ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ብርሃኑ፦ ስሜ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ብርሃኑ ይባላል። የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ነኝ።
ስምዐ ጽድቅ፦ በአሁኑ ሰዓት በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን ይመስላል?
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ፦ በሀገረ ስብከታችን መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም እንቅስቃሴ በተገቢው ሁኔታ እየተካሔደ ነው። ሥርዓተ ቅዳሴው፣ሥርዓተ ማኅሌቱ፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ከርእሰ ከተማው ጀምሮ በየወረዳው ባሉት አብያተ ክርስቲያናት እየተከናወነ ነው። በሰንበት ትምህርት ቤቱም አደረጃጀት ሆነ በስብከተ ወንጌሉ ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ አለ። ከተወሰኑት እና አንዳንድ ከፍተኛ ችግር ካለባቸው ወረዳና አጥቢያ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በስተቀር በአብዛኛው አገልግሎቱ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
ስምዐ ጽድቅ፦ የሀገረ ስብከቱን አመሠራረት ታሪክ ይንገሩን?
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ፦ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በ፲፱፻፹፩ ዓ.ም የተቋቋመ ነው። ከዚያ በፊት ጨርጨር፣ አዳልና ጋራ ጉራቻ በሚል የሚጠራና በሐረር ጠቅላይ ግዛት ሥር ሆኖ በአውራጃ ቤተ ክህነት ነበረ የሚመራው። በኋላ ላይ በዞን ደረጃ ሲዋቀር በወቅቱ በደርግ ዘመነ መንግሥት የዞኑ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ኢብራሂም ሀጂ የሚባሉ የሙስሊም እምነት ተከታይ ዞን እንደመሆኑ መጠን ለክርስትናው እምነትም የሃይማኖት አባት፤ የሃይማኖት መሪ ያስፈልገዋል ብለው መጀመሪያ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብ አስደርገዋል።
በዚህ መሠረት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሀገረ ስብከታችን ሲዋቀር ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመደቡልን። በሰዓቱ ብፁዕነታቸው እኒህን የዞን አስተዳዳሪ ‹‹ ኢብራሂም አይደለም ከዚህ በኋላ አብርሃም ብዬ ነው የምጠራው ›› ብለዋቸዋል። ከዛሬ ፴፪ ዓመት ጀምሮ በሀገረ ስብከት ደረጃ ተቋቁሞ እና ተዋቅሮ ሥራውን እየሠራ ነው ያለው። የክርስትናው እንቅስቃሴ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ ፤ አብያተ ክርስቲያናትም እየተስፋፉ መጥተዋል። አሁን በቅርብ ከዐሥር በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ አድርገናል። ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለው።
ስምዐ ጽድቅ፦ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት በተጀመረው ዘመቻ የጥፋት ዒላማ ከነበሩት አካባቢዎች አንዱ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ነውና እስኪ ስለዚህ ቢነግሩን?
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጡን ተከትሎ በነበረው ጥፋት ከተጎዱት ሀገረ ስብከቶች አንዱ የኛ ሀገረ ስብከት ነው። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ጉዳት ደርሶብናል፤ ምእመናን መከራ ተቀብለዋል፤ ተሠውተዋል በጭሮ ከተማ አቶ ብርሃኑ ዝቅአርጋቸው የሚባሉ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመን ሰማዕትነት ተቀብለዋል።
በአሰቦት ከተማ ደግሞ አቶ ተድላ ከተማ የተባሉ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፤ አካባቢውን እና ቤተ ክርስቲያንን ሲደግፉ የነበሩ ምእመን ተገድለዋል። ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተነሳው ሁከት ነው ሕይወታቸው ያለፈው። ሌላም የተጎዱ፣የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ብዙ ምእመናን አሉ። በዚያው አካባቢ ከ፳፩ በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል ፤ ከ፲፰ በላይ ሰዎች ተደብድበዋል፤ ከ፹፬ በላይ የተለያዩ ንብረቶች ወድመዋል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከ፭፻፷ በላይ የሆኑ ምእመናን በወቅቱ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። በአጠቃላይ ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የጥቃቱ ሰለባ ነበረ።
ስምዐ ጽድቅ፦ የደረሰው ጥቃት በቤተ ክርስቲያኒቱ ብሎም በሀገር ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ እንዴት ይገልጹታል?
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ፦ በመጀመሪያ በዚህ ጥቃት የተነሣ ምእመናኑ ተስፋ እየቆረጡ ነው ‹‹ዛሬ ባላሰብንበት እንዲህ ዓይነት ጥቃት ከደረሰ ነገ የመኖር ተስፋችን፣ ዋስትናችን ምንድነው?›› በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው ያሉት። እውነት ለመናገር ክርስቲያኑ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቆአል። እውነት ነው በዚህ ምክንያት አንዳንዶች አካባቢያቸውን እየለቀቁ ወደ ሰፊ ከተማ፣ ወደ ትልልቅ ከተማ፣ ወደ ቤተ ሰቦቻቸው እየሔዱ ነው። ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ጉዳት ነው፤ ትልቅም ኪሳራ ነው።
እንደ ሀገርም ስናይ ከፍተኛ ባለሀብት እና ከሰሩት ሥራ ላይ ለመንግሥትም ከፍተኛ ግብር የሚከፍሉ፤ በኢኮኖሚም ከተማውን የሚያንቀሳቅሱ፤ በሥራቸውም ብዙ ሠራተኞች ያስተዳድሩ የነበሩ ምእመናን ቦታውን ለቀው ከሄዱ እንደ ሀገርም ከተማዋ ትጎዳለች፤ እየተዳከመች ትመጣለች። ቅድም እንዳልኩት እንደ ቤተ ክርስቲያን በእነሱ መሄድ ሌላውም ተስፋ እየቆረጠ ለመሄድ ልቡ ይነሳሳል።
ስምዐ ጽድቅ፦ ከዚህ በመነሣት የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ዕጣ ፈንታ እንዴት ይገልጡታል?
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ፦ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ለቤተ ክርስቲያን አስጊ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ምእመናን ከሌሉ አገልግሎቱ ለማን ይሰጣል? ቅዳሴው፣ ስብከቱ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቶቹ ሁሉ ለማን ነው? ለምእመን ነው። ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ ምእመናን፤ ምእመናን ባሉበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን አለች። ስለዚህ ምእመናኑ እየፈለሱ ጥለው እንዳይሄዱ የማጽናት ሥራ ያስፈልጋል።
የነዋ ቤተ ክርስቲያን የተሻለ ነፃነት እንዲኖራት ፣ ምእመኑ በተሻለ ሁኔታ እና በነፃነት እምነቱን እንዲያራምድ ዛሬ ላይ ቆም ብሎ ትላንት ያልሠራናቸው ሥራዎች ምንድናቸው? ክፍተታችን ምንድነው? ነገስ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን ቆም ብሎ በማሰብ ሁሉም ሥራውን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ። ስለዚህ ተግተን ካልሠራን የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ዕጣ ፈንታዋ መዘጋት ነው የሚሆነው ማለት ነው።
ምእመናን ከሌሉ ቤተ ክርስቲያን ይዘጋል። ለማን ነው የሚቀደሰው? መባውን፣ ስጦታውን በመስጠት ቤተ ክርስቲያን እንዲከፈት የሚያደርጉት ምእመናን ናቸው። ቤተ ክርስቲያን እንዳትዘጋ ምእመናን ሊኖሩ ይገባል። ምእመናን ከሌሉ ካህኑም አይኖርም። ስለዚህ ካህኑም እንዳይፈልስ መሠራት ያለባቸውን ነገሮች አጠናክሮ መሠራት ያስፈልጋል። ክፍተታችንን ካልሞላን ከባድ ነው የሚሆነው፤ እንደቤተ ክርስቲያን መሥራት ያለብንን ቤተ ክርስቲያን መሥራት አለባት እንደ መንግሥትም ደግሞ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ ችግሮች እንዲፈቱ የማሳመን ሥራ መሥራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።
ስምዐ ጽድቅ፦ ከምእመኑ ጀምሮ እስከ ካህኑ እንዲሁም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ደርሷል፤ የጉዳቱ መጠን፣ በጥቃቱ ሳቢያ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ምእመናንና ካህናት ቁጥር በሀገረ ስብከቱ ደረጃ የተጠናከረ መረጃ አላችሁ? ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን በቦታው ያሉና የተረፉ ክርስቲያኖችን የማጽናቱ ሥራ፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ እንዴት እየተሠራ ነው?
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች በተመለከተ የተደራጀ ሙሉ ዳታ አለን በወቅቱም ለቅዱስ ሲኖዶስ ለቅዱስነታቸው ለብፁዕ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አስተላልፈናል፤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ፣አዲስ አበባ ለተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በአድራሻ በደብዳቤ አሳውቀናል። ይህን ያህል ሰው ተፈናቀለ፣ ይህን ያህል ሰው ተጎዳ የሚለውን አካተን በዝርዝር አሳውቀናል። የተጎዱትን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን የመፈለግ የመሰብሰብ ኀላፊነት አለባትና በዚህም መሠረት መልሰን እንድናቋቁማቸው፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ባቀረብነው መሠረት ለእያንዳንዳቸው ቡክ ወጥቶላቸው እንዲረዱ ጥረት እያደረግን ነው።
ይህ ጥቃት የደረሰው በሰኔ ፳፫ ብቻ አይደለም ለምሳሌ ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም በመሰላ ወረዳ ዕርቀ ሰላም ሞገስ የምትባል መምህርት የ፲፭ ቀን አራስ የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኝ የሆነች ሴት በግፍ በድንጋይ ተወግራ ተገድላለች። እዚያው ወረዳ ላይ ከ፺፭ በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል። ሁለት ከብቶች በቁማቸው ተቃጥለዋል። አትክልቶች ተጨፍጭፈዋል እንዲሁ ኅዳር ፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም በደበሶ፣ በሂርና፣ በዶባ ፣በቀራሮ ጊዮርጊስ፣ በበዴሳ፣ በመጣቀሻ በተለያዩ ዞኖች ውስጥ ባሉት ወረዳዎች ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ የመጣ ነበረ። በተለይ በ፳፻፲፪ ዓ.ም በሀገረ ስብከታችን የነበረው እና ያሳለፍነው ፈተና ከባድ ነው።
እነዚህን የደረሱትን ፈተናዎች መልሶ እንዳይደገሙ፤ ጥቃቶች እንዲቆሙ ከመንግሥትም ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር፣ በማስረዳት በጽሑፍም ሪፖርት አድርገናል፤ በአካልም ቀርበን አስረድተናል። ከእግዚአብሔር በታች ሕዝቡ መንግሥትን ተስፋ አድርጎ ነው የተቀመጠው፤መንግሥት ይጠብቀኛል እያለ ነው። እግዚአብሔር ይመስገን ጥቃቱ ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችል ነበረ፤ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ነው ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ እና በቁጥጥር ሥር እንዲውል የተቻለው። አሁንም ካሉት የመንግሥት አካላት ጋር አብረን እየሠራን ነው። ችግሩ እልባት እንዲያገኝ አብረን ተቀራርበን እየሠራን ነው። ምእመናኑም ተስፋ እንዳይቆርጡ ጎን ለጎን የማጽናናቱን ሥራ እያከናወንን ነው።
በሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ እንጦንስ የሚመራ ቡድን ከሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ ኀላፊዎች፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ እንዲሁም ከምእመናን፣ከአዲስ አበባው ዐቢይ ኮሚቴ የተውጣጡ ልኡካን አንድ ላይ ተቀናጅተው በሚኤሶ፣ በጭሮ፣ በአሰቦት ቦታው ድረስ በመሄድ ተጎጂዎቹን አሰባስበን አነጋግረን አጽናንተናቸው መጥተናል። ከዚህም በተጨማሪ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር እና ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር በመቀናጀት ፣ቤታቸው ድረስ በመሄድ ቁሳቁሶችን በመስጠት፣የገንዘብ ድጋፍም አድርገንላቸዋል። አሁንም በዚሁ ላይ እየሠራን ነው፤ወደ ፊትም ይህንኑ አጠናክረን እንቀጥልበታለን።