቀረ አይሉም። በጣም ይወዱኝ ነበረ ‹‹ልጄ በእግሬ ትተካለህ›› ይሉኝ ነበረ። ያን ጊዜ እኔ ቤተ እግዚአብሔር ጌሾ፣ ብቅል ስወቅጥ፣ እንጨት ስፈልጥ ውዬ ነው የምመጣ እሳቸው ደግሞ እየመጡ ‹‹የት እየዋልክ ነው?›› ብለው ይቆጣሉ።
‹‹ቤተ እግዚአብሔር እያገለገልኩ›› እላቸዋለሁ።
‹‹ተማር አላልኩህም ወይ ልጄ አንተ ሥራህ ይሄ አይደለም ገዳም እንጨት ሚፈልጥ አያጣም ቤተ ክርስቲያን የሚረከብ የለም አንተ ቤተ ክርስቲያን ትረከባለህ›› ይሉኝ ነበረ። ትልቁ አብነቴ እሳቸው ናቸው።
እሳቸው ገደል አህያ በተባለ ቦታ መጽሐፍ ቤት እያለሁ ነው የሞቱት። በሳቸው ሞት ዓመት አልቅሻለሁ። ሰው የሚለወጥ ቢሆን በሕይወት እንዲኖሩ ራሴን እለውጥላቸው ነበር። በጊዜው ‹‹ባህር ዳር የካህናት ማሰልጠኛ ኮርስ መሰልጠን አለብኝ ከዚያ ቶሎ እመለሳለሁ›› ስላቸው ‹‹አንተ አትመጣም እኔንም አታገኘኝም›› ይሉኝ ነበር ‹‹ጾመ ድጓ፣ ቅዳሴ፣ ሌላ በእጅ የተጻፈ ደግሞ የዜማ መጽሐፍ ነበረ እርሱን አስቀምጡ›› ስላቸው። ‹‹ አይ እኔን አታገኘኝም መጻሕፍትህን እቃ ቤት ታገኛቸዋለህ›› ብለውኝ ነበር። በጊዜው እመለሳለሁ ብዬ ስዋሻቸው አውቀውብኝ ስለነበር አትሂድ ብለውኝ ነበር። እኔ ግን በመሄዴ ወሰንኩ በኋላም ደብረ ሊባኖስ እንደምመነኩስ የምሰራውን ሥራ ሁሉ የወደፊት ሕይወቴን ነገሩኝ ።ከዚያ ከወጣሁ በዐሥር ዓመቴ ነው የተመለስኩት ያኔ ምክር ይመስለኝ የነበረው ሁሉ በሕይወቴ ሁሉም ነው የተፈጸመው በኋላ ሳስበው ነው የብቃት መሆኑ የገባኝ።
እኚህ አባት በፊት በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ግቢ ገብርኤል የድጓ መምህር ነበሩ መፈንቅለ መንግሥት ሲነሳ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ይህች ሀገር ሰላም የላትም፤ መማርያም የማስተማሪያም ጊዜም አይደለም ብለው›› የዘጉ አባት ነበሩ። እንግዲህ አብነት የምላቸው እሳቸውን ነው የቅኔ መምህራኑን እነዚያም ቢሆን ትግሀ ለሌሊት ማስተማር ሳይሰለቹ ጥዋት ማታ ከወንበር ገበታ መገኘት፣ ለጸሎት የማይሰለቹ ነበሩ።ይሄ ሁሉ ትጋት እያለ የሚናገሩት ትርፍ ንግግር እና ቁጣ እዚህ መጥቼ ሳየው ቅዱስ ጳውሎስ በገላ ፭፥፲፮—፳ የሥጋ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ ቁጣ መሆኑን እና እነዚያን የሥጋ ሥራዎች የሚፈጽም አይጸድቅም ስለሚል ያ ቁጣቸውን ነው የምናየው ወይስ የትኛውን ነው እያልኩ አስብ ነበር። እንግዲህ ባንድ ቀን ቁጣ ሙሴም ደብረ ናባው ቀርቷል ዮሐንስ አፈወርቅም ቁጡ ሰው አይጸድቅም ብሏል ከዚያ ወዲህ ቁጡ መምህርማ ምን ያደርጋል የሚል ትምህርት አግኝቼበታለሁ ትጋታቸው እንዳለ ሆኖ ትርፉን ነገር ደግሞ ትርፍ ነው ብዬ ትቼዋለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ በአምስት ተማሪዎች እንደጀመሩ እና ቁጥሩ እየጨመረ እንደመጣ ነግረውናል አሁን ምን ያህል ተማሪዎች ያስተምራሉ?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ በአሁኑ ወቅት ወደ ፻፸ ይሆናሉ።
ስምዐ ጽድቅ፦ የተማሪው ቁጥር በጣም ብዙ ነው ምናልባት ቁጥሩ መብዛቱ ያስቸግርዎት ይሆን? የተቸገሩበት ሁኔታ የወሰዱት መፍትሄ ይኖር ይሆን?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ ፦ አሁን የሚማሩት አብዛኛዎቹ የአብነት መምህራን ናቸው። ከየደብሩ የመጡ አለቆችም አሉ። ሌሎቹ ግራ ጌታ፣ ቀኝ ጌታ በሚል ማዕረግ የዝማሬ የቅኔ የአቋቋም የድጓ መምህራን ናቸው። መጀመሪያ ዓመት የነበሩ ተማሪዎች ትንሽ ያስቸግሩ ነበረ ሰዎች አለቆቹ ሳይቀሩ ‹‹እነዚያን ሁከት የሚያነሱትን አትመርቃቸው›› ይሉኝ ነበረ። ‹‹እንዴ ይሄንማ ካላለፍኩት ለወደፊቱ በጎ ሰው አይገጥመኝም ባለቤቱ ይሁዳን ባህሪው ሥራው አባረረው እንጂ ባለቤቱ ውጣልኝ አላለውም። እና ይሄንን ሳልፈው ነው ደግ ሰው የሚገጥመኝ›› እል ነበር። እነዚያ ካለፉ በኋላ ከዚያ ወዲያ ተማሪ አሁንም ሰይጣን እስከ ለተ ምጻት ይሰርልኝ እንጂ ኮሽ ብሎ አያውቅም አዋቂዎች ናቸው ስርዓት አክብረው ነው የሚመጡ ሁለት ሰዓት እዚህ ይደርሳሉ ውዳሴ ማርያም ጸሎት እንዳያልፋቸው ቀደም ብለው ነው የሚገኙት ከሩቅ ነው የሚመጡት ከአዲስ አበባ ዳርቻ ነው የሚመጡት አሁን አስራ አንድ ዓመት የተቀመጡም አሉ ብሉይም ተመርቀው ለጸሎተ ማርያም የማይለዩ አሉ። እንዲያው እንዲህ ስንል ምናልባት ሰይጣን ካፍ ሲወጣ እንዳይቀና እንጂ ያሉት ሁሉ አዋቂዎች ስለሆኑ በሚማሩበት ክፍል ውስጥ አንድ ሰው አልጎምጉሞ እኔን ቀና ብለው አይተውኝ አያውቁም። ይሄ የባለቤቱ ስጦታ የጉባኤው ባለቤት እንጂ የሰው አይደለም።
ስምዐ ጽድቅ፦ ቤተ ክርስቲያን እንደርስዎ ያሉ መምህራን እንዲበዙ ምን ማድረግ አለባት ብለው ይላሉ?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ ፦ በእርግጥ መምህራኑ መብታቸው ሲከበር እነርሱም ስራቸውን ያከብራሉ። በአብነት ትምህርት ቤት አንዱ ችግር የልብ መከፈል ነው። ሰው እጠቀምበታለሁ ብሎ ካልያዘ ለማስተማር ካልተጠራ በመምህርነት ወንበር መቀመጥ የእግዚአብሔር ጥሪ እንጂ የትምህርት ችሎታ አይደለም ብዬ ነው እኔ የምገምተው። ግን ከቤተ ክርስቲያናችንም ከበላይ አመራርም መረዳት ያለባቸው መምህራንን እንደየሁኔታቸው ፣እንደየስሜታቸው ማስተናገድ አለባቸው። ብህትውና የሚፈልግ አለ፣ ወንበሩን ብቻ እያስተማረ ማገልገል የሚፈልግ አለ እንግዲህ ደብረ ሊባኖስም ጎንጅም ስናድግ የኛ የመምህራን ችግር መምህራን ስብሰባ አይገቡም ነገር ውስጥ አይገቡም በቃለ እግዚአብሔር እንጂ ስለሰው አስተያየት፣ ስለአመራር አስተያየት የስልጣን ጥማት የላቸውም። አገርህ የት ነው? አይሉም እኔ ያሳለፍኩአቸው መምህራኑ ሁሉም አገርህ የት ነው? አይሉም ምግባርና ሃይማኖት ብቻ ነው የሚጠይቁት እኔም ያን ስላየሁ ሀገርህ የት? ነው ብዬ ተማሪን ጠይቄ አላውቅም።
እኛ ሰውን እናስተካክላለን ስንል የኛ ጠባይ ሰላማዊ ሰው ይለውጠዋል የመምህር ጠባይ እና ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ትኩረት ብትሰጥ ባሉበት መምህራን መብታቸው ቢጠበቅላቸው እላለሁ። ማስተማር የሚወድ አለ የአደባባይ ሰው አለ። መምህራን የአደባባይ ሰው አይደሉም የነገር ሰው አይደሉም፣ የጋዜጣ ሰዎችም አይደሉም። ይሄ ነው እንግዲህ ካለፍላጎታቸውና ካለ ችሎታቸው ሲነካኩአቸው ጥለውት የሚሔዱት። የስልጣን ጥማት ካለው አደባባይ የመውጣት ፍላጎት ካለው ከወንበሩ ጋር አይሄድም።ለምሳሌ ደብረ ሊባኖስም እያለን የድጓ ፣ የአቋቋም መምህራን እኔ አብሬአቸው ነበርኩ ጎረቤት ነን ምን ዓይይነት ፍላጎት እንደነበራቸው አውቅ ነበር። ከቤተ ክርስቲያን ፣ከአገልግሎት፣ ከጸሎት መልስ ሌላ ነገር ውስጥ አይገቡም። እንዲህ እኛ እንኳን ተማሪዎች አድመን ስናማክራቸው ‹‹ይሄ እኮ የጤና አይደለም ልጆቼ ይህን ተዉትና ዝም ብላችሁ ጸልዩ›› ይሉ ነበረ። እና መምህሩ እና ትምህርቱ፣ መምህሩና ተማሪው አልተገናኙም፣ መምህሩና ቦታው አልገናኝ እያለ ነው የሚያስቸግረው። የአካባቢው ሁኔታ ደግሞ ይወስነዋል።
ትልቁ ርእሳችን መምህራን መብታቸው ይጠበቅላቸው ከመምህራን፣ አብነትነት ሲወጡ ደግሞ ምክር ይሠጣቸው። ቤተ ክርስቲያን ምክር ትስጥ አንተን አይቶ የኋላ ልጅ ምን ይከተላል? ካንተ ምን እንጠብቃለን? ተብለው ለነሱም ምክር ያስፈልጋቸዋል ። ደግሞም እንደፍላጎታቻው መብታቸው መጠበቅ አለበት። የአባትነታቸው ጠባይ እንዳይቀየር ቤተ ክርስቲያን ክትትል ታድርግ። ብዙ ጊዜ በየቦታው የሚያጋጥም ነገር አለ። ብዙ ዘመን አገልግለው የኖሩ መምህራን አዲስ አመራር ሲመጣ የኖሩበትን የጸለዩበትን ቤት የጸለዩበትን ቦታ ልቀቁ አርጅታቸኋል ይሏቸዋል። ይሄ ግፍ ሰው እንዳናወጣ ያደርገናል።
ስምዐ ጽድቅ፦ ብዙዎቹ ቀን እየሰሩ በትርፍ ሰዓታቸው ለመማር ቢያስቡ ምን ዓይነት ነገር ይመቻችላቸዋል
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ ያው ትምህርት ቤቱ በግቢው ውስጥ ሲሆን ነው የሚመቸው እዚያ ሆነው ሲማሩ ማለት ነው። መማሩ እውቀት መጨመሩ ጥሩ ሆኖ አንድ ሰው ደግሞ ብቻውን ሆኖ የሚኖር ከሆነ የሌላው አይገባውም ከሰው ጋር መኖርን የተማሪ እና የአስተማሪ ፍላጎትን የጊዜውን ሁኔታ ያን መገንዘብ ያስፈልጋል። ግን ብዙ ጊዜ አስተማሪው የሚወጣ የሚገባ ከሆነ ተማሪውም ባካና ነው የሚሆነው። ችግሩን ስላየሁት ነው አሁን በአዲስ አበባ ያሉ ብዙዎቹ ቀን አስተምረን ማታ እንማራለን ማታ አስተምረን ቀን እንማራለን ሲሉ ተማሪው ሁሉ በዚያው ባካና ነው የሆነው። እውቀት መጨመሩ የመማር ፍላጎቱ ማዳበሩ እንዳለ ሆኖ የመምህሩ ልቦና በባከነ ቁጥር የተማሪውም እግረ ልቦና እየባከነ ነው የሚሄደው። መምህሮቻቸው በፈለጉአቸው ሰዓት ወንበር ገበታ ላይ አይገኙም ምንም ሳይጎድላቸው ማለት ነው። ለአብነት ትምህርት ቤቱ መነሻው ገጠር ነው ያ ሁሉ መምህራን ይዞሩ ነበር ወይ? ነው። የአቋቋሙም፣ የዝማሬው መምህርም ቤተ ልሔም ብንሄድ፤ ዙራምባ ብንሄድ ፤ጎንደር ብንሄድ አጫበሩ፣ ቆሜው፣ ጎጃም ብንሄድ እነዚህ ሁሉ መምህራን በዐት ይለቃሉ ወይ? ነው። እነዚያ መምህራን ፈልሰው አዲስ አበባ ገብተዋል። ያ ተማሪያቸው ግን ከዚያ አልተተካም። ለምን እውቀት ፈላጊዎች እናተርፋለን ሲሉ እያጎደሉ መጡ በበዐት ባለመገኘታቸው እኮ ነው። ከዚያ ለምኖ ነው የሚማረው ከዚህ ግን ድርጎ አለው፤ ደሞዝ አለው፤ ግን እንዳይቀመጥ የመምህሩ ቀልብ በባከነ ቁጥር ተማሪውም ባካና ይሆናል ነው የኔ ፍርሃት መማሩ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
ስምዐ ጽድቅ፦ ባገልግሎት ዘመንዎ መምህርም ከሆኑ በኋላ ተማሪም እያሉ ያጋጠሞት መልካምም ሆነ መጥፎ አጋጣሚ የሚሉት ካለ ቢገልጹልን?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ አንዴ አባይን ከጓደኛዬ ጋር ስንሻገር የገጠመኝ ነው ። ነሐሴ ፫/3/ ቀን በፍልሰታ በቆሎ ስንለምን ውለን ወዲህ ማዶ ቆይተን ወዲያ ማዶ ለመሻገር ታንኳ ይዘን ሳለ ማዕበል ተነሳና ተመለስን መንገድ ላይ አንድ ሰው እኔ ላሻግራችሁ አለን ዐሥር ዐሥር ሣንቲም ከፈልንና መካከል ላይ ስንደርስ ማዕበል ሞገድ ተነሳ እና እንግዲህ ለእቃው አትዘኑ ታኳው ከተገለበጠ ታንኳውን ያዙ ብሎ ያ ማዕበል መጥቶ ሲያሰጥመን ታንኳው ሳያሰጥመን ውስጥ ገብተን እንወጣለን ሰውየው ቆሞ አባይ ተወልዶ አባይ ያደገ እያለ ምንም ሳንል ብስብስ ብለን አባይ ዳር ላይ ደረሰን። ያን ተአምር ካየሁ በኋላ ‹‹ከእንግዲህ ሞት የለም›› ብያለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ መቼም እዚህ ለመድረስ ከእግዚአብሔር በታች አስተዋጽኦ ያደረገ አካል ሊኖር ይችላል የቤተ ሰብዎ የእናት አባትዎ አስተዋጽኦ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ እዚህ ለመድረሴ ትልቅ ቦታ አላቸው የሚሏውን ከቤተሰብዎ ጀምሮ ቢነግሩን?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ አባቴ በትምህርት ሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ለምሳሌ በመጀመሪያ ዲቁና ልቀበል ስሄድ ጳጳሱ ጠፉ ሁለተኛ ሂዱ ሲባል ተናድጄ አልሄድም አልኩኝ ኋላ አባቴ አታሎ ‹‹ ልጄ አይዞህ ክህነት እኮ የውስጥ ስልጣኔ ነው ረድኤተ እግዚአብሔር ይቀርብሃል አቃቤ መልአክ ያቀርባል ጤና ይሰጣል እንደው ክትባት እኮ ነው አይዞህ እንደሞግዚት አሳዳጊ ማለት እኮ ነው›› ብሎ ራሴን አሻሽቶ ‹‹አትበሳጭ እንጂ ክነት ጥሩ እኮ ነው፤ አይዞህ ለሰው ትተርፋለህ እሺ በልና ›› ብሎ ቀስ ብሎ እየጎተተ አንገቴን ታቅፎ ይዞኝ በመሄድ ዲቁና እንድቀበል አድርጓል። በኋላም የአገባብ መምህራችን ‹‹ልጄ አንተ የገዳም ሰው ነህ ስለ ዓለም እንዳታስብ›› ይሉ ነበር ። በፈቃደ እግዚአብሔር ነው ውስጡ ግን የአባቴም ፈቃድ ፈቃዱ ነው እላለሁኝ። እንድመነኩስ፣ መንፈሳዊ እንድሆን፣ ትልቅ ቦታ እንድደርስ ከዚያ በፊት ብዙ አጎቶቻችን ጥሩ ጥሩ የድጓ መምህራን ነበሩ እኔ ግን ይህን አላስብም ነበረ በፈቃዴ ወንበር ተክዬ እዚህ እደርሳለሁ ብዬ አላስብም ነበረ። እነዚህ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው።
ስምዐ ጽድቅ፦ ወላጅ አባትዎ?በቤተ ክህነት ትምህርት ትምህርቱ ነበራቸው?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ ፊት በልጅነቱ ዳዊት ደግሞ ነው የተወው አጎቱ የድጓ መምህር ነበሩ። ያን አስተምረውት በኋላ ላይ‹‹አንተ እርሻህን እረስ›› ብለው ወደ እርሻ እንዲመለስ አደረጉት ምን እንደታያቸው አላወቅም። አባቴ ጥሩ አራሽ አምራች ገበሬ የነበረ። መጀመሪያ ግን ዳዊት ደግሞ ነው የተወው።
ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንዎን ይባርክ እግዚአብሔር ያቆይልን እግዚአብሔር ያክብርልን?
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፦ እኔም አመሰግናለሁ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ተከታትሎ የት ወደቃችሁ ብሎ ያንዱን ሕይወት የሰው ኑሮ አይቶ እንዲረዳ ለትውልድ የሚተላለፍ በማድረጋችሁ አመሰግናለሁ። አሁንም ክትትላችሁ ይቀጥል እላለሁ።