Friday, 22 January 2021 00:00

ዘመኑን መዋጀት ተገቢ ነው

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት ውስጥ አንዱ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ምእመን የሚሰበሰብበት ፣ የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚከወኑበት ከዋዜማው (ከከተራው) ጀምሮ እስከ ዕለቱ የጥምቀት በዓል ድረስ አገልግሎቱ በሰፊው የሚሰጥ ከሌሎቹ የቤተ ክርስቲያን በዓላት ሁሉ ለየት ባለ ሁኔታ የሚከበር በዓላችን ነው፡፡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ፣ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን  ወጥተው ወደ ተዘጋጀላቸው ማደሪያ በመሄድ የሚከበር ታላቅ በዓላችን ነው፡፡  የጥምቀት በዓል ምእመናን በብዛት የሚገኙበትና የሚከበር ብቻ ሳይሆን በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች (ቱሪስቶች) የሚታደሙበት ታላቅ የአደባባይ በዓላችን ጭምርም ነው፡፡ ይህ  ሕዝብ በብዛት የሚሳተፍበት ታላቅ በዓል ሃይማኖታዊ ዕሴቱን ፣ ባሕላዊ ወጉን በጠበቀ መልኩ ሲከናወን መቆየቱ ዓለም አቀፍ ትኩረትን በመሳቡ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ለመመዝገብ የበቃ እንዲሁም ለኢትየጵያውያን በተለይም ለኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ጭምር ታላቅ ኩራትም ነው፡፡ 

 

ይህ ብዙ ሕዝብ የሚሳተፍበት የአደባባይ በዓል (ጥምቀት) በተለይ የዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል የተለየ የሚያደርገው በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተሰራጨ ፤በተለይም በአሁኑ ወቅት ደግሞ መልኩን ቀይሮ እና እጅግ የከፋ ሆኖ በመጣው የኮረና ወረርሺኝ ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ዘር፣ ሃይማኖት እና ቀለምን ሳይለይ ብዙዎችን እየገደለ ያለው ዓለም አቀፍ በሽታ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ተዳሮት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከትላንት ዛሬ የተሻለ ቢሆንም ወደ ትላንቱ እንዳንመለስና ቤተ ክርስቲያን ዳግም እንዳትዘጋ በዚህ የአደባባይ በዓላችን ላይ ወቅቱን የዋጀ ትልቅ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡

የጥምቀት በዓል በቤተ መቅደስ እና በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ከሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት በተለየ መልኩ በአደባባይ የሚከበርና በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበት እንደመሆኑ መጠን የቫይረሱ ስርጭት እንዳያባብሰው እጅግ ጥንቃቄን ያሻል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ ሰጥታ ከምታስተምረው፣ ከምትመክረው እንዲሁም ከምትከውን የጾም የጸሎትና የምሕላ አገልግሎት ጎን ለጎን ቫይረሱን ለመግታት የሚወሰዱ እንቅስቃሴዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ወቅት ነውና ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የኮቪድ-፲፱ ወረርሺኝ መከሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ዘርፈ ብዙ ተጽእኖ አስከትሏል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ሀገራችን ኢትዮጵያን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ጎድቶ አልፎአል አሁንም እየጎዳ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት ላይ ለመታደም ከመላው ዓለም የሚመጡ ጉብኚዎች ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ምክንያት የሆነው ወረርሸኝ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ አሉታዊ ተጽዕኖ በዚሀ እንዳይቀጥል የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከምእመናን እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ በአንድነት ሊሠሩ ይገባል፡፡

ሕዝብ በብዛት በሚገኝበት በዚህ የጥምቀት በዓል ላይ የኮቪድ-፲፱ ወረርሺኝ እንዳይስፋፋ የሚደረገው ቅድመ ጥንቃቄ ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ከዓሉ ዝግጅት ጎን ለጎን የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ስለሚቻልበትና ስለሚወሰደው ቅድመ ጥንቃቄ አብሮ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ኮቪድ ወደ ሀገራችን በገባ የመጀመሪያዎቹ ወራት አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ብሎም ምእመናን እንዳይሰበሰቡ እስከ ማድረግ መድረሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይህ ነገ ተመልሶ እንዳይመጣ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ አጥብቃ ልትሠራበት ምእመናንን ልታነቃበትና ራሳቸውንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማዳን የሚችሉበትን ትምህርት ልታስተምር ይገባታል፡፡

ዓለም አሁን እያስተናገደች ባለችው በዚህ አደገኛ ወረርሺኝ ተጠቂው ሰው እና የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ወረርሺኝ ሳቢያ ብዙዎች በጅምላ ሞተዋል ፤ ዛሬም ለቁጥር የሚያታክት የሰው ልጅ እየተቀጠፈ ያለበት ጊዜ ነውና ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን አባቶች እና አገልጋዮች እንዲሁም ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመናበብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትኖረው ምእመናን ሲኖሩ ነውና የሰዎች ደኅንነት ሰፊ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በመሆኑም  ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ተከታዮቿ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡  

ከጾም ፣ ከጸሎቱ እና ከምህላው ጎን ለጎን የጤና ባለሙያዎች ፣ የመንግሥት አካላት የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ይጠበቃል፡፡ በዓሉ የአደባባይ እና ብዙ ሕዝብ የሚሳተፍበት እንደመሆኑ በሽታውን ሊያስተላልፉ የሚችሉ እና ስርጭቱን የሚጨምሩ ድርጊቶችን ከማድረግ መቆጠብ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ሌሎች የመንግሥት አካላት የሚሰጡትን መመሪያ መተግበር ከእያንዳንዱ ክርስቲያንም የሚጠበቅ ነው፡፡

ክርስቲያን እንደመሆናችን መንፈሳዊውን መፍትሔ በጸሎትና በምህላ እየተጋን ቫይረሱ የሚሰራጭበትን መንገድ ለማጥበብ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ጭምብል ማጥለቅና ንጽሕናን መጠበቅ ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ ይህን ለማስፈጸም በየደረጃው የሚገኙ የተለያዩ አካላትንም መስማት እና መታዘዝ ይልቁንም ለክርስቲያን ተገቢ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሳይታጎል ይቀጥል ዘንድ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ወደ ቀደመ ስፍራቸው እንዲመለሱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬ ላይ አጥብቀው ሊሠሩ ይገባል፡፡

በየጊዜው መልኩን እየለወጠ የመጣውን ወረርሺኝ እንደ አመጣጡ ተቀብሎ ለጊዜው የሚያስፈልገውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ንቁ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ በራሳቸውም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከሚደርሰው ፈተና መታደግ ነውና፡፡ ሥርዓቱ ሳይቋረጥ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲቀጥል ምእመኑ የሚተላለፉትን መመሪያዎችንም ሆነ ትእዛዞች ሰምቶ ሊተገብር ይገባል፡፡ ምእመኑ ራሱ ከመጠንቀቅ አልፎ አንዱ ለሌላው አስተማሪ እና መካሪ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል፡፡ 

የአደባባይ በዓላችን ክብሩን ጠብቆ ሁሉም የሚመለከተው አካል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ዘመኑን መዋጀት እና በጥንቃቄ መጓዝ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ኃላፊነት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከጸሎት ጋር ጥንቃቄ ያስፈልጋል እንላለን፡፡

 

 

Read 558 times